በተስፋለም ወልደየስ
በሽብር ወንጀል ተጠርጥረው ከትላንት በስቲያ ክስ የተመሰረተባቸው የፓርላማ አባሉ አቶ ክርስቲያን ታደለ እና የአማራ ክልል ምክር ቤት አባሉ አቶ ዮሃንስ ቧያለው በዛሬው ዕለት ፍርድ ቤት ቀረቡ። ሁለቱን የህዝብ ተወካዮች ጨምሮ በተመሳሳይ መዝገብ የተከሰሱ 14 ተጠርጣሪዎች፤ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የህገ መንግስት እና ሽብር ወንጀል ጉዳዮች ችሎት ፊት ቀርበው የክስ መዝገባቸውን ተቀብለዋል።
ጋዜጠኞች እና የተከሳሾች ቤተሰብ አባላት እንዲከታተሉት ባልተፈቀደላቸው የዛሬው የችሎት ውሎ አንድ ሰዓት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የተጠናቀቀ ነበር። ፍርድ ቤቱ የተከሳሾችን ማንነት እና አድራሻ መዝግቦ እንዳጠናቀቀ፤ በፍትህ ሚኒስቴር አማካኝነት የቀረበባቸው ክስ በአካል ችሎት ለተገኙ ተጠርጣሪዎች ለእያንዳንዳቸው እንዲደርስ ተደርጓል።
በፌደራል ዐቃቤ ህግ በተመሰረተው ክስ ከተዘረዘሩ 52 ተጠርጣሪዎች ውስጥ፤ ሰላሳ ስምንቱ በዛሬው ችሎት አልተገኙም። ጉዳያቸው በሌለበት ከሚታየው ተከሳሾች ውስጥ እስክንድር ነጋ እና ዘመነ ካሴ ይገኙበታል። ችሎቱ የዛሬውን ውሎውን ከመቀጠሉ በፊት፤ በአካል የቀረቡትን ተከሳሾች የወከሉት ጠበቃ ሰለሞን ገዛኸኝ ከደንበኞቻቸው ጋር የመመካከሪያ ጊዜ ጠይቀው ተፈቅዶላቸዋል።
የችሎቱ ሂደት ከአፍታ ቆይታ በኋላ ሲቀጥል፤ ዐቃቤ ህግ ተከሳሾቹ አሁን ያሉበት የፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ የእስረኞች ማቆያ ጠባብ እና ለረጅም ጊዜ ይዞ ለማቆየት አመቺ ባለመሆኑ ወደ ማረሚያ ቤት እንዲዛወሩ ጥያቄ አቅርቧል። ይህንን የዐቃቤ ህግ ጥያቄ “ተገቢ” እና “ስነ ስርዓታዊ” አለመሆኑን በመጥቀስ፤ የተከሳሽ ጠበቃ ተቃውሞ አሰምተዋል።
“ተከሳሾች ወደ ማረሚያ ቤት መዛወራቸውን በሚመለከት ትዕዛዝ ሊሰጥ የሚገባው ፍርድ ቤት እንጂ ዐቃቤ ህግ አይደለም። ተከሳሾቹ ወደ ማረሚያ ቤት ይዛወሩ ከተባለም፤ በአቆያየታቸው እና በዋስትና ጥያቄያቸው ላይ ክርክር ከተሰማ በኋላ መሆን ይኖርበታል። ስለዚህ ጥያቄው ወቅቱን የጠበቀ አይደለም ብለን ለችሎት አመልክተናል” ሲሉ ጠበቃ ሰለሞን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ይሄ መከራከሪያቸው በችሎቱ ተቀባይነት ማግኘቱንም አክለዋል።
በዛሬው የፍርድ ቤት ውሎ የተነሳው ሌላው ጉዳይ፤ በተከሳሾች በኩል የተነሳው “የመብት ጥሰት እና ጉድለት” ጥያቄ ነው። ተከሳሾቹ ይህንኑ ለችሎቱ ማቅረብ እንዲችሉ እንዲፈቅድላቸው መጠየቃቸውን አቶ ሰለሞን አስረድተዋል። ተከሳሾች ህክምና የማግኘት እና መሰል ጥያቄዎች ካሏቸው፤ ከዚህ ቀደምም እንደሚደረገው አቤቱታቸውን በጠበቃቸው በኩል በጹሁፍ እንዲያስገቡ በችሎቱ ዳኞች እንደተነገራቸው ጠበቃው ተናግረዋል።
ሆኖም ተከሳሾቹ “ጊዜ የማይሰጣቸው” “አሳሳቢ” የመብት ጥሰት እንደገጠማቸው በመጥቀስ ለችሎቱ በድጋሚ ጥያቄ በማቅረባቸው፤ ችሎቱ ለአቶ ዮሃንስ ቧያለው የመናገር ዕድል እንደተሰጣቸው አቶ ሰለሞን ገልጸዋል። አቶ ዮሃንስ ለችሎቱ በቃል ባቀረቡት አቤቱታ፤ በፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ ታስረው የሚገኙት “በጨለማ ቤት” መሆኑን መናገራቸውን ጠበቃቸው ጠቅሰዋል። ከዚህም በተጨማሪ ተከሳሾቹ በታሰሩበት ክፍል ተቆልፎባቸው ስለሚቀመጡ፤ መንቀሳቀስ እንደማይችሉ አቶ ዮሃንስ ለፍርድ ቤቱ ተናግረዋል ብለዋል።
ህክምናን በተመለከተ ተከሳሾቹ በፌደራል ፖሊስ ሆስፒታል ላይ “ጥርጣሬ” ስላላቸው፤ በግል የህክምና ተቋማት ለመታከም ቢጠይቁም እንዳልተፈቀደላቸው ለችሎቱ ማስረዳታቸውን ጠበቃው ገልጸዋል። ለአስራ አራቱ ተከሳሾች የቤተሰብ ጥያቄ የተፈቀደው ጊዜ 10 ደቂቃ በመሆኑ፤ ቤተሰቦቻቸውን በአግባቡ ማግኘት አለመቻላቸውን አቶ ዮሃንስ ለችሎቱ መናገራቸውን ጠበቃው አመልክተዋል። ተከሳሾቹ ጠበቆቻቸውንም ሆነ የሃይማኖት አባቶቻቸውን እንዳያገኙ መደረጋቸውም በአቤቱታው ላይ ተነስቷል ተብሏል።
አቤቱታውን ያደመጠው ፍርድ ቤቱ፤ ከፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ የመጡ ኮማንደርን ችሎት ፊት በማቅረብ በተነሱት የመብት ጥሰቶች ላይ ምላሽ እንዲሰጡ አድርጓል። ኮማንደሩ በምርመራ ቢሮው ውስጥ “ጨለማ ቤት የለም” ሲሉ ማስተባበላቸውን እንደዚሁም ተጠርጣሪዎቹ ጠበቃ እና ሌሎች ጎብኚዎች እንዳያገኟቸው ያደረገው “ኮማንድ ፖስት” መሆኑን መናገራቸውን አቶ ሰለሞን ጠቅሰዋል።
የፖሊስን ምላሽ ያደመጠው ፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የህገ መንግስት እና ሽብር ወንጀል ጉዳዮች ችሎት፤ ተከሳሾቹ “ከዛሬ ጀምሮ እንደ መደበኛ እስረኛ እንዲታዩ” እና “ማንኛውም እስረኛ የሚያገኟቸው መብቶች እንዲያገኙ” ትዕዛዝ መስጠቱን ጠበቃ ሰለሞን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ፍርድ ቤቱ የዛሬውን የችሎት ውሎውን ያጠናቀቀው ለሚቀጥለው ሳምንት አርብ መጋቢት 27፤ 2016 ቀጠሮ በመስጠት ነው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
[በዚህ ዘገባ ላይ ከቆይታ በኋላ ተጨማሪ መረጃ ታክሎበታል]