በተስፋለም ወልደየስ
ከፈረንሳዊው ጋዜጠኛ አንቷን ጋሊንዶ ጋር አብረው የታሰሩት፤ ፖለቲከኛው አቶ በቴ ኡርጌሳ ላይ ፍርድ ቤት ተጨማሪ አምስት የምርመራ ቀናት ፈቀደ። የአዲስ አበባ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ቀናቱን የፈቀደው፤ ፖሊስ “የተጠርጣሪውን ስልክ ምርመራ ውጤት ለመቀበል” ተጨማሪ ጊዜ እንዲሰጠው ያቀረበውን ማመልከቻ በመቀበል ነው።
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የሆኑት አቶ በቴ፤ “አፍሪካ ኢንተለጀንስ” ለተሰኘው የዜና ድረ ገጽ ዘጋቢ ከሆነው አንቷን ጋር በቁጥጥር ስር የዋሉት ባለፈው ሳምንት ሐሙስ የካቲት 14፤ 2016 ነበር። ከአዲስ አበባው ስካይ ላይት ሆቴል የተያዙት ፖለቲከኛው እና ጋዜጠኛው፤ ቦሌ ሩዋንዳ ወደሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ ተወስደዋል።
በተያዘቡት ዕለት ምሽት ወደ ቦሌ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የተዛወሩት አቶ በቴ እና አንቷን፤ ከአንድ ቀን በኋላ ፍርድ ቤት ቀርበዋል። የኦነጉ ፖለቲከኛ እና ፈረንሳዊው ጋዜጠኛ በአዲስ አበባ ከተማ የመጀመሪያ ፍርድ ቤት ቦሌ ምድብ ችሎት ባለፈው ቅዳሜ በቀረቡበት ወቅት፤ ፖሊስ “ከፋኖ እና ከኦነግ ሸኔ ጋር በመተባበር በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ሁከት ለማስነሳት በመሞከር” እንደጠረጠራቸው ገልጾ ነበር።
ፖሊስ በዚሁ የችሎት ውሎ፤ ሌሎች አባሪዎችን ለመያዝ እና በተጠርጣሪዎቹ የሞባይል ስልኮች ላይ ምርመራ ለማድረግ ተጨማሪ 14 ቀናት እንዲሰጡት ፍርድ ቤቱን ጠይቆ ነበር። ጉዳዩን ያደመጠው ችሎቱ፤ ለፖሊስ ስድስት ቀናትን ብቻ በመፍቀድ ለዛሬ አርብ የካቲት 22፤ 2016 ተለዋጭ ቀጠሮ መስጠቱ ይታወሳል። ሆኖም በትላንትናው ዕለት ጋዜጠኛ አንቷን ጋሊንዶ ከእስር ተለቅቆ፤ እኩለ ለሊት ገደማ ኢትዮጵያን በመልቀቅ ወደ ሀገሩ ተመልሷል።
የአዲስ አበባ ከተማ የመጀመሪያ ፍርድ ቤት አስቀድሞ በሰጠው ቀጠሮ መሰረት የተጠርጣሪዎቹን ጉዳይ ዛሬ መመልከት ሲጀምር፤ ቅድሚያ የማስረዳት ዕድሉን የሰጠው ለመርማሪ ፖሊስ ነው። ፖሊስ በተሰጡት ስድስት ቀናት፤ የአንድ ሰው ቃል መቀበሉን እና የተጠርጣሪዎችን የሞባይል ስልክ ለማስመርመር ወደ ፌደራል ፖሊስ መላኩን አስረድቷል። ሆኖም የስልክ ምርመራ ውጤቱን ተቀብሎ ከምርመራ መዝገቡ ጋር ማያያዝ እንደሚቀረው ገልጿል።
ፖሊስ በተሰጡት የምርመራ ቀናት፤ ከተጠርጣሪዎቹ አንዱን በዋስትና መልቀቁን አመልክቷል። የውጭ ሀገር ዜጋ የሆነው ይህ ተጠርጣሪ፤ እንዴት ወደ ሀገር ውስጥ እንደገባ ለማጣራት ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጥያቄ ማቅረቡንም ፖሊስ ተናግሯል። ተጠርጣሪውን በተመለከተ ቀሪ መረጃዎችን ለማሰባሰብ፣ የሌሎች ምስክሮችን ቃል ለመቀበል እንዲሁም ያልተያዙ ተጠርጣሪዎችን ለመያዝ፤ ተጨማሪ 14 ቀናት እንዲሰጡት ፖሊስ ፍርድ ቤቱን ጠይቋል።
በመርማሪ ፖሊስ ጥያቄ ላይ ያላቸውን አስተያየት እንዲያቀርቡ የተጠየቁት የአቶ በቴ ሁለት ጠበቆች፤ መቃወሚያቸውን በዝርዝር ለችሎቱ አሰምተዋል። አቶ ቱሊ ባይሳ የተባሉት የአቶ በቴ ጠበቃ፤ ፖሊስ ራሱ በዋስትና በለቀቀው ሰው ላይ ለሚያደርገው ምርመራ ደንበኛቸው በእስር መቆየት እንደሌለባቸው ተሟግተዋል። አቶ በቴ ኢትዮጵያ መሆናቸውንን በመጥቀስም፤ በዚህ ረገድ የሚጣራ ነገር እንደሌለ ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል።
አቶ ቱሊ ደንበኛቸው በቁጥጥር ስር የዋሉት፤ አሁን ከተለቀቀው ተጠርጣሪ ጋር “ተገናኝተሃል፤ የሀገር ምስጢር አሳልፈህ ሰጥተሃል” በሚል እንደነበር ለፍርድ ቤቱ በቃል ባቀረቡት መቃወሚያቸው አስታውሰዋል። ባለፈው ፍርድ ቤት በቀረቡበት ወቅት፤ ተጠርጣሪዎቹ “ፋኖ እና ሸኔን ለማገናኘት ይሰራሉ” የሚል ውንጀላ እንደቀረበባቸው ጠቅሰዋል። ሆኖም ደንበኛቸው የታሰሩት፤ ከውጭ ሀገር የመጣው ጋዜጠኛ በሰላማዊ መንገድ የሚንቀሳቀስ ፓርቲ አባል ከሆኑት አቶ በቴ ጋር “ውይይት በሚያደርጉበት ወቅት ነው” ሲሉ ጉዳዩ በፖሊስ እንደቀረበው እንዳልሆነ ተከራክረዋል።
ከዚህ ቀደም ከነበራቸው ልምድ እንደሚረዱት በሞባይል ስልክ ላይ የሚደረግ ምርመራን የሚያከናወነው የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢንሳ) መሆኑን በመግለጽ፤ ደንበኛቸው በዋስትና ቢለቀቁ በምርመራው ላይ ተጽዕኖ ሊያደርጉ የሚችሉበት ዕድል እንደሌለ አብራርተዋል። ምስክሮችን በተመለከተ ፖሊስ ያነሳው ሃሳብም ቢሆን፤ ምን ያህል መሆናቸው ያልተጠቀሰ እና የሚመሰክሩት ጉዳይ ያልተገለጸ መሆኑን አመልክተዋል። ፍርድ ቤቱ የፖሊስ ምርመራ መዝገብን ተቀብሎ፤ ፖሊስ በእያንዳንዱ ሰዓት ምን ሰራ የሚለውን እንደሚለከት ጠይቀዋል።
ፖሊስ “እስካሁን ያልተያዙ ሌሎች ተጠርጣሪዎችን ለመያዝ” በሚል ተጨማሪ ቀናት መጠየቁንም ጠበቃው ተቃውመዋል። ይህ የፖሊስ ጥያቄ ደንበኛቸውን በእስር አቁይቶ ከማጉላላት ውጪ፤ ይዞ ለማቆየት ምክንያት ሊሆን እንደማይችልም ለችሎቱ ተናግረዋል። አቶ በቴ “ከሸኔ ጋር ግንኙነት አላቸው” በሚል በፖሊስ ለቀረበው ውንጀላም፤ ደንበኛቸው ከተያዙበት ቀን ጀምሮ ለስምንት ቀናት ያህል በዚህ ጉዳይ “አንድም ማስረጃ አለመቅረቡን” በማንሳት ተከላክለዋል።
አቶ በቴ “በሰላማዊ መንገድ የሚታገሉ ናቸው” ያሉት ጠበቃቸው፤ በቁጥጥር ስር የዋሉትም አባል ከሆኑበት የአዲስ አበባ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ስብሰባ በኋላ ከጋዜጠኛ ጋር ውይይት እያደረጉ ባለበት ወቅት መሆኑን በድጋሚ አጽንኦት ሰጥተዋል። አቶ ቱሊ የደንበኛቸውን የፖለቲካ ተሳትፎን በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጭምር የተመሰከረ መሆኑን ገልጸዋል። “ይህንኑ የሚያሳይ ነው” የቦርዱን ደብዳቤን ለችሎቱ ዳኛ አስረክበዋል።
የፖለቲከኛው ጠበቃ በመጨረሻም፤ አቶ በቴ የተያዙበት ዋናው ምክንያት “ከፈረንጅ ጋዜጠኛ ጋር ተገናኝተሃል” በሚል እንደሆነ ጠቅሰው፤ ዋናው ተጠርጣሪ በፖሊስ ከተለቀቀ አባሪው የሚቆይበት ምክንያት የለም” ሲሉ ደምድመዋል። አቶ ቦና ያዘው የተባሉት ሁለተኛ ጠበቃ በበኩላቸው፤ የፖሊስ የምርመራ ሂደት “ተጠርጣሪውን ይዞ ወንጀል እየፈለገ የሚገኝበት ነው” ሲሉ ተችተዋል። ፖሊስ አቶ በቴን ከያዘ በኋላ በየጊዜው የሚቀያይራቸው ውንጀላዎች፤ ደንበኛቸው “በቁጥጥር ስር ሊያውል የሚያስችል በቂ ምክንያት እንዳልነበረ የሚሳይ ነው” ሲሉም አክለዋል።
የግራ ቀኙን ክርክር ያደመጡት ዳኛ የማጣሪያ ጥያቄዎችን ለመርማሪ ፖሊስ አቅርበዋል። ፖሊስ አቶ በቴን በምን እንደጠረጠራቸው በፍርድ ቤቱ ለቀረበለት ጥያቄ ሲመልስ፤ “ከሸኔ እና ፋኖ ጋር በመገናኘት ሁከት እና ብጥብጥ ለማነሳሳት ሙከራዎች አሉ” በሚል እንደሆነ ገልጿል። ይህን አስመልክቶ በደረሳቸው ጥቆማ መሰረት፤ ሁለቱን ተጠርጣሪዎች መያዛቸውን መርማሪው ፖሊስ አስረድተዋል።
ከተጠርጣሪዎቹ ከተያዙት የሞባይል ስልኮች ውስጥ አንደኛው ተመርምሮ ምንም እንዳልተገኘበት እና የሌላኛውን ምርመራ ውጤት እየተጠባበቁ መሆኑን አብራርተዋል። ተጨማሪ የሰነድ እና የሰው ማስረጃ በማሰባሰብ የምርመራ መዝገቡን እስኪያጠናቀቁ ድረስም፤ የጠየቁት 14 ቀናት እንዲፈቀድላቸውም መርመማሪው በድጋሚ ጠይቀዋል።
በዚህ መካከል ለመናገር ጠይቀው የተፈቀዳላቸው አቶ በቴ፤ በሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ውስጥ እንዳሉ እና በፓርቲያቸው የተመደበቡት ዘርፍም የፖለቲካ ኦፊሰርነት እንደሆነ አስታውሰዋል። አብሯቸው ታስሮ የነበረውን ጋዜጠኛ ከዚህ ቀደም እንደማያውቁት የተናገሩት አቶ በቴ፤ ከጋዜጠኛው ጋር የተገናኙት በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የፓርቲያቸውን አቋም ለማስረዳት እንደነበር አስረድተዋል። ከፈረንሳዊው ጋዜጠኛ ጋር የነበራቸው ቆይታም፤ በየሚቀረጽ ቃለ መጠየቅ ሳይሆን ውይይት እንደነበረም ጠቁመዋል።
ሲቪል በለበሱ ግለሰቦች በተያዙበት ወቅት ያሰሯቸውን ሰዎች “ከፍርድ ቤት የመያዣ ትዕዛዝ እንዳላቸው” መጠየቃቸውን ለፍርድ ቤት የተናገሩት አቶ በቴ፤ በዚህ ጊዜ ፖሊስ የሚጠረጥራቸውን ሰዎች ማቆየት ይችላል የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸው ገልጸዋል። ይህም ቢሆን “ህግ አክብረው” ወደ ፖሊስ ጣቢያ መሄዳቸውን እና የተቀረጸ ነገር እንዳለ ለማረጋገጥ የሞባይል ስልካቸውን ከፍተው እንዲያሳዩ በተጠየቁበት ወቅት መተባበራቸውን አስረድተዋል።
አብሯቸው የታሰረው ጋዜጠኛ ተመሳሳዩን እንዲያደርግ በተጠየቀ ጊዜ፤ የምንጮቹን ማንነት የመጠበቅ ኃላፊነት እንዳለበት በመግለጽ ፍቃደኛ ሳይሆን መቅረቱንም አስታውሰዋል። ያልተከፈተው የእርሱ ሞባይል ስልክ ምን የለበትም ተብሎ ተመርምሮ ሲመጣ፤ ራሳቸው ከፍተው የሰጡት የሞባይል ስልክ እስካሁንም ውጤቱ አለመታወቁ እንዳስገረማቸውም አልሸሸጉም።
በምርመራ ወቅት ጋዜጠኛው ወደ ሀገር ውስጥ ከገባ ጀምሮ በመንግስት የጸጥታ ኃይሎች ክትትል ውስጥ እንደነበር መገለጹን የጠቀሱት አቶ በቴ፤ ዋነኛው ተፈላጊ ተለቅቆ እያለ እርሳቸው በእስር መቆየት እንደማይገባቸው ተናግረዋል። የተጠርጣሪውን ማብራሪያዎች የሰሙት ዳኛ፤ የፖሊስን የምርመራ መዝገብ ጥቂት አፍታ ወስደው ተመልክተዋል። መርማሪ ፖሊስ ተጨማሪ ቀናትን የጠየቀበትን ምክንያት በድጋሚ ካጣሩ በኋላ፤ ፖሊስ የሚያቀርበውን “የስልክ ምርመራ ውጤትን ለመስማት” ለቀጣዩ ሳምንት ረቡዕ የካቲት 27፤ 2016 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)