የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ካቢኔ የፕሪቶሪያው ስምምነት አፈጻጸም ውይይት፤ ከሁለቱ የስምምነቱ ፈራሚ ወገኖች ወጥቶ በአፍሪካ ህብረት ፓነል በኩል እንዲደረግ ጠየቀ። የጊዜያዊ አስተዳደር ካቢኔው፤ “በተለያዩ ምክንያቶች ሲጓተት ቆይቷል” ያለው የአፍሪካ ህብረት ፓነል ውይይትም በፍጥነት እንዲጀመር አሳስቧል።
በፌደራል መንግስት እና በህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) መካከል በጥቅምት 2015 ዓ.ም. በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ከተማ በተፈረመው የግጭት ማቆም ስምምነት ላይ፤ የዚህኑ አፈጻጸም ለመከታተል እና ለማረጋገጥ የሚረዳ የጋራ ኮሚቴ ይቋቋማል የሚል አንቀጽ ተካትቶ ነበር። በአፍሪካ ህብረት “ከፍተኛ ደረጃ” ፓነል የሚመራው ኮሚቴ፤ ከፈራሚ ወገኖች እንዲሁም ከምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ድርጅት (ኢጋድ) የሚወከሉ አባላትን እንደሚይዝ በስምምነቱ ላይ ተቀምጧል።
ኮሚቴው የግጭት ማቆም ስምምነቱን አፈጻጸም ለመከታተል እንዲያስችለው፤ በቁጥር ከ10 መብለጥ የሌለባቸው አፍሪካውያን ባለሙያዎች እንደሚመደቡለትም ስምምነቱ ያትታል። ስምምነቱን የፈረሙት ወገኖች፤ ከእነዚህ አፍሪካውያን ባለሙያዎች ጋር አብረው የሚሰሩ ባለሙያዎችን መመደብ እንደሚጠበቅባቸውም በስምምነቱ ላይ ሰፍሯል።
የፕሪቶሪያ ስምምነት አፈጻጸምን በተመለከተ ትላንት ረቡዕ የካቲት 20፤ 2016 አመሻሽ ውይይት ያደረገው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ካቢኔ፤ ለስምምነቱ ተግባራዊ መሆን የፌደራል መንግስት እና የአፍሪካ ህብረት ግዴታቸውን እንዲወጡ ጠይቋል። የጊዜያዊ አስተዳደሩ ካቢኔ፤ በትግራይ ክልል ዘላቂ ሰላም ይመጣ ዘንድ መፈጸም አለባቸው ያላቸውን ሶስት ጉዳዮች ዘርዝሯል።
የመጀመሪያው ጉዳይ፤ የትግራይ ክልል የግዛት ወሰን “በህገመንግስቱ መሰረት ይከበር” የሚለው ነው። አሁንም ድረስ “የትግራይ ክልል ስፍራዎችን ተቆጣጥረው ይገኛሉ” በሚል በተደጋጋሚ ውንጀላ የሚቀርብባቸው፤ የኤርትራ ሰራዊት እና የአማራ ታጣቂ ኃይሎች “ከትግራይ ጠቅልለው ይውጡ” የሚለው ጥያቄ በጊዜያዊ አስተዳደር ካቢኔው በሁለተኛ ነጥብነት ተነስቷል። ካቢኔው በሶስተኛነት የጠቀሰው ጉዳይ፤ ከቀያቸው የተፈናቀሉ የትግራይ ክልል ነዋሪዎች “ወደ መኖሪያቸው ይመለሱ” የሚለውን ነው።
የትግራይ ግዛታዊ አንድነትን በተመለከተ ያለውን ችግር፤ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር በፕሪቶሪያው ስምምነት እና በህገመንግስቱ መሰረት እንዲቋጭ ሲሰራ መቆየቱ በዛሬው ዕለት በክልሉ ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት በወጣ መግለጫ ላይ ተጠቅሷል። ሆኖም እስካሁን ባለው ሁኔታ፤ በሁለቱም ወገኖች በኩል “ስምምነት ላይ የተደረሰበት ነገር እንደሌለ” መግለጫው በድጋሚ አጽንኦት ሰጥቷል።
የካቢኔው ይህ ገለጻ፤ የፕሪቶሪያው ስምምነት አፈጻጸምን አስመልክቶ ኢፌዲሪ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ባለፈው ጥር ወር መግለጫ ከሰጠ በኋላ፤ የጊዜያዊ አስተዳደሩ የሰጠውን የተቃውሞ ምላሽ ያስተጋባ ሆኗል። የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ከአንድ ወር በፊት ባወጣው መግለጫ፤ “የአከራካሪ ቦታዎችን ሁኔታ በዘላቂነት ለመፍታት በህገ መንግስቱ መሰረት ህዝበ ውሳኔ እንዲደረግ፤ ጉዳዩ በዋናነት ከሚመለከታቸው ከአማራ እና ከትግራይ ክልሎች ጋር መግባባት ላይ ተደርሶ ነበር” ማለቱ ይታወሳል።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ካቢኔ በትላንቱ ስብሰባው፤ “በአንድ ወገን ውሳኔ ብቻ፣ በትግራይ ላይ ጫና ለማድረግ የሚደረገው እንቅስቃሴ እንዲታረም” ጠይቋል ተብሏል። ሆኖም በክልሉ ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት የተሰራጨው መግለጫ፤ “የአንድ ወገን ውሳኔ” የተባለውን ጉዳይ በግልጽ አላብራራም።
የፕሪቶሪያ ስምምነት ተግባራዊ እንዲሆን በጊዜያዊ አስተዳደሩ በኩል የሚጠበቀውን ሲሰራ መቆየቱን የገለጸው ካቢኔው፤ ቀጣይ ዘላቂ መፍትሄ እንዲመጣ “በተለያዩ ምክንያቶች ሲጓተት ቆይቷል” ያለውን የአፍሪካ ህብረት ፓነል ውይይት በፍጥነት እንዲጀምር ጠይቋል። የጊዜያዊ አስተዳደሩ ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ረዳኢ ሓለፎም ከትላንት በስቲያ ማክሰኞ ከትግራይ ቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ የፕሪቶርያው ስምምነት አፈጻጸምን የተመለከተ ውይይት “አደራዳሪዎች” በሚኖሩበት በቀጣይ ሳምንት እንደሚካሄድ አስታወቀው ነበር።
በፌደራል መንግስት እና በህወሓት መካከል ሲደረግ የነበረውን የሰላም ንግግር የመምራት ኃላፊነት ሲወጡ የቆዩት፤ የቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ ነበሩ። በሰላም ንግግሮቹ ላይ የቀድሞው የኬንያ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ እና የቀድሞዋ የደቡብ አፍሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር ፑምዚ ለምላምቦ “በደጋፊነት” ሲካፈሉ መቆየታቸውም ይታወሳል።
በቀጣይ በሚካሄደው የአፍሪካ ህብረት ፓነል ስብሰባ፤ የትግራይ ህዝብ ጥያቄዎች በአግባቡ እንዲመለሱ እና ችግሮችም እንዲፈቱ ጥያቄ እንደሚያቀርብ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ካቢኔ አስታውቋል። ከፕሪቶሪያ ስምምነት አተገባበር ጋር ያለው ችግር እልባት እንዲያገኝም፤ ጉዳዩ ከሁለቱ የስምምነቱ ፈራሚ ወገኖች ወጥቶ በአፍሪካ ህብረት ፓነል በኩል እንዲደረግ ካቢኔው ጠይቋል።
የፕሪቶሪያው ስምምነት እንዲደረስ የአፍሪካ ህብረትን ጨምሮ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ አሜሪካ፣ ኢጋድ፣ ኬንያ እና ሌሎች “ወዳጅ” በሚል የጠራቸው ሀገራት ሚና ትልቅ እንደነበር ካቢኔው አስታውሷል። ከስምምነቱ አፈጻጸም ጋር ተያይዞ ያለው ችግር እንዲፈታ እና ስምምነቱ ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ እንዲደረግ፤ እነዚህ አካላት የሚጠበቅባቸውን እንዲሰሩ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ካቢኔ ተማጽኗል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)