በሰለሞን በርሀ
በትግራይ ክልል ጦርነት ወቅት “ተማርከው ነበር” የተባሉ 112 የኢፌዲሪ መከላከያ ሰራዊት አባላት፤ በዛሬው ዕለት “በምህረት” መፈታታቸውን የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር አስታወቀ። በዛሬው ፍቺ ያልተካተቱ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ጉዳይም “በአጭር ጊዜ ውስጥ” መፍትሔ እንደሚያገኝም አስተዳደሩ ገልጿል።
የመከላከያ ሰራዊት አባላቱ፤ የፌደራል መንግስት እና የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) በጥቅምት 2015 ዓ.ም. በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ የግጭት ማቆም ስምምነት ከመፈራረማቸው በፊት የተማረኩ መሆናቸውን የትግራይ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት ዛሬ ምሽት ባወጣው መግለጫ ጠቅሷል። ከፕሪቶሪያው ስምምነት በኋላ ከ16 ሺህ በላይ የመከላከያ ሰራዊት አባላት መለቀቃቸውን ጽህፈት ቤቱ በመግለጫው አስታውሷል።
ዛሬ አርብ መጋቢት 13፤ 2016 የተለቀቁት የመከላከያ ሰራዊት አባላት፤ “በከባድ ወንጀል” ተጠርጥረው “በቁጥጥር ስር የቆዩ” መሆናቸውን ጽህፈት ቤቱ አመልክቷል። የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ለእነዚህ የሰራዊት አባላት “ምህረት” ያደረገው፤ የፕሪቶሪያ ስምምነት አፈጻጸምን በተመለከተ ባለፈው ሳምንት በአዲስ አበባ በተደረገ ውይይት ላይ “በተደረሰው መግግባት” መሆኑንም አክሏል።
“ስትራቴጂካዊ ግምገማ” የሚል ስያሜ የተሰጠው ይህ ውይይት፤ የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት “ወሳኝ ሁኔታዎች” በተባሉት የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት፣ የትጥቅ መፍታት፣ ታጣቂዎች እንዲበተኑ ማድረግ እና ከህብረተሰቡ ጋር መልሶ ማዋሃድ እንዲሁም የመልሶ ግንባታ ላይ ትኩረቱን ያደረገ ነበር። በአፍሪካ ህብረት አማካኝነት በተካሄደው በዚህ ውይይት ላይ፤ የፌደራል መንግስት እና የህወሓት ተወካዮች፣ ሁለቱን ወገን ያሸማገሉ የቀድሞ የሀገራት መሪዎች እና ታዛቢዎች መገኘታቸው አይዘነጋም።
በዚህ ውይይት “ስትራቴጂካዊ ግምገማ” ላይ “የተቀመጡ አቅጣጫዎችን” ተከትሎ እንደተፈጸመ በተነገረለት፤ በዛሬው “ምህረት” ያልተካተቱ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ብዛት “በቁጥር ትንሽ” መሆናቸውን የትግራይ ክልል የኮሙዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት በመግለጫው ጠቁሟል። የእነዚህ የሰራዊት አባላት ጉዳይም “በአጭር ጊዜ ውስጥ” መፍትሔ እንደሚያገኝ ጽህፈቱ ቤቱ አስታውቋል።
በትግራይ ጦርነት ወቅት በፌደራል መንግስት የታሰሩ የትግራይ ተወላጅ የመከላከያ ሰራዊት አባላትን “የመፍታት ሂደት” ተጠናክሮ እንዲቀጥል የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ጥሪ አቅርቧል። ከእነዚህ እስረኞች ውስጥ የተወሰኑት ፍርድ ያገኙ ሲሆን እና ቀሪዎቹ እስካሁንም የፍርድ ሂደታቸው ያልተጠናቀቀ መሆኑን በመግለጫው ላይ ተመልክቷል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)