ከግማሽ በላይ ኢትዮጵያዊን በድህነት ውስጥ እንደሚኖሩ አንድ የዳሰሳ ጥናት አመለከተ  

በናሆም አየለ

ከኢትዮጵያ ህዝብ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት በድህነት ውስጥ እንደሚኖሩ በጥናት ማረጋገጡን “አፍሮ ባሮ ሜትር” የተሰኘው አፍሪካ አቀፍ የጥናት እና ምርምር ተቋም አስታወቀ። ከግማሽ በላይ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን፤ ለመኖር የሚያስፈልጋችውን መሰረታዊ ነገሮች ለማግኘት እንደሚቸገሩም ተቋም ያደረገው የዳሰሳ ጥናት አመልክቷል። 

በዲሞክራሲ፣ በመንግስት አስተዳደር፣ በኢኮኖሚ እና በማህበራዊ ጉዳዮች ላይ የህዝብን አመለካከት ለመለካት የዳሰሳ ጥናት የሚያደርገው “አፍሮ ባሮ ሜትር”፤ በኢትዮጵያ ተመሳሳዩን ጥናት ያከናወነው ባለፈው ዓመት ግንቦት እና ሰኔ ወራት እንደሆነ ገልጿል። በኢትዮጵያ ለሁለተኛ ጊዜ በተካሄደው በዚህ የዳሰሳ ጥናት፤ 2,400 ገደማ ኢትዮጵያውያን ተሳትፈዋል ተብሏል። 

ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች የተዳሰሱበት የዚህ ጥናት ውጤት ዛሬ ረቡዕ መጋቢት 18፤ 2016 በአዲስ አበባው ኢትዮጵያ ሆቴል ይፋ ተደርጓል። በጥናቱ መሰረት ብዙሃኑ ኢትዮጵያውያን፤ የሀገሪቱ የኢኮኖሚ ሁኔታ “መጥፎ ነው” የሚል አመለካከት አላቸው። 

ተቋሙ የዛሬ አራት ዓመት ባደረገው ተመሳሳይ የዳሰሳ ጥናት፤ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ “በመጠኑ መጥፎ ነው” እና “በጣም መጥፎ ነው” ሲሉ የገለጹ ዜጎች መጠን 44 በመቶ ነበር። በአሁኑ ጥናት ይህ አሃዝ ወደ 65 በመቶ አሻቅቧል። በአንጻሩ በኑሮ ሁኔታቸው እርካታ ያላቸው ዜጎች መጠን በፈረንጆቹ 2020 ዓመት ከነበረው 51 በመቶ ወደ 38 በመቶ አሽቆልቁሏል።

በኢትዮጵያ “የአፍሮ ባሮ ሜትር” ተወካይ የሆኑት አቶ ሙሉ ተካ፤ በጥናቱ ከተሳተፉ ኢትዮጵያውያን መካከል 47 በመቶዎቹ “የግል የኑሮ ሁኔታቸው መልካም አለመሆኑን” መግለጻቸውን ጠቅሰዋል። በዚሁ የዳሰሳ ጥናት፤ 18 በመቶ የሚሆኑት ኢትዮጵያውያን “በቂ ምግብ እንደማያገኙ” መረጋገጡንም አክለዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)