የትግራይ ስደተኞች ያሉበት “አስከፊ” ሁኔታ እንዲሻሻል፤ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተቋማት በሳዑዲ አረቢያ መንግስት ላይ ጫና እንዲያሳድሩ ጥሪ ቀረበ 

በሰለሞን በርሀ

በሳዑዲ አረቢያ የሚገኙ የትግራይ ስደተኞች ያሉበት አስከፊ አያያዝ እንዲሻሻል፤ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተቋማት በሀገሪቱ መንግስት ላይ ጫና እንዲያሳድሩ ሳልሳይ ወያነ ትግራይ (ሳወት) ፓርቲ ጥሪ አቀረበ። እነዚህን ስደተኞች ደህንነታቸው ተጠብቆ ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ፤ የኢትዮጵያ መንግስት በአስቸኳይ መፍትሔ ሊያፈላልግ እንደሚገባም ፓርቲው አሳስቧል። 

በትግራይ ክልል ከሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች አንዱ የሆነው ሳወት ጥሪውን እና ማሳሳቢያውን ያቀረበው፤ ዛሬ ሰኞ መጋቢት 2፤ 2016 ባወጣው ሳምንታዊ መግለጫ ነው። ከኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ባለፈው የካቲት ወር ህጋዊ እውቅና ያገኘው ሳወት፤ “በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ” የትግራይ ወጣቶች በየወሩ ወደ መካከለኛው ምስራቅ ሀገራት በዋነኛነትም ወደ ሳዑዲ አረቢያ እንደሚሰደዱ በመግለጫው አመልክቷል።

ወጣቶቹ “ጦርነት የወለዳቸው መልከ-ብዙ ችግሮችን በመሸሽ” ቢሰደዱም፤ ወደ እነዚህ ሀገራት ከደረሱ በኋላ “የዘፈቀደ እስርን” ጨምሮ እስከ “ሞት” የደረሰ አስከፊ አደጋ እንደሚገጥማቸው ፓርቲው ገልጿል። ሳወት “አሳሳቢ” በሚል የገለጻቸው ባለፈው ሳምንት የወጡ ሪፖርቶች፤ የትግራይ ስደተኞች ጽዳቱ ባልተጠበቀ ማቆያ ማዕከሎች በተጨናነቀ ሁኔታ ታስረው እንደሚገኙ ማሳየታቸውን ጠቅሷል። ይህ የእስር ቤቶቹ ሁኔታ፤ ስደተኞቹን “ለበሽታ እና ለሞት” በከፍተኛ ሁኔታ እንዳጋለጣቸው ጠቁሟል። 

ከእነዚህ ተጋላጭ ግለሰቦች “በርካቶች መሞታቸውን” በሪፖርቶቹ መጠቀሱን ያነሳው ሳወት፤ ለዚህ “አስከፊ ሁኔታ” መፍትሔ ለማበጀት እንደ አምነስቲ ኢንተርናሽናል እና ሂዩማን ራይትስ ዎች ያሉ ድርጅቶች “ወሳኝ ሚና አላቸው” ብሏል። እነዚህ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ጉዳዩ ላይ ግንዛቤ እንዲፈጥሩ እንዲሁም የትግራይ ስደተኞች ሰብዓዊ አያያዝ እንዲረጋገጥ በሳዑዲ አረቢያ መንግስት ላይ ጫና እንዲያሳድሩ ፓርቲው ጠይቋል። 

ሳወት በዛሬው መግለጫው፤ የኢትዮጵያ መንግስት ለጉዳዩ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አሳስቧል። ይህን የዜጎች ሰቆቃ የኢትዮጵያ መንግስት “ችላ ሊለው አይገባም” ያለው ተቃዋሚ ፓርቲው፤ መንግስት በስደተኞቹ ላይ እየደረሰ ያለውን ስቃይ መረዳቱን እንዲገልጽ በመግለጫው ጠይቋል። ስደተኞቹ ደህንነታቸው ተጠብቆ ወደ ሀገራቸው ስለሚመለሱበት ሁኔታ፤ የኢትዮጵያ መንግስት በአስቸኳይ መፍትሔ እንዲያፈላልግም ፓርቲው ጥሪ አቅርቧል።

“ቀውሱን በዘላቂነት ለመፍታት፤ በትግራይ ካለው መፈናቀል ጀርባ ያሉት መነሻ ምክንያቶች መፈታት አለባቸው” ሲልም ሳወት በዛሬው መግለጫው አስፍሯል። ፓርቲው “የችግሩ መነሻ” በሚል በመግለጫው ከዘረዘራቸው ውስጥ “የወደቀ የፖለቲካ ስርዓት” የሚለው ይገኝበታል። አሁን ያለው የፖለቲካ ስርዓት “ለመጪው ጊዜ ተስፋ መስጠት ያቃተው ነው” ሲል ፓርቲው ተችቷል።

ፓርቲው በትግራይ ተወላጆች ላይ ተፈጽሟል የሚለው “የዘር ማጽዳት” እና “በኃይል ማፈናቀል”፤ ለትግራይ ወጣቶች በገፍ መሰደድ ምክንያትነት ከጠቀሳቸው ውስጥ ይገኙበታል። ሳወት በመግለጫው ማጠቃለያ ላይ፤ በትግራይ የሚገኙ የውጭ ሃገር ወታደሮች እንዲወጡ፣ ያልተገደበ ሰብዓዊ እርዳታ ወደ ተራቡ ዜጎች እንዲደርስ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ጫና እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርቧል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)