በዘንድሮው ዓመት ለ50 ሺህ መምህራን “ልዩ የክረምት ስልጠና” ለመስጠት፤ “አስፈላጊው ዝግጅት መጠናቀቁን” የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ተናገሩ። በመጪዎቹ ሐምሌ እና ነሐሴ ወራት የሚሰጠው ይህ ስልጠና የቅድመ አንደኛ፣ የአንደኛ ደረጃ እና የሁለተኛ ደረጃ መምህራንን አቅም ለማሳደግ ያለመ መሆኑን ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
የትምህርት ሚኒስትሩ ይህን የገለጹት፤ የሚኒስትሮች ምክር ቤት የ2016 ዓ.ም. የሁለተኛው ሩብ አመት የስራ አፈጻጸም ግምገማ ላይ ባቀረቡት ሪፖርት ነው። በተለያዩ ዘርፎች በመከፋፈል ከትላንት በስቲያ የካቲት 26፤ 2016 በተካሄደው በዚህ ግምገማ፤ ፕሮፌሰር ብርሃኑ በማህበራዊ ዘርፍ ስር የታቀፉ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ባለፉት ስድስት ወራት የነበራቸውን የስራ አፈጻጸም በዝርዝር አቅርበዋል።
በማህበራዊ ዘርፍ ከተካተቱ አራት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች አንዱ በእርሳቸው የሚመራው የትምህርት ሚኒስቴር ነው። የትምህርት ቤቶችን ደረጃ እና ጥራት ለማሻሻል፤ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ባለፉት ስድስት ወራት ያከናወናቸው ስራዎች በሪፖርቱ ቅድሚያ ተሰጥቶታል። የአጠቃላይ ትምህርት የስርዓተ ትምህርት ለውጥ እና ትግበራ የደረሰበት ደረጃም በሪፖርቱ ተዳስሷል።
ፕሮፌሰር ብርሃኑ በዚሁ ሪፖርታቸው፤ የትምህርት ጥራትን ለማሻሻል ለትምህርት ቤት አመራሮች እና መምህራን ስለሚሰጡ ስልጠናዎች ማብራሪያ አቅርበዋል። “በትምህርት ቤት አመራሮች ዙሪያ የአንድ ዓመት ልዩ ስልጠና ስንሰጥ ነበር” ያሉት የትምህርት ሚኒስትሩ፤ በዚህ መርሃ ግብር አማካኝነትም ለ4,580 የትምህርት ቤት አስተዳዳሪዎች ስልጠና መሰጠቱን ተናግረዋል። ከእነዚህ ሰልጣኞች መካከል 850ዎቹ ሴቶች መሆናቸውንም ጠቅሰዋል።
ለመምህራን የሚሰጥ “መደበኛ ስልጠናን” በተመለከተ ደግሞ “ባሉበት ሁኔታ ጥሩ አስተማሪዎች እንዲሆኑ ለማድረግ” ያለመ ስልጠና በመጪዎቹ ሐምሌ እና ነሐሴ ወራት እንደሚካሄድ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ተናግረዋል። ከዚህ ቀደም ለመምህራን በዩኒቨርስቲዎች ይሰጥ የነበረው ስልጠና ባለፈው ዓመት “ተዘግቶ” እንደነበር ያስታወሱት የትምህርት ሚኒስትሩ፤ ይህ የሆነበት ምክንያት በትምህርት ጥራት ረገድ ችግር በመፈጠሩ እንደሆነ አስረድተዋል።
“ሁለት ሳምንት እያስተማሩ፤ ‘ተምረዋል፣ ሰልጥነዋል’ እያሉ እየለቀቁ፤ ከጥራት አኳያ በጣም ብዙ ችግር ገጥሞን ነበር” ያሉት ፕሮፌሰር ብርሃኑ፤ ዘንድሮ የትምህርት ካሌንደሩን በማስተካከል ሁለት ወር ለስልጠና ክፍት መደረጉን አትተዋል። ዘንድሮ የሚሰጠው ስልጠና ለቅድመ አንደኛ፣ አንደኛ ደረጃ እና ሁለተኛ ደረጃ መምህራን የተዘጋጀ እና “በሚያስተምሩት ትምህርት ውጤታማ” እንዲሆኑ የሚያደርግ የማስተማር ስነ ዘዴ (ፔዳጎጂ) እንደሆነም ሚኒስትሩ በሪፖርታቸው አብራርተዋል።
በዚህ ዓመት በሚጀመረው የአቅም ማሳደጊያ ልዩ የክረምት ስልጠና፤ 50 ሺህ መምህራንን ለማስተማር “አስፈላጊው ዝግጅት መጠናቀቁን” ፕሮፌሰር ብርሃኑ በሪፖርታቸው ጠቅሰዋል። ትምህርት ሚኒስቴር እነዚህን ስልጠናዎች ለማከናወን የሚያስችሉ “ሞጁሎችን” ከማዘጋጀት ጀምሮ ሌሎች አስፈላጊ ቅድመ ዝግጅቶችን እያደረገ መሆኑን በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የመምህራን እና የትምህርት ልማት ዴስክ ኃላፊ ወ/ሮ አሰገደች ምሬሳ ከአንድ ወር በፊት ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረው ነበር።
በተመረጡ ዩኒቨርስቲዎች እንደሚሰጥ የተነገረለት ይህ ስልጠና ይበልጡኑ ትኩረት የሚያደርገው፤ “የሁለተኛ ደረጃ የሳይንስ እና የእንግሊዝኛ ቋንቋ ትምህርቶች ላይ” መሆኑንም ኃላፊዋ በወቅቱ ገልጸዋል። አቅም ማጎልበቻ ስልጠናው የመምህራንን ፍላጎት ታሳቢ ያደረገ እንዲሆን በማሰብም፤ ለሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መምህራን የተዘጋጀ መጠየቅ ከአንድ ወር በፊት በትምህርት ሚኒስቴር አማካኝነት ይፋ መደረጉ አይዘነጋም። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)