በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የተሾሙት አቶ አደም ፋራህ የፓርቲ ስልጣናቸውን ይዘው ይቆያሉ ተባለ

ገዢው የብልጽግና ፓርቲ ካሉት ሁለት ምክትል ፕሬዝዳንቶች አንዱ የሆኑት አቶ አደም ፋራህ፤ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዲሞክራሲ ስርዓት ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ ሆነው ተሾሙ። ለአቶ አደም ዛሬ ሰኞ መጋቢት 23፤ 2016 ሹመቱን የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ መሆናቸውን ጽህፈት ቤታቸው አስታውቋል።

የቀድሞው የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት እንዲሆኑ የተመረጡት፤ በመጋቢት 2014 በተካሄደው የፓርቲው አንደኛ ጠቅላላላ ጉባኤ ላይ ነው። በወቅቱ የገዢው ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት እንዲሆኑ ከተጠቆሙት ሶስት አባላት ውስጥ አቶ አደም 1,330 ድምጽ በማግኘት በከፍተኛ ድምጽ መመረጣቸው ይታወሳል። 

በዚያ ጉባኤ ከተሳተፉ 1,564 አባላት መካከል የ970ዎቹን ድምጽ በማግኘት ሁለተኛ ደረጃ ያገኙት፤ ባለፈው ጥር ወር ከፓርቲው ኃላፊነታቸው የተሰናበቱት አቶ ደመቀ መኮንን ነበሩ። በመጋቢት 2014ቱ ስብሰባ ሶስተኛ ሆነው ያጠናቀቁት አቶ ተመስገን ጥሩነህ፤ ከሁለት ወር በፊት በተካሄደው የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ አቶ ደመቀን በመተካት የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት ሆነዋል። 

አቶ ተመስገን ይህን ኃላፊነት ከተረከቡ ከቀናት በኋላ፤ አቶ ደመቀ ለበርካታ ዓመታት ይዘውት በቆዩት የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርነት ስልጣን ተሹመዋል። ሌላኛው የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አደም፤ በዚህ የኃላፊነት ቦታ ከተመረጡበት ጊዜ አንስቶ የፓርቲውን ጽህፈት ቤት በበላይነት ሲመሩ መቆየታቸው አይዘነጋም።

አቶ አደም በዛሬው ዕለት የመንግስት ስልጣን ቢሰጣቸውም፤ በፓርቲው ውስጥ ያላቸውን ሹመት እንዳስጠበቁ እንደሚቀጥሉ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጭ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። አዲሱ ተሿሚ ከሶስት ዓመት ከመንፈቅ በፊት ወደ ፌደራል መንግስት ስልጣን ከመምጣታቸው አስቀድሞ፤ የሶማሌ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ በመሆን ሰርተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)