የአቶ ታዬ ደንደአ ምርመራ ተጠናቅቆ ለጠቅላይ ዐቃቤ ህግ መላኩን ፖሊስ ለፍርድ ቤት አስታወቀ 

በተስፋለም ወልደየስ

ከሶስት ወራት በፊት ከሰላም ሚኒስትር ዴኤታነታቸው ከተነሱ በኋላ በቁጥጥር ስር በዋሉት አቶ ታዬ ደንደአ ላይ የጀመረውን ምርመራ አጠናቅቆ ለፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ መላኩን የፌደራል ፖሊስ አስታወቀ። ፖሊስ ይህን ያስታወቀው፤ የአቶ ታዬን “አካልን ነጻ የማውጣት”  አቤቱታ እየተመለከተ ለሚገኘው የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በሰጠው ምላሽ ነው።

የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት  ጉዳዩን መመልከት የጀመረው፤ በአቶ ታዬ ጠበቃ በኩል የቀረበውን አቤቱታ ባለፈው ሰኞ መጋቢት 9፤ 2016 ከተቀበለ በኋላ ነው። “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የተመለከተችው በሶስት ገጾች የተዘጋጀው አቤቱታ፤ የፌደራል ፖሊስ የአቶ ታዬን “በነጻነት የመዘዋወር ሕገ መንግስታዊ መብት በመጣስ”፣ “ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ”፣ “ህገወጥ በሆነ መንገድ” ያሰራቸው መሆኑን የሚያትት ነው። 

ለፍርድ ቤቱ የቀረበው አቤቱታ፤ የኢፌዲሪ ህገ መንግስት “ማንኛውም ሰው በህግ ከተደነገገው ስርዓት ውጭ ሊያዝ፣ ክስ ሳይቀርብበት ወይም ሳይፈርድበት ሊታሰር እንደማይችል” መደነገጉን ይጠቅሳል። በወንጀል ተጠርጥሮ የተያዘም ሰው ቢሆን፤ በህገ መንግስቱ መሰረት በ48 ሰዓት ውስጥ ፍርድ ቤት ሊቀርብ እንደሚገባም አቤቱታው አስታውሷል። 

“ፖሊስ በ48 ሰዓት ውስጥ ወደ ፍርድ ቤት ካላቀረበ ደግሞ ፍርድ ቤቱ የአካል ነጻነታቸውን እንዲያስከብርላቸው የመጠየቅ”፣ “ሊጣስ የማይችል መብት” እንዳላቸው በህገ መንግስቱ ላይ መቀመጡን አቤቱታው አመልክቷል። ኢትዮጵያ ባጸደቀችው ዓለም አቀፍ የሲቪል እና የፖለቲካ መብቶች ድንጋጌ፤ ማንኛውም ሰው “የነጻነት እና የደህንነት መብት እንዳለው” እና “በዘፈቀደ መታሰር እንደሌለበት” የሚያወሱ አንቀጾች ተካትተው እንደሚገኙም በአቤቱታው ላይ ሰፍሯል።

ይኸው ድንጋጌ“ ማንም ሰው በህግ እና በታወቀ የህግ ስነ ስርዓት ካልሆነ በስተቀር ነጻነቱን ማጣት እንደሌለበት” እንዲሁም በወንጀል ተጠርጥሮ በተያዘ ጊዜ “ወዲያውኑ ዳኛ ፊት መቅረብ እንዳለበት” መደነገጉም በአቤቱታው ላይ ተነስቷል። ከዚህም በተጨማሪ አቶ ታዬ በተያዙበት ወቅት የኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት (ጨፌ ኦሮሚያ) እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባል በመሆናቸው፤ በኢፌዲሪ እና በክልሉ ህገ መንግስቶች መሰረት ያለ ምክር ቤቶቹ ፍቃድ “ሊያዙም ሆነ ሊከሰሱ እንደማይገባ” በአቤቱታው ተመላክቷል።    

ሆኖም የፌደራል ፖሊስ እነዚህን ህገ መንግስታዊ እና ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎች “በግልጽ በመጣስ”፤ ከታህሳስ 1፤ 2016 ጀምሮ አቶ ታዬን በወንጀል ምርመራ ቢሮ አስሮ እንደሚገኝ አቤቱታው አብራርቷል። የፌደራል ፖሊስ አቶ ታዬን ያሰረው “ያለ አንዳች የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ወይም ውሳኔ” “በህገ ወጥ መንገድ” መሆኑን አክሏል። የቀድሞው ሚኒስትር ዴኤታ “እስካሁን ፍርድ ቤት አለመቅረባቸውን” እና “ምንም አይነት ክስ” እንዳልተመሰረተባቸውም አቤቱታው አጽንኦት ሰጥቷል።

አቶ ታዬ በጠበቃቸው በኩል ባቀረቡት በዚህ አቤቱታ ማገባደጃ ላይ፤ የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት፤ ልደታ ምድብ፤ ስምንተኛ የፍትሐብሔር ችሎት ጉዳያቸውን ተመልክቶ ዳኝነት እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል። በዚህም መሰረት የፌደራል ፖሊስ “ወደ ፍርድ ቤት እንዲያቀርባቸው” እንዲደረግ እና ፍርድ ቤቱም አቶ ታዬ “የታሰሩበትን ምክንያት በማጣራት የአመልካችን አካል ነጻ እንዲያወጣቸው” በአቤቱታው ጥያቄ ቀርቧል። አመልካች በ“አፋጣኝ ከህገ ወጡ እስራት እንዲለቀቁ”፤ የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ለፌደራል ፖሊስ “ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸውም” በአቤቱታቸው አመልክተዋል።

ጉዳዩ በጹሁፍ የቀረበለት የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት፤ የፌደራል ፖሊስ “ምላሹን ከእነ ማስረጃው” “በጹሁፍ እና በሶፍት ኮፒ” ለዛሬ አርብ መጋቢት 13፤ 2016 እንዲያቀርብ ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር። በትዕዛዙ መሰረትም፤ የፌደራል ፖሊስ የተደራጁ እና የሽብር ወንጀሎች መምሪያ ምላሹን ለፍርድ ቤቱ በጹሁፍ አቅርቧል። “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የተመለከተችው የፖሊስ ምላሽ፤ አቶ ታዬ ፍርድ ቤት ያልቀረቡት “በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መሰረት” የታሰሩ በመሆናቸው እንደሆነ ገልጿል።

በዋነኛነት በአማራ ክልል እና እንዳስፈላጊነቱ ደግሞ “በየትኛውም የኢትዮጵያ አካባቢ” ተፈጻሚነት የሚኖረው የአስቸኳይ ጊዜ በይፋ የታወጀው ባለፈው ዓመት ነሐሴ 2015 ዓ.ም. ነበር። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ፤ ይህንኑ ለማስፈጸም ለተቋቋመው ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ “የጠረጠራቸውን ማናቸውንም ሰው ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ በቁጥጥር ስር በማድረግ ለማቆየት” ስልጣን ሰጥቶታል። 

ጠቅላይ መምሪያ ዕዙ ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ በቁጥጥር ስር ለማድረግ በአዋጅ ከተፈቀደለት ውስጥ፤ “በሀገረ መንግስቱ እና በህገመንግስታዊ ስርዓቱ ላይ የሚቃጡ ወንጀሎችን” “መፈጸሙ፣ መምከሩ ወይም ለመፈጸም በዝግጅት ላይ መሆኑ የተጠረጠረ ሰው” የሚለው ይገኝበታል። “የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የመጣስ እና አፈጻጸሙን የማደናቀፍ ወንጀልን መፈጸሙ፣ መምከሩ ወይም ለመፈፀም በዝግጅት ላይ መሆኑ የተጠረጠረ ማናቸውም ሰው” በተመሳሳይ መልኩ በዕዙ አማካኝነት በቁጥጥር ስር ሊቆይ እንደሚችል በአዋጁ ላይ ሰፍሯል። 

የፌደራል ፖሊስ ለፍርድ ቤት ባቀረበው ምላሽ፤ አቶ ታዬ የተጠረጠሩበት “የወንጀል ድርጊት” ካጣራ በኋላ የምርመራ መዝገባቸውን ለሚመለከተው አካል መላኩን አስታውቋል። አመልካች ለፍርድ ቤት ላቀረቡት አቤቱታ፤ የምርመራ መዝገቡን በተረከበው የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ በኩል “ምላሽ እንዲሰጥበት” እንዲደረግ የፌደራል ፖሊስ በምላሹ ጠይቋል። የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የግራ ቀኙን ክርክር በቃል ለመስማት ለመጪው ማክሰኞ መጋቢት 17፤ 2016 ቀጠሮ ሰጥቷል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)