የኦነግ የፖለቲካ ኦፊሰር አቶ በቴ ኡርጌሳ፤ በ100 ሺህ ብር ዋስትና ከእስር እንዲፈቱ በፍርድ ቤት ተወሰነ 

በተስፋለም ወልደየስ

“ሁከት እና በጥብጥ በማነሳሳት” ወንጀል ተጠርጥረው ላለፉት 13 ቀናት በእስር ላይ የቆዩት የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር አቶ በቴ ኡርጌሳ፤ 100 ሺህ ብር የዋስትና ገንዝብ በማስያዝ ጉዳያቸውን በውጭ እንዲከታተሉ በፍርድ ቤት ተወሰነላቸው። ለፖለቲከኛው ዋስትናውን የፈቀደው፤ የአዲስ አበባ ከተማ የመጀመሪያ ፍርድ ቤት ቦሌ ምድብ ችሎት ነው።

አቶ በቴ ሲቪል በለበሱ የጸጥታ ኃይሎች ተይዘው በቁጥጥር ስር የዋሉት፤ “አፍሪካ ኢንተለጀንስ” ለተሰኘው የዜና ድረ ገጽ ዘጋቢ ከሆነው  አንቷን ጋሊንዶ ጋር ሐሙስ የካቲት 14፤ 2016 በአዲስ አበባው ስካይ ላይት ሆቴል በውይይት ላይ በነበሩበት ወቅት ነው። ዛሬን ጨምሮ ለሶስተኛ ጊዜ ፍርድ ቤት የቀረቡት የኦነጉ ፖለቲከኛ፤ በፖሊስ ተደጋጋሚ የጊዜ ቀጠሮ ሲጠየቅባቸው ቆይቷል።

ዛሬ ረፋዱን በተካሄደው ችሎትም፤ ፖሊስ “ምርመራዬን አልጨረስኩም” በሚል ተጨማሪ 11 የምርመራ ቀናትን ጠይቋል። የአዲስ አበባ ከተማ የመጀመሪያ ፍርድ ቤት ባለፈው ሳምንት ሐሙስ በነበረው ችሎት ለፖሊስ ተጨማሪ አምስት የምርመራ ቀናት የፈቀደው፤ ፖሊስ የሚያቀርበውን “የስልክ ምርመራ ውጤትን ለመስማት” ነበር። 

በዛሬው ችሎት የተገኙት መርማሪ ፖሊስ፤ የአቶ በቴን የስልክ የምርመራ ውጤት ለመቀበል ለኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢንሳ) በተደጋጋሚ ጥያቄ ምማቅረባቸውን ሆኖም እስካሁን ውጤቱን አለመቀበላቸውን ገልጸዋል። ከዚህ በተጨማሪም የሰው ማስረጃ ለማሰባሰብ ተጨማሪ ቀናት እንደሚያስፈልጓቸው አስረድተዋል። 

የአቶ በቴ ጠበቃ የሆኑት አቶ ቦና ያዘው፤ በተጠርጣሪው ስልክ ላይ “ምርመራ ያደርጋል” የተባለው የመንግስት መስሪያ ቤት መሆኑን አስታውሰዋል። ይህ የመንግስት መስሪያ ቤት ውጤቱን ያላቀረበበት ምክንያት ለችሎቱ ሊነገር ሲገባው አለመደረጉ፤ ፖሊስ በተሰጡት ቀናት  ምንም እንዳልሰራ አመላካች መሆኑን ለችሎቱ አስረድተዋል። 

ፖሊስ በደንበኛቸው ላይ አራት የወንጀል አይነቶችን በማቀያየር ሲያቀርብ መቆየቱን የተናገሩት ጠበቃው፤ እስካሁን ያለው የምርመራ ሂደት አቶ በቴ ከታሰሩ በኋላ “ወንጀል እየተፈለገባቸው መሆኑን” የሚያሳይ መሆኑን ገልጸዋል። ይህ አይነቱ አካሄድ ደግሞ ህገ መንግስቱን፣ የወንጀል ህጉ እና የወንጀለኛ ህግ ስነ ስርዓትን የሚጣረስ መሆኑን አብራርተዋል። 

መርማሪ ፖሊስ እስካሁን አከናውኘዋለሁ በሚል ባለፈው ችሎት ያስታወቀው የአንድ ሰውን ቃል መቀበል መሆኑን ያስታወሱት አቶ ቦና፤ ይህ ግለሰብ ደንበኛቸው “እንዲታሰር የሚፈልግ ሹም ሊሆን ይችላል” ሲሉ ጥርጣሬያቸውን አጋርተዋል። ፖሊስ ገለልተኛ ተቋም ስለሆነ የመጣለትን ጥቆማ ተቀብሎ ሰው ማሰር ብቻ ሳይሆን፤ የራሱን ማጣራት ሊያደርግ ይገባ እንደነበር ጠበቃው አሳስበዋል። ሆኖም ፖሊስ ያደረገው “ለጥርጣሬ በቂ ባልሆነ ማስረጃ ሰውን አስሮ ወንጀል መፈለግ ነው” ሲሉ አቶ ቦና ተሟግተዋል። 

በእስር ላይ የሚገኙት ደንበኛቸው “ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል የሚያካሄዱ”፣ በዚህም “በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚታወቁ” መሆናቸውን አቶ ቦና ለችሎቱ አስረድተዋል። የአራት ልጆች አባት እና በአሁኑ ወቅት ህመምተኛ የሆኑት አቶ በቴ፤ በግብርና ስራ የሚተዳደሩ እና ቋሚ አድራሻ ያላቸው መሆናቸውን ጠበቃቸው ጨምረው ገልጸዋል። አቶ በቴ በዋስትና ቢለቀቁ በተፈለጉ ጊዜ በቀላሉ ሊገኙ የሚችሉ መሆናቸውን ያስገነዘቡት ጠበቃው፤ በዚህም መሰረት ፍርድ ቤቱ የዋስትና መብታቸውን እንዲጠበቅላቸው አመልክተዋል። 

በጠበቃው ያልተነሳ ነጥብ ካለ እንዲናገሩ ዕድል የተሰጣቸው አቶ በቴ፤ በራሴ እና በፖለቲካ ፓርቲዬ ላይ “አፈና ነው የተደረገብኝ” ብለዋል። የደህንነት መስሪያ ቤት ገለልተኛ ሊሆን እንደሚገባው የተናገሩት የኦነግ የፖለቲካ ኦፊሰር፤ መስሪያ ቤቱ “በእኛ እና በብልጽግና ፓርቲ መካከል ባለው ሰላማዊ ትግል መሃል በመግባት፤ እኔን እና የድርጅቴን እንቅስቃሴ ማፈን አልነበረበትም” ሲሉ ተደምጠዋል። 

እርሳቸው በቁጥጥር ስር የዋሉት ህገ መንግስታዊ መብታቸው ተጥሶ እንደሆነ የገለጹት አቶ በቴ፤ የሚዲያ እና የመናገር ነጻነት ሊከበር ይገባ እንደነበርም አጽንኦት ሰጥተዋል። “እስካሁን የተደረገብኝ ግፍ ነው” ያሉት ፖለቲከኛው፤ ፍርድ ቤቱ ይህን ተረድቶ በነጻ እንዲለቅቃቸው ጠይቀዋል። ደንበኛቸውን ተከትለው ተጨማሪ ነጥቦች ለማከል ዕድሉን የወሰዱት ጠበቃ አቶ ቦና፤ ከእርሳቸው ጋር ተይዘው የነበሩት የውጭ ሀገር ዜጋ “ነጻ” ተብለው መለቀቃቸውን ጠቅሰዋል።

ጠበቃው የጠቀሱት ፈረንሳዊው ጋዜጠኛ አንቷን ጋሊንዶ ከእስር የተለቀቀው ባለፈው ሳምንት ሐሙስ የካቲት 21፤ 2016 ነው። አንቷን በእስር በተለቀቀበት ዕለት ለሊቱን ወደ ሀገሩ ፈረንሳይ ተመልሷል። ፖሊስ በበነጋታው በነበረ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት፤ ጋዜጠኛው የተለቀቀው በዋስትና መሆኑን መጥቀሱ ይታወሳል። የአቶ በቴ ጠበቃ በዛሬው የችሎት ውሎ “ዋና ወንጀል አድራጊው ነጻ ተብሎ ተለቅቆ፤ አባሪው ላይ ወንጀል መፈለግ ህግን የሚጣረስ ነው” ሲሉ አቤት ብለዋል። 

ይህንን ተከትሎ ጉዳዩን የሚመለከቱት ዳኛ፤ ፖሊስ በምርመራ መዝገቡ የቀረውን እንዲያስረዳ በድጋሚ ጠይቀዋል። መርማሪ ፖሊስ፤ በተጠርጣሪው ጠበቃ እንደቀረበው በአቶ በቴ ላይ አዲስ ወንጀል እየፈለጉ አለመሆኑን ለፍርድ ቤቱ አስረድተዋል። በአቶ በቴ ላይ ምርመራ እያካሄዱ ያሉት ቀድሞም በተጠረጠሩበት “ሁከት እና ብጥብጥ ማነሳሳት” በሚለው ወንጀል መሆኑን መርማሪው ገልጸዋል። የስልክ የምርመራ ውጤት ከኢንሳ ለመቀበል የጠየቁት 11 ቀናት እንዲፈቀድላቸውም በድጋሚ ጠይቀዋል።

የግራ ቀኙን አስተያየት ያደመጡት የችሎቱ ዳኛ፤ አቶ በቴ 100 ሺህ ብር የዋስትና ገንዘብ በማስያዝ ጉዳያቸውን በውጭ ሆነው እንዲከታተሉ ውሳኔ ሰጥተዋል። ይህ የማይሆን ከሆነ ግን ፖሊስ መዝገብ አደራጅቶ በፍጥነት ክስ እንዲመሰርት ትዕዛዝ ሰጥተዋል። የዛሬው የፍርድ ቤት ውሎ የኦነግ ተወካይ በችሎት ተገኝተው ተከታትለዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)     

[በዚህ ዘገባ ላይ ከቆይታ በኋላ ተጨማሪ መረጃ ታክሎበታል]