በተስፋለም ወልደየስ
በጋምቤላ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ባለፉት ዘጠኝ ወራት ውስጥ በተካሄዱ ግጭቶች፤ ቢያንስ 138 ሰዎች መገደላቸውን እና በ113 ሰዎች ላይ ቀላልና ከባድ የአካል ጉዳት መድረሱን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አስታወቀ። በግጭቶቹ የተነሳ በርካታ ነዋሪዎች መፈናቀላቸውን፣ መኖሪያ ቤቶች እና ንብረቶች መቃጠላቸውን እንዲሁም ዘረፋ መፈጸሙን ኮሚሽኑ ገልጿል።
ብሔራዊው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ይህን የገለጸው፤ ካለፈው ዓመት ግንቦት ወር ጀምሮ እስከ ጥር 2016 ዓ.ም በጋምቤላ ክልል የተከሰቱ ግጭቶችን ከመረመረ በኋላ ባወጣው ሪፖርት ነው። ዛሬ ረቡዕ የካቲት 20፤ 2016 ይፋ የተደረገው ይህ የምርመራ ሪፖርት፤ ተደጋጋሚ ግጭቶች ያስተናገደው የኢታንግ ልዩ ወረዳን ጨምሮ በጋምቤላ ወረዳ፣ በጎግ ወረዳ እና በጋምቤላ ከተማ የተከሰቱ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን የዳሰሰ ነው።
ኢሰመኮ ሪፖርቱን ለማዘጋጀት፤ ግጭት ወደተከተሰባቸው ቦታዎች በአካል በመሄድ ከተጎጂዎች፣ ከተጎጂ ቤተሰቦች፣ ከአይን ምስክሮች ከሀገር ሽማግሌዎች እና ከሃይማኖት መሪዎች ጋር ቃለ መጠይቆች እና የቡድን ውይይቶች ማድረጉን ገልጿል። በመንግስት የተወሰዱ እርምጃዎችን በተመለከተ፤ በየደረጃው የሚገኙ የጋምቤላ ክልል መንግስት የጸጥታና አስተዳደር አካላትን እንዲሁም የፌዴራል ተቋማትን በማነጋገር መረጃዎችን እና ማስረጃዎችን ማሰባሰቡንም በሪፖርቱ አመልክቷል።

ከእነዚህ የመስክ ምልከታዎች በኋላ ተጨማሪ ክትትሎች በማድረግ በኮሚሽኑ የተዘጋጀው ባለ 15 ገጽ ሪፖርት፤ የግጭቱን መነሻ እና ከዚያ በኋላ በነበሩት ጊዜያት በተለያዩ አካባቢዎች የደረሱ ጥቃቶች፣ ግጭቶች እና ጉዳቶችን በዝርዝር የያዘ ነው። በጋምቤላ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች በየጊዜው ለሚያገረሽው ግጭት በመነሻነት የተጠቀሰው በግንቦት 2015 ዓ.ም. በኢታንግ ልዩ ወረዳ የተፈጠረ ክስተት ነው።
በወቅቱ በልዩ ወረዳው ፒኝዋ ቀበሌ ነዋሪ የነበረ ግለሰብ “ጫካ ለእንጨት ለቀማ ሄዶ መጥፋቱን” ተከትሎ፤ በፒኝዋ እና ሌር ቀበሌ ነዋሪዎች መካከል የተፈጠረው አለመግባባት ቀስ በቀስ ወደ ማህበረሰባዊ ግጭት (Inter-communal conflict) ተሸጋግሮ ጥቃቶች መድረሳቸውን ኢሰመኮ በሪፖርቱ አሰፍሯል። በእነዚህ ጥቃቶች ቢያንስ 82 ሰዎች ሲገደሉ፤ 80 የሚሆኑ ሰዎች ላይ ከቀላል እስከ ከባድ የአካል ጉዳት መድረሱን ኮሚሽኑ ገልጿል።
ከዚህ ክስተት ሁለት ወር በኋላ በልዩ ወረዳው ውስጥ በሚገኙት ሌር እና ፒኖ ቀበሌ ነዋሪዎች መካከል በተከሰተ የእርስ በእርስ ግጭት ቢያንስ፤ የ46 ሰዎች ህይወት ማለፉን ኢሰመኮ አስታውቋል። በግጭቱ 46 ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት መድረሱን እና ቁጥራቸው በውል የማይታወቅ ነዋሪዎች መፈናቀላቸውን ከተጎጂ ቤተሰቦች እና ከተለያዩ አካላት መረዳቱን ኮሚሽኑ በሪፖርቱ ጠቅሷል። ይህ ግጭት ከተካሄደ ከሳምንት በኋላ “የታጠቁ ቡድኖች” በሌር ቀበሌ ላይ ፈጽመውታል በተባለ ጥቃት፤ ቢያንስ የ19 ሰዎች ሕይወት ማለፉን እና 11 ሰዎች መቁሰላቸውን ኮሚሽኑ ባሰባሰበው መረጃ እና ማስረጃ ማረጋገጡንም በሪፖርቱ ላይ አስፍሯል።

የኢሰመኮ የምርመራ ሪፖርት፤ ከኢታንግ ልዩ ወረዳ በተጨማሪ በሰኔ እና ነሐሴ 2015 ዓ.ም. በጋምቤላ እና ጎግ ወረዳዎች የተፈጸሙ ጥቃቶችን ዝርዝር መረጃ አካትቷል። የጋምቤላ ክልል መንግስት መቀመጫ በሆነችው ጋምቤላ ከተማ፤ በግንቦት፣ ሰኔ እና ሐምሌ 2015 ዓ.ም በሰላማዊ ሰዎች ላይ የተፈጸሙ ጥቃቶች በተመሳሳይ መልኩ በሪፖርቱ ቀርበዋል። የኮሚሽኑ ሪፖርት፤ በጋምቤላ ክልል የተለያዩ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ በሚኖሩ የደቡብ ሱዳን ስደተኞች ላይ የደረሱ ግድያዎችንም ዳስሷል።
በጋምቤላ ክልል በተጠለሉ በደቡብ ሱዳን ስደተኞች ላይ ከሚያዝያ እስከ ነሐሴ 2015 ዓ.ም በደረሱ ጥቃቶች፤ ቢያንስ 27 ሰዎች መገደላቸውን እና በ12 ሰዎች ላይ ቀላልና ከባድ የአካል ጉዳት መድረሱን ኢሰመኮ በዛሬው ሪፖርቱ ይፋ አድርጓል። ስደተኞቹ “በታጠቁ ቡድኖች እና ግለሰቦች” ጥቃት የደረሰባቸው፤ በመጠለያ ጣቢያ ውስጥ ባሉበት እንዲሁም ከመጠለያ ጣቢያዎች ውጪ ለምግብ ፍለጋ እና ለተለያዩ ጉዳዮች ሲንቀሳቀሱ በነበረበት ወቅት መሆኑን ኮሚሽኑ ገልጿል።
በአንዳንድ አካባቢዎች ስደተኞችም ጭምር በግጭቶች ላይ ተሳታፊ እንደነበሩ ነዋሪዎች እና የመንግስት አካላትን ዋቢ አድርጎ ኢሰመኮ አስታውቋል። የጋምቤላ ክልል ከ384,000 በላይ የሚሆኑ የደቡብ ሱዳን ስደተኞችን፤ በሰባት የመጠለያ ጣቢያዎች በማስተናገድ ላይ ይገኛል። የክልሉ መንግስት፤ በስደተኞች እና በክልሉ ነዋሪዎች መካከል በየጊዜው የሚነሱ “አለመግባባቶችን” ለመፍታት፤ የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች አገልግሎት (RRS) ከተሰኘው የፌደራል ተቋም እና ከሌሎች አጋር አካላት ጋር በመቀናጀት “በርካታ ስራዎችን እያከናወነ” መሆኑን ኢሰመኮ በመግለጫው ዕውቅና ሰጥቷል።
“የተሟላ ፍትህ የሚረጋገጠው ጥፋተኞች ተጠያቂ ሲሆኑ፣ የተበደሉ ሲካሱ እና ለወደፊትም ተመሳሳይ አደጋ እንዳይከሰት አስፈላጊ እርምጃዎች ተግባራዊ ሲደረጉ ስለሆነ [የክልሉ መንግስት] ለዚህ ውጤት በቁርጠኝነት መስራት መቀጠል አለበት”
ዶ/ር ዳንኤል በቀለ፤ የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር
ሆኖም ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት፤ ስደተኞች ባሉባቸው እና ተደጋጋሚ ግጭቶች በሚያስተናግዱ ስፍራዎች “በቂ የጸጥታ ኃይሎችን በቋሚነት መመደብ” እንደሚገባ ኮሚሽኑ አሳስቧል። የክልሉ መንግስት እንደ ኢታንግ ልዩ ወረዳ ባሉ ስፍራዎች “አከናውኗቸዋል” የተባሉ “የማረጋጋት እና ሰላም የማስፈን ጥረቶች” በአንጻሩ በሪፖርቱ በጥሩ ጎን ተጠቅሰዋል። የክልሉ መንግስት “በወንጀል ድርጊት ላይ ተሳትፈዋል” ተብለው የተጠረጠሩ የአስተዳደር አመራሮችን እና የጸጥታ አባላትን በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ማድረጉንም ኮሚሽኑ “አበረታች” ብሎታል።
የጋምቤላ ክልል መንግስት የጀመራቸውን ተጠያቂነት የማረጋገጥ ስራዎች እንዲቀጥልበት በሪፖርቱ ያሳሰበው ኮሚሽኑ፤ የካሳ ጉዳይም ቸል ሊባል የማይገባው መሆኑን አጽንኦት ሰጥቷል። የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ፤ “የተሟላ ፍትህ የሚረጋገጠው ጥፋተኞች ተጠያቂ ሲሆኑ፣ የተበደሉ ሲካሱ እና ለወደፊትም ተመሳሳይ አደጋ እንዳይከሰት አስፈላጊ እርምጃዎች ተግባራዊ ሲደረጉ ስለሆነ ለዚህ ውጤት በቁርጠኝነት መስራት መቀጠል አለበት” ሲሉ ለክልሉ መንግስት ጥሪ አቅርበዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
[በዚህ ዘገባ ላይ ከቆይታ በኋላ ተጨማሪ መረጃ ታክሎበታል]