የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ወታደሮች ከአምስት ወራት በፊት በባህር ዳር ከተማ ፈጽሟቸዋል የተባሉ “ከህግ አግባብ ውጭ የሆኑ ግድያዎች”፤ በዓለም አቀፍ ህግ መሰረት “የጦር ወንጀሎች ሊሆኑ ይችላሉ” ሲል አምነስቲ ኢንተርናሽናል አስታወቀ። ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋም፤ በኢትዮጵያ ውስጥ “ተንሰራፍቷል” ያለው “የተጠያቂነት እጦት፤ “በዓለም አቀፍ ህግ ወንጀል የሆኑ ከባድ በደሎችን የሚፈጽሙ አካላትን የሚያደፋፍር ነው” ሲል ወንጅሏል።
አምነስቲ ኢንተርናሽናል ይህን ያስታወቀው፤ ባለፉት ነሐሴ እና መስከረም ወራት በባህር ዳር ከተማ የተገደሉ 12 ሰዎችን በተመለከተ፤ ዛሬ ሰኞ የካቲት 18፤ 2016 ባወጣው አጭር ሪፖርት ነው። ዓለም አቀፉ ተቋም በዚሁ ሪፖርቱ በመጀመሪያ የዳሰሰው፤ በባህር ዳር ከተማ ቀበሌ 14 በተለምዶ አቡነ ሀራ እና ልደታ በሚባሉ አካባቢዎች የተፈጸመውን የስድስት ሰላማዊ ዜጎችን ግድያ ነው።
ስድስቱ የባህር ዳር ከተማ ነዋሪዎች የተገደሉት፤ በኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አባላት “በቅርብ በተተኮሱ ጥይቶች” መሆኑን አምነስቲ የዓይን እማኞችን እና የቤተሰብ አባላትን ዋቢ በማድረግ በሪፖርቱ ይፋ አድርጓል። የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ “ከህግ አግባብ አውጪ” ተገድለዋል ካላቸው “ሰላማዊ ዜጎች” መካከል፤ “በመኖሪያ ግቢያቸው እንጀራ እየጋገሩ ባሉበት በተተኮሰባቸው ጥይት እንደተመቱ” የዓይን እማኞች የመስከሩላቸው ወ/ሮ ይታጠቁ አያሌው አንዷ ናቸው።
በዚህ ጥቃት ሰለባ ከሆኑት ውስጥ፤ “በንግድ ስራ ይተዳደሩ ነበር” የተባሉት የ55 ዓመቱ አዛውንት አቶ አየነው ደፍረሽ እና ሁለት ልጆቻቸው ይገኙበታል። “እነዚህ ሶስት የቤተሰብ አባላት የተገደሉት፤ ከቤተክርስቲያን ወደቤታቸው በመመለስ ላይ እያሉ ጎዳና ላይ በጥይት ተመተው ነው” ሲል አምነስቲ ኢንተርናሽናል በሪፖርቱ ላይ አስፍሯል።
በአማራ ክልል በመከላከያ ሰራዊት እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል “የትጥቅ ግጭት” በተቀሰቀሰ በሁለተኛ ወሩ፤ በባህር ዳር ከተማ የተለያዩ አካባቢዎች ተካሄዶ በነበረው ውጊያ ወቅት ተፈጽመዋል የተባሉ ግድያዎችም በዛሬው የአምነስቲ ሪፖርት ተካትቷል። ባለፈው መስከረም ወር መጨረሻ ሰባ ታሚት በሚባለው የባህር ዳር አካባቢ፤ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ወታደሮች “ስድስት ሰዎችን ከህግ አግባብ ውጭ መግደላቸውን” ማረጋገጡን አምነስቲ ኢንተርናሽናል አስታውቋል።
የመከላከያ ሰራዊት ወታደሮች መስከረም 29፤ 2016 አቶ ታደሰ መኮንን የሚባሉ የ69 ዓመት አዛውንት ቤት ከገቡ በኋላ፤ የእርሳቸውን ሶስት ልጆች እና በግቢው ውስጥ ተከራይ የነበረን ግለሰብ “ከህግ አግባብ ውጭ መግደላቸውን” የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋሙ በሪፖርቱ ገልጿል። ወታደሮቹ የሟቾቹ አስከሬን እንዳይነሳ በመከልከላቸው፤ ከጠዋቱ ሶስት ሰአት እስከ ቀኑ 10 ሰአት ድረስ በመንገድ ላይ ተዘርግቶ መቆየቱን ሶስት የዓይን እማኞች እንደነገሩት አምነስቲ ኢንተርናሽናል በሪፖርቱ ላይ አመልክቷል።
ጥቃቱ በተፈጸመበት ወቅት በስፍራው የነበሩ የአቶ ታደሰ የቤተሰብ አባል በበኩላቸው፤ የሟቾቹን የቀብር ስነ- ስርዓት በአቅራቢያቸው በሚገኝ ቤተ ክርስቲያን ለመፈጸም ጭምር ስጋት እንደነበረባቸው ለተቋሙ አስረድተዋል ተብሏል። በዚህም ምክንያት የሟቾቹ የቀብር ስነ- ስርዓት የተካሄደው፤ ከአካባቢው ራቅ ባለ ቤተ ክርስቲያን መሆኑን አምነስቲ ኢንተርናሽናል ጠቅሷል።
በመስከረም ወር መጨረሻ በባህር ዳር ከተማ መገደላቸው ከተረጋገጡ ግለሰቦች መካከል፤ “በጤና ጣቢያ ውስጥ ህክምና እየተከታተለ እያለ የተገደለ አንድ ታካሚ” እንደሚገኝበት ዓለም አቀፉ ተቋም በዛሬው ሪፖርቱ አስታውቋል። በእዚሁ ጤና ጣቢያ ውስጥ የሚሰሩ የጤና ባለሙያዎችን፤ የመከላከያ ሰራዊት ወታደሮች “ደብድበዋል፤ በጠበንጃም አስፈራርተዋል” ሲልም ተቋሙ አክሏል።
የመከላከያ ሰራዊት አባላት እና ተባባሪዎቻቸው ከ2013 ዓ.ም. ጀምሮ “በአለም አቀፍ ህግ ወንጀል የሆኑ ተግባራት ፈጽመዋል” በሚል ውንጀላ ሲቀርብባቸው መቆየቱን አምነስቲ ኢንተርናሽናል በዛሬው ሪፖርቱ አስታውሷል። ሆኖም በትግራይ የነበረው ጦርነት ካበቃ ከአንድ አመት በኋላ፤ የመከላከያ ሰራዊት ወታደሮች በአማራ ክልል “የሰብአዊ መብቶችን እና አለም አቀፍ የሰብአዊነት ህጎችን መጣስ ቀጥለዋል” ሲል ከስሷል።
አምነስቲ ኢንተርናሽናል በዛሬው ሪፖርቱ የሰነዳቸው “ከህግ አግባብ ውጭ የሆኑ ግድያዎች፤ በአለም አቀፍ የሰብዓዊነት ህግ (International Humanitarian Law) ላይ የተፈጸሙ “ከባድ ጥሰቶች” መሆናቸውን አስታውቋል። ሰውን “ከህግ አግባብ ውጭ መግደል” በአለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ህግ የተደነገገው “በህይወት የመኖር መብት ጥሰት ነው” ሲል ተቋሙ አስገንዝቧል። በባህር ዳር ከተማ የተፈጸሙት ግድያዎች “በዓለም አቀፍ ህግ መሰረት መሰረት የጦር ወንጀሎች ሊሆኑ ይችላሉ” በማለትም አምነስቲ ኢንተርናሽናል ድርጊቶቹን ለሚያስከትሉት ተጠያቂነት አጽንኦት ሰጥቷል።
“በኢትዮጵያ ውስጥ ተዓማኒነት ያለው የፍትህ እና የተጠያቂነት ስርዓት እስካሁን ድረስ ተግባራዊ አለመደረጉን” በሪፖርቱ የጠቀሰው ዓለም አቀፉ ተቋም፤ በዚህም ምክንያት “የተጠያቂነት እጦት” በሀገሪቱ መንሰራፋቱን አመልክቷል። ይህ ሁኔታ “በዓለም አቀፍ ህግ ወንጀል የሆኑ ከባድ በደሎችን የሚፈጽሙ አካላትን የሚያደፋፍር ነው” ያለው አምነስቲ ኢንተርናሽናል፤ “በሀገር አቀፍ ደረጃ የተንሰራፋው የፍትህ እና ተጠያቂነት እጦት አሁኑኑ ሊገታ ይገባዋል” ሲል አሳስቧል።
የኢትዮጵያ መንግስት በመከላከያ ሰራዊት አባላት እና ተባባሪዎቻቸው ላይ ሲቀርብባቸው በቆየው ውንጀላ ላይ፤ “ምርመራ ማድረግ እና ተጠርጣሪዎችን ለፍርድ እንዲቀርቡ እንዲያደርግም” ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ጠይቋል። የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የምስራቅ እና ደቡብ አፍሪካ ዋና ዳይሬክተር ቲጌሬ ቻጉታህ “የኢትዮጵያ መንግስት በባህር ዳር እና በመላው የአማራ ክልል እየተከሰቱ ካሉት ግጭቶች ጋር በተያያዘ የሚፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ላይ፤ ውጤታማ እና ገለልተኛ የሆኑ ምርመራዎችን በአስቸኳይ ሊጀምር ይገባል” ብለዋል።
“የኢትዮጵያ መንግስት በባህር ዳር እና በመላው የአማራ ክልል እየተከሰቱ ካሉት ግጭቶች ጋር በተያያዘ የሚፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ላይ፤ ውጤታማ እና ገለልተኛ የሆኑ ምርመራዎችን በአስቸኳይ ሊጀምር ይገባል”
ቲጌሬ ቻጉታህ፤ የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የምስራቅ እና ደቡብ አፍሪካ ዋና ዳይሬክተር
የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች ፈጽመዋል ተብለው በተጠረጠሩ ሰዎች ላይ በቂ ማስረጃ በሚገኝበት ጊዜ፤ “የዓለም አቀፍ የፍትሃዊ የፍርድ ሂደት መስፈርቶችን (fair trial standards) ባሟላ መንገድ” “ለፍርድ ማቅረብ” እንደሚገባ ቻጉታህ ተናግረዋል። ተጠርጣሪዎቹ ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙ፤ “ከሞት ቅጣት በስተቀር ተመጣጣኝ ቅጣት እንዲጣልባቸው ማድረግ ይገባል” ሲሉ ዋና ዳይሬክተሩ አጽንኦት ሰጥተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)