በናሆም አየለ
በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ከሚገኙ ባለ ኮከብ ሆቴሎች መካከል አምስቱ “ከደረጃ በታች” ሲሰሩ መገኘታቸውን የቱሪዝም ሚኒስቴር አስታወቀ። በመዲናይቱ ካሉ ሆቴሎች ውስጥ አስራ አምስቱ፤ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱን “አስገዳጅ መስፈርቶች” ሳያሟሉ በስራ ላይ ያሉ መሆናቸው መረጋገጡንም ገልጿል።
በሚኒስቴሩ የቱሪስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት የብቃት ማረጋገጥ እና ደረጃ ምደባ መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ ታሪኩ ደምሴ፤ ሆቴሎቹ “ከደረጃ በታች” እንደሚሰሩ የተደረሰባቸው መስሪያ ቤታቸው ባደረገው “ድንገተኛ የክትትል እና የቁጥጥር ስራ” መሆኑን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። እነዚህ ሆቴሎች “በሚቀመጥላቸው የጊዜ ገደብ አገልግሎታቸውን እንዲያስተካክሉ”፤ በቅርቡ ማስጠንቀቂያ እንደሚደርሳቸውም አመልክተዋል።
ሆቴሎቹ በተባለው መልኩ አገልግሎታቸውን የማያስተካክሉ ከሆነ፤ የቱሪዝም ሚኒስቴር ከዚህ ቀደም የሰጣቸውን የኮከብ ደረጃ “እንደሚቀማ” አቶ ታሪኩ ጠቁመዋል። ከሚኒስቴሩ በተገኘው መረጃ መሰረት፤ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በአሁኑ ወቅት የኮኮብ ደረጃ የተሰጣቸው ሆቴሎች ብዛት 142 ነው።
እነዚህ ሆቴሎች የኮከብ ደረጃቸውን አስጠብቀው ለመዝለቅ፤ የቱሪዝም ሚኒስቴር የሚያስቀምጠውን “አስገዳጅ መስፈርቶች” ማሟላት ይጠበቅባቸዋል። የሆቴሎቹ የንጽህና አጠባበቅ እና የእሳት አደጋ የመከላከል አቅም፤ ከአስገዳጅ መስፈርቶቹ መካከል የሚጠቀሱ ናቸው። የቱሪዝም ሚኒስቴር በቅርቡ ባካሄደው “ድንገተኛ ክትትል”፤ ከተሰጣቸው ደረጃ በታች ሲሰሩ የተገኙ ሆቴሎች “ከፍተኛ የሆነ የንጽህና ችግር እንዳለባቸው” ማረጋገጡን አቶ ታሪኩ አስረድተዋል።
ሆቴሎቹ የእሳት አደጋን የመከላከል አቅማቸውን የሚያሳይ ማረጋገጫ ከአዲስ አበባ ከተማ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን መውሰድ ሲገባቸው፤ ይህንኑ ሳያደርጉ መገኘታቸውን ስራ አስፈጻሚው አስታውቀዋል። የቱሪዝም ሚኒስቴር በተወሰኑ ባለ ኮከብ ሆቴሎች ላይ የተስተዋሉ እነዚህን መሳይ ችግሮች ለመቅረፍ ከሚያደርገው ጥረት ጎን ለጎን፤ አዳዲስ የኮከብ ደረጃ ጥያቄ ላቀረቡ 64 ሆቴሎች እውቅና ለመስጠት የሚያስችለውን ምዝናዎች ሲያካሄድ መቆየቱን አቶ ታሪኩ አክለዋል።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የዚሁ ስራው አካል የሆነውን እውቅና የመስጠት መርሃ ግብር ዛሬ ሐሙስ መጋቢት 19፤ 2016 በአዲስ አበባው ስካይ ላይት ሆቴል አካሄዷል። በመርሃ ግብሩም “ለሆቴሎች የኮከብ ደረጃ ለመስጠት የተቀመጠውን መስፈርት አሟልተው ተገኝተዋል” ለተባሉ 31 ሆቴሎች አዲስ የኮከብ ደረጃዎች ተሰጥቷቸዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)