ላለፈው አንድ ወር ከ12 ቀን በእስር ላይ የቆዩት፤ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የፓርላማ አባል ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ ዛሬ ከሰዓት መለቀቃቸውን የዓይን እማኞች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገለጹ። የቀድሞው የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አብዲ መሐመድ ዑመር (አብዲ ኢሌ)፣ የቀድሞው የብረታ ብረት እና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጄነራል ክንፈ ዳኘውም “በምህረት” ከእስር እንደሚፈቱ ታማኝ ምንጮች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።
ዶ/ር ደሳለኝ “በዋስትና እንደሚለቀቁ” የተነገራቸው፤ ዛሬ ምሳ ሰዓት ገደማ መሆኑን በስፍራው የነበሩ የዓይን እማኞች ገልጸዋል። የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የፓርላማ ተወካይ የሆኑት ዶ/ር ደሳለኝ፤ ጥር 22፤ 2016 ምሽት በጸጥታ ኃይሎች ከቤታቸው ከተወሰዱ በኋላ ታስረው የቆዩት በአዲስ አበባ ሜክሲኮ አደባባይ አካባቢ በሚገኘው የፌደራል የወንጀል ምርመራ የእስረኞች ማቆያ ስፍራ ነው።
ዶ/ር ደሳለኝ ከእስር ከመለቀቃቸው ከሰዓታት በፊት በተካሄደ የተወካዮች ምክር ቤት ስብሰባ፤ ከፓርላማው “የምክር ቤት ጉዳዮች አማካሪ ኮሚቴ” አባልነታቸው ተነስተዋል። ይህ ኮሚቴ “የተወካዮች ምክር ቤት የሚወያይበትን ማንኛውም አጀንዳ የመቅረጽ” ኃላፊነት ያለበት ሲሆን የሚመራው በፓርላማው አፈ ጉባኤ ነው። በዛሬው ስብሰባ፤ ላለፉት ሰባት ወራት በእስር ላይ ያሉት ሌላኛው የአብን የፓርላማ ተወካይ አቶ ክርስቲያን ታደለ ያለመከሰስ መብት መነሳቱ ይታወሳል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)