ባለፈው ሳምንት ከብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ኃላፊነታቸው “በገዛ ፍቃዳቸው” እንደለቀቁ የተነገረላቸው አምባሳደር ተሾመ ቶጋ፤ የዓለም አቀፉ የቀርክሀ ድርጅትን በዋና ዳይሬክተርነት እንዲመሩ ተሾሙ። አምባሳደር ተሾመ ዋና ጽህፈት ቤቱን በቻይና ያደረገውን ተቋም ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ መምራት እንደሚጀምሩ ድርጅቱ አስታውቋል።
“ኢንተርናሽናል ባምቦ ኤንድ ራታን ኦርጋንያዜሽን” የሚል ስያሜ ያለው ይህ ዓለም አቀፍ ድርጅት፤ ቀርክሀ እና ራታን የተባለን የተክል ዝርያ በመጠቀም ዘላቂ ልማት እንዲመጣ የሚያበረታታ ተቋም ነው። ከ27 ዓመታት በፊት የተመሰረተው ድርጅቱ፤ ኢትዮጵያ፣ ኤርትራ እና ኬንያን ጨምሮ 50 አባል ሀገራት አሉት።
ራሱን “የበይነ-መንግስታት የልማት ድርጅት” ብሎ የሚጠራው ይህ ተቋም፤ በቻይና ከሚገኘው ዋና ጽህፈት ቤቱ በተጨማሪ በኢትዮጵያ፣ በካሜሩን፣ በጋና፣ በህንድ እና ኤኳዶር አምስት ቀጠናዊ ቢሮዎች አሉት። በኢህአዴግ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ የነበሩት አቶ ተሾመ ዓለም አቀፍ ድርጅቱን የመምራት ኃላፊነት የሚረከቡት፤ ላለፉት አምስት ዓመታት በዋና ዳይሬክተርነት ካገለገሉት ታንዛኒያዊው አሊ ምቹሞ ነው።
ከአባላቱ መካከል ሃያ ሁለቱ ከአፍሪካ አህጉር የሆኑት የዚህ ዓለም አቀፍ ተቋም ምክር ቤት፤ የአምባሳደር ተሾመን ሹመት ማጽደቁን ድርጅቱ ዛሬ ሐሙስ መጋቢት 19፤ 2016 ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። አዲሱ ተሿሚ ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ አምባሳደርነት ወዳገለገሉበት ቻይና ዳግም ከመመለሳቸው በፊት፤ በብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን የነበራቸውን ኃላፊነት ከሁለት ቀናት በፊት በይፋ አስረክበዋል።
የቀድሞው ዲፕሎማት የቀድሞ ተዋጊዎችን ወደ ማህበረሰቡ በዘላቂነት እንዲቀላቀሉ እና ሰላማዊ ኑሮ መምራት እንዲችሉ እንዲያደርግ” የተቋቋመውን ኮሚሽን ላለፉት አስር ወራት መርተውታል። ኮሚሽኑ በህዳር 2015 የተቋቋመው፤ የኢትዮጵያ መንግስት እና ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ግጭት የማቆም ስምምነት በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ከተማ በተፈራረሙ በጥቂት ቀናት ልዩነት ነው።
አምባሳደር ተሾመ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ሹመት ካገኙ በኋላ ሲመሩት የቆዩት ብሔራዊ የተሃድሶ ኮሚሽን፤ ከ371 ሺሕ በላይ የቀድሞ ተዋጊዎችን በመበተን ወደ መደበኛ ሕይወት የመመለስ ኃላፊነት የተጣለበት ነው። የኮሚሽኑ ስራ በስምንት ክልሎች እንደሚከናወን ቢገለጽም፤ ከፍተኛ ትኩረት የተሰጣቸው ግን የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ያዳረሳቸው የትግራይ፣ አፋር እና አማራ ክልሎች ናቸው።
በፕሪቶሪያው ግጭት የማቆም ስምምነት አንዱ ቁልፍ ጉዳይ የሆነውን የቀድሞ ተዋጊዎችን ትጥቅ አስፈትቶ፣ በመበተን ወደ ማህበረሰቡ የማዋሃድ ስራ፤ አሜሪካ እና የአውሮፓ ህብረትን ጨምሮ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለመደገፍ ቃል ገብቶ ነበር። ሆኖም የኮሚሽኑ ስራ ሳይጠናቀቅ አምባሳደር ተሾመ እና ምክትላቸው ዶ/ር አትንኩት መዝገበ ከኃላፊነታቸው መሰናበታቸው ተገልጿል።
“በግል ጉዳያቸው ምክንያት” ከኃላፊነታቸው ለቀቁ በተባሉት አምባሳደር ተሾመ ምትክ፤ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የውጭ ፖሊሲ አማካሪ ሆነው በመስራት ላይ የነበሩት ተመስገን ጥላሁን መሾማቸውን ኮሚሽኑ መጋቢት 12፤ 2016 ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። አቶ ተመስገን ወደ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት በአማካሪነት ከመዛወራቸው አስቀድሞ፤ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ምክትል ኮሚሽነር ሆነው ከአምስት ዓመታት በላይ ሰርተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)