በትግራይ ክልል መቐለ ከተማ የሚገኙ ጡረተኞች ዛሬ ሐሙስ ባካሄዱት ሰላማዊ ሰልፍ፤ የ18 ወራት የጡረታ አበል ባለማግኘታቸው በአስከፊ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ገለጹ። የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር የጡረተኞችን ጉዳይ አጽንኦት ሰጥቶ፤ ግዴታውን እንዲወጣ ሰልፈኞቹ ጠይቀዋል።
ቁጥራቸው 250 ገደማ የሚሆኑት ሰልፈኞች፤ መፈክሮችን፣ የትግራይ ክልል እና የፌደራል መንግስት ባንዲራዎችን አንግበው ዛሬ ረፋዱን በመቐለ ከተማ ጎዳናዎች ተዘዋውረዋል። ሰልፈኞቹ ከያዟቸው መፈክሮች መካከል፤ “መንግስት ለጡረተኞች ራሱ ያወጣውን አዋጅ እና ደንብ ያክብር”፣ “ባለውለታ ይከበራል እንጂ በረሃብ እና በበሽታ አይቀጣም” የሚሉት ይገኙበታል።
በመቐለ ከተማ ከሚገኙ የተለያዩ የጡረተኛ ማህበራት የተውጣጡት ሰልፈኞች፤ ጥያቄያቸውን በመያዝ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ጽህፈት ቤት አምርተዋል። ሰልፈኞቹ ለአንድ ዓመት ከስድስት ወር የዘገየው ውዝፍ የጡረታ አበል እንዲከፈላቸው እና የጡረተኞች ቦርድ አመራሮች ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥያቄ አቅርበዋል። በጥቅምት 2015 ዓ.ም. በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ የተፈረመው የግጭት ማቆም ስምምነትም በአስቸኳይ ሙሉ በመሉ ተግባራዊ እንዲደረግም ጠይቀዋል።
በሰልፉ ላይ ንግግር ያደረጉት የመቐለ ከተማ ጡረተኞች ማህበር ኃላፊ ዶ/ር ገብረሚካኤል ንጉሰ፤ በተደጋጋሚ ጥያቄ ብናቀርብም “መንግስት ረስቶናል። እንደ ዜጋ እየቆጠረን አደለም” ሲሉ ቅሬታቸውን አሰምተዋል። በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ጽህፈት ቤት አማካሪ የሆኑት አቶ አማኑኤል አታኽልቲ፤ ችግሩ እንዲፈታ ለፌደራል መንግስት በተደጋጋሚ ጥያቄ መቅረቡን ተናግረዋል።
የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ጉዳዩን አስመልክቶ አሁንም ከፌደራል መንግስት ንግግር እያደረገ መሆኑንም አስታውቀዋል። የሰሜን ሪጅን ማህበራዊ ዋስትና እና የመንግስት ሰራተኞች ኤጀንሲ፤ ጡረተኞች እስካሁን ያልተከፈላቸውን አበል እንዲያገኙ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር እና የፌደራል መንግስት እየተነጋገሩ መሆኑን ለሰልፈኞቹ ጥያቄ በሰጠው ምላሽ አረጋግጧል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)