የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ካቢኔ፤ የመሬት ካሳ አሰራርን ለማሻሻል የቀረበለትን ደንብ አጸደቀ

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ካቢኔ፤ በክልሉ ለረዥም ጊዜ በስራ ላይ የቆየውን የገጠር እና ከተማ መሬት ካሳ አሰራር ለማሻሻል የቀረበለትን ደንብ አጸደቀ። የጊዜያዊ አስተዳደሩ ካቢኔ፤ የኢንቨስትመንት መሬት ማስተላለፍ እና ማስተዳደርን በተመለከተ የተዘጋጀውን መመሪያም “ማስተካከያዎች ከተደረጉበት በኋላ” ተግባራዊ እንዲደረግ ውሳኔ አሳልፏል።

በአቶ ጌታቸው ረዳ የሚመራው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ካቢኔ እነዚህን ውሳኔዎች ያሳለፈው፤ ትላንት እና ዛሬ ባካሄደው መደበኛ ስብሰባው መሆኑን የክልሉ ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ አስታውቋል። ካቢኔው ከተወያየባቸው ጉዳዮች አንዱ፤ ከዚህ ቀደም የፍትሃዊነት ጥያቄዎች እና አቤቱታዎች ሲቀርቡበት የቆየውን “የገጠር እና ከተማ መሬት ካሳ አሰራርን” የተመለከተ እንደሆነ ቢሮው ገልጿል። 

ይህንኑ አሰራር ለማሻሻል የተዘጋጀው ደንብ፤ “ባለመብቶች ካሳ እንዲያገኙ ከማድረግ ባሻገር በቋሚነት ዘላቂ መፍትሄ ሊያመጣ ይችላል” የሚል እምነት በካቢኔው ዘንድ ማሳደሩን የኮሚዩኒኬሽን ቢሮው ዛሬ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። በአሰራሩ ላይ ይቀርቡ የነበሩ አቤቱታዎችን “ትርጉም ባለው መንገድ ያሻሽላል” ብሎ ካቢኔው እንደሚያምንም መግለጫው ጠቅሷል። 

በመጋቢት 2015 ዓ.ም. የተዋቀረው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ካቢኔ ከዚህ ቀደም ባካሄደው ስብሰባ፤ መሬትን የተመለከተ ውሳኔ ማስተላለፉ ይታወሳል። ካቢኔው በዚሁ ውሳኔው፤ በትግራይ ክልል ለሁለት ዓመት በተካሄደው ጦርነት ወቅት የተደረጉ ከመሬት ጋር የተያያዙ ሽያጮች ተቀባይነት እንደማይኖራቸው አስታውቆ ነበር። 

የጊዜያዊ አስተዳደር ካቢኔ በአሁኑ መደበኛው ስብሰባው፤ ለኢንቨስትመንት የተመደቡ መሬቶችን ለማስተላለፍ እና ለማስተዳደር የቀረበለትን መመሪያ ተመልክቷል። ይህ መመሪያ አስፈላጊ ማስተካከያዎች ከተደረገበት በኋላ ወደ ስራ እንዲገባ ተወስኗል። በትግራይ ክልል በጦርነት ምክንያት የተቀዛቀዘውን ኢንቨስትመንት “ያነቃቃል” የሚል እምነት የተጣለበት ይህ መመሪያ፤ “አስፈላጊ ማስተካከያዎች ከተደረጉበት በኋላ ወደ ስራ እንዲገባ” መወሰኑን የትግራይ ክልል ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ገልጿል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)