የቀድሞው የብረታ ብረት እና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ዋና ዳይሬክተር ሜጀር ጄነራል ክንፈ ዳኘው፤ ከአምስት ዓመት ከአራት ወር እስር በኋላ ዛሬ ከሰዓት ከእስር መፈታታቸውን ጠበቃቸው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናገሩ። ሜጀር ጄነራል ክንፈ የተፈቱት፤ በእርሳቸው ላይ ቀርበው የነበሩ ተደራራቢ ክሶች “ለህዝብ ጥቅም” ሲባል በትላንትናው ዕለት መቋረጣቸውን ተከትሎ ነው።
የቀድሞው የሜቴክ ዋና ዳይሬክተር ዛሬ አርብ መጋቢት 6፤ 2016 ከቀኑ 10 ሰዓት ገደማ የተለቀቁት፤ አብዛኛውን የእስር ጊዜያቸውን ካሳለፉበት ከቃሊቲ ማረሚያ ቤት መሆኑን ጠበቃቸው አቶ ሐፍቶም ከሰተ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። ሜጀር ጄነራል ክንፈ ከእስር ሲለቀቁ በቤተሰቦቻቸው አቀባበል እንደተደረገላቸውም አክለዋል።
ሜጀር ጄነራል ክንፈ በከባድ የሙስና ወንጀል ተጠርጥረው፤ በፌደራል ፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋሉት ህዳር 3፤ 2011 ዓ.ም. ነበር። የቀድሞው የሜቴክ ዋና ዳይሬክተር ከተያዙበት ትግራይ ክልል ወደ አዲስ አበባ በሄሊኮፕተር ተጓጉዘው ሲደርሱ፤ በብሔራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያ “በሰበር ዜና” እንዲሰራጭ ከተደረገ በኋላ ጉዳያቸው ከፍተኛ መነጋገሪያ ሆኖ መቆየቱ አይዘነጋም።
ተጠርጣሪው ሜቴክ በሚያስተዳድራቸው እና በሚሳተፍባቸው ፕሮጀክቶች ከተፈጸሙ 37 ቢሊዮን ብር ከሚያወጡ ግዢዎች ጋር በተያያዘ፤ ተደራራቢ የሙስና ወንጀል ክስ ቀርቦባቸው ጉዳያቸውን በፍርድ ቤት ሲከታተሉ ቆይተዋል። የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ በሜጀር ጄነራል ክንፈ ላይ ያቀረባቸው 13 ክሶች፤ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሲታዩ የቆዩት በስድስት መዝገቦች ነበር።
ከእነዚህ መዝገቦች ውስጥ ከራዳር ግዢ በተያያዘ በቀረበባቸው ክስ በፍርድ ቤት “ጥፋተኛ” የተባሉት ሜጀር ጄነራል ክንፈ፤ በሶስት ዓመት ከሰባት ወር እስራት እንዲቀጡ እንደተበየነባቸው ይታወሳል። የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ከትላንት በስቲያ ባስቻለው ችሎት፤ በቀድሞው የሜቴክ ዋና ዳይሬክተር ላይ በሌላ ክስ የጥፋተኝነት ፍርድ አስተላልፎባቸው ነበር። ሜጀር ጄነራል ክንፈ በረቡዕ ችሎት “ጥፋተኛ” የተባሉት፤ “ሪቬራ” እና “ኤምፔሪያል” የተባሉ ሁለት ሆቴሎችን ግዢ “ከህግ ወጪ ፈጽመዋል”፣ “ከፍተኛ ጉዳትም አድርሰዋል” በሚል ነው።
ሆኖም ይህ የጥፋተኝነት ውሳኔ በተላለፈ በማግስቱ፤ የፍትህ ሚኒስቴር በሜጀር ጄነራል ክንፈ እና የቀድሞው የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አብዲ መሐመድ ዑመር (አብዲ ኢሌ) ላይ ቀርበው የነበሩ ክሶች እንዲቋረጡ መወሰኑን አስታውቋል። በሁለቱ ተከሳሾች ላይ የቀረቡ ክሶች እንዲቋረጡ የተወሰነው “ለዘላቂ የህዝብ ጥቅም” ሲባል መሆኑን ሚኒስቴሩ ገልጿል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)