ፓርላማው የአንድ አባሉን ያለመከሰስ መብት በነገው ዕለት ሊያነሳ ነው

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በነገው ዕለት በሚያደርገው መደበኛ ስብሰባ፤ የአንድ የፓርላማ አባልን ያለመከሰስ መብት ሊያነሳ ነው። ምክር ቤቱ በዚህ ስብሰባው፤ የተጓደሉ የምክር ቤት ጉዳዮች ማካሪ ኮሚቴ አባላትን ለማሟላት የሚቀርብለትን የውሳኔ ሃሳብም መርምሮ ያጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል።

ፓርላማው ነገ ሐሙስ መጋቢት 5፤ 2016 በሚያካሄደው መደበኛ ስብሰባው፤ ለመመልከት ቀጠሮ የያዛቸው አጀንዳዎች ብዛት 12 ነው። ከእነዚህ አጀንዳዎች ሶስቱ፤ በኢትዮጵያ መንግስት እና በዓለም አቀፍ ልማት ማህበር መካከል የተደረጉ የብድር ስምምነቶችን ማጽደቅን የሚመለከቱ ናቸው። በተመሳሳይ መልኩ ከጣሊያን መንግስት ጋር የተደረጉ ሁለት የብድር ስምምነት አዋጆችም፤ በነገው ዕለት የፓርላማ ስብሰባ ላይ እንዲቀርቡ በአጀንዳ ዝርዝር ውስጥ ተይዘዋል። 

በነገው የተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ላይ ከሚቀርቡ ስምምነቶች ውስጥ፤ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ድርጅት (ኢጋድ) የሚመለከተው ይገኝበታል። የኢጋድ ማቋቋሚያን ለማሻሻል ኢትዮጵያ ያደረገችው ስምምነት፤ በነገው ስብሰባ ቀርቦ ውይይት ከተደረገበት በኋላ ለዝርዝር ዕይታ ወደሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ ይመራል ተብሏል። የውጭ ሀገር የስራ ስምሪትን በተመለከተ በኢትዮጵያ እና በዮርዳኖስ መካከል የተፈረመው የመግባቢያ ሰነድም በተመሳሳይ መልኩ ለቋሚ ኮሚቴ እንዲመራ በአጀንዳው ተካትቷል።

የተቃዋሚውን የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄን (አብን) ወክለው ፓርላማ የገቡት አቶ ክርስቲያን በቁጥጥር ስር የዋሉት በአማራ ክልል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በተዋጀበት ዕለት ባለፈው ሐምሌ ወር መጨረሻ ነው። እንደ እርሳቸው ሁሉ የአብን የፓርላማ ተወካይ የሆኑት ዶ/ር ደሳለኝ፤ በፖሊስ ተይዘው የታሰሩት ባለፈው ጥር ወር መጨረሻ ገደማ ነው

ዶ/ር ደሳለኝ “የተወካዮች ምክር ቤት የሚወያይበትን ማንኛውም አጀንዳ የመቅረጽ” ኃላፊነት ያለበት፤ “የምክር ቤት ጉዳዮች አማካሪ ኮሚቴ” አባል ጭምር ናቸው ነው። ይህ አማካሪ ኮሚቴ በፓርላማው አፈ ጉባኤ የሚመራ ሲሆን፤ ምክትል አፈ ጉባኤ፣ የፓርቲ ተጠሪዎችን ጨምሮ የምክር ቤቱ የፓርላማ ቡድኖች “ባላቸው መቀመጫ መጠን የሚወከሉበት” ነው። ፓርላማው በነገው ስብሰባው፤ የተጓደሉ የአማካሪ ኮሚቴ አባላትን ለመሟላት የሚቀርብለትን የውሳኔ ሃሳብ መርምሮ ያጸድቃል። 

በተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደር እና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ክርስቲያንም ሆኑ ዶ/ር ደሳለኝ፤ እስካሁን ድረስ ፍርድ ቤት አለመቅረባቸውን ቤተሰቦቻቸው ተናግረዋል። ሁለቱ ተጠርጣሪዎች በአሁኑ ወቅት በእስር ላይ ያሉት በአዲስ አበባ ከተማ ሜክሲኮ አካባቢ በሚገኘው የፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ ውስጥ ባለ የእስረኞች ማቆያ ውስጥ ነው።

የኢትዮጵያ ህገ መንግስት “ማንኛውም የተወካዮች ምክር ቤት አባል ከባድ ወንጀል ሲፈጽም እጅ ከፍንጅ ካልተያዘ በስተቀር ያለ ምክር ቤቱ ፈቃድ አይያዝም፤ በወንጀልም አይከሰስም” ሲል ይደነግጋል። በወንጀል የተጠረጠረ ማንኛውም የፓርላማ አባል የህግ ከለላ እንዲነሳ የሚቀርብ ማንኛውም ጥያቄ፤ ለአፈጉባኤው በጹሁፍ መቅረብ እንዳለበት የተወካዮች ምክር ቤት የአሰራር እና የአባላት የሥነ ምግባር ደንብ ይደነግጋል። የፓርላማ አባሉን የመያዝና እና የመክሰስ ስልጣን ያለው የፌደራል የፍትህ አካል በሆነ ወቅት፤ ጥያቄው ለተወካዮች ምክር ቤት የሚቀርበው በፍትህ ሚኒስትሩ መሆኑም በደንቡ ላይ ሰፍሯል።

ባለፈው የካቲት ወር አጋማሽ ያለመከሰስ መብታቸው የተነሳው የአዲስ አበባ ምክር ቤት አባሉ ዶ/ር ካሳ ተሻገር ጉዳይ የታየው፤ በፍትሕ ሚኒስቴር ጥያቄ ከቀረበ በኋላ እንደነበር በወቅቱ መገለጹ ይታወሳል። በተወካዮች ምክር ቤት የአሰራር እና የአባላት የሥነ ምግባር ደንብ መሰረት፤ የህግ ከለላ የማንሳት ጥያቄ በተመሳሳይ መልኩ ከቀረበ በኋላ የፓርላማው አፈ ጉባኤ በቀጥታ ሊያቀርበው አሊያም ለህግ እና ፍትህ ቋሚ ኮሚቴ ሊመራው ይችላል። 

የህግ ከለላ የማንሳት ጥያቄው የተመራለት የህግ እና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ዋና ድርሻ፤ ያለመከሰስ መብትን ለማንሳት የሚያስችሉ “በቂ አመላካች ሁኔታዎች መኖራቸውን ማረጋገጥ” እንደሆነ በደንቡ ላይ ተቀምጧል። ቋሚ ኮሚቴው ይህንን አመላካች ሁኔታዎች መኖራቸውን ለመገንዘብ ይረዳው ዘንድ፤ “የሰው ወይም የሰነድ ማስረጃዎች እንዲቀርቡለት ወይም የሚመለከተው አካል በጉዳዩ ላይ ቀርቦ እንዲያስረዳ” ሊያደርግ እንደሚችል በደንቡ ላይ ተመላክቷል። የፓርላማው ቋሚ ኮሚቴ “አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው ያለመከሰስ መብት የማንሳት ጥያቄው የቀረበበትን የምክር ቤት አባል ሊጠየቅ እንደሚችልም” ደንቡ አክሏል።

የህግ እና ፍትህ ቋሚ ኮሚቴው “የውሳኔ ሃሳብ” ሲያዘጋጅ፤ “ተፈጸመ የተባለውን ወንጀል አጠቃላይ ክብደት እና አመላካች ሁኔታዎችን በመገምገም” እንደሆነ የአሰራር እና የአባላት የሥነ ምግባር ደንቡ ያትታል። የተወካዮች ምክር ቤት በቋሚ ኮሚቴው የሚቀርብለትን የውሳኔ ሃሳብ መነሻ በማድረግ ውሳኔ ካስተላለፈ በኋላ አፈ ጉባኤው ጥያቄውን ላቀረበው መስሪያ ቤት እና ለሚመለከተው አካል ውሳኔውን  በጹሁፍ እንደሚያሳውቅ በደንቡ ላይ ተብራርቷል።

የተወካዮች ምክር ቤት በነገው ዕለት የአንድ አባሉን ያለመከሰስ መብት ካነሳ፤ አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ተመሳሳይ ውሳኔ የተላለፈባቸውን የክልል፣ የከተማ እና የፌደራል ምክር ቤት ተመራጮችን ቁጥር አራት ያደርሰዋል። ባለፈው የካቲት ወር በተካሄዱት የኦሮሚያ እና የአማራ ክልል ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባዎች የአቶ ታዬ ደንደአ እና የአቶ ዮሐንስ ቧያለው የህግ ከለላ መነሳቱ ይታወሳል። በዚሁ ወር አጋማሽ መደበኛ ስብሰባው ያካሄደው የአዲስ አበባ ምክር ቤትም፤ የአባሉን የዶ/ር ካሳ ተሻገርን ያለመከሰስ መብት በተመሳሳይ ሁኔታ አንስቷል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)

[በዚህ ዘገባ ላይ ከቆይታ በኋላ ተጨማሪ መረጃ ታክሎበታል]