በሀገራዊ የምክክር ሂደት ላይ በአጀንዳ ግብዓት ማሰባሰብ የሚሳተፉ ተወካዮች መረጣ በ850 ወረዳዎች መጠናቀቁ ተገለጸ 

በናሆም አየለ

በኢትዮጵያ ካሉ 1,300 ወረዳዎች መካከል በ850ዎቹ የምክክር አጀንዳዎች የሚለዩ ተወካዮች ምርጫ መጠናቀቁን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስታወቀ። ኮሚሽኑ “ባጠሩ ሳምንታት” ውስጥ አጀንዳ የማሰባሰብ ስራውን ሊጀምር በመሆኑ፤ የወረዳ እንዲሁም የክልል ተወካዮች ከወከላቸው የማህበረሰብ ክፍል ጋር ውይይት እንዲጀምሩ ጥሪ አቅርቧል። 

የኮሚሽኑ ቃል አቀባይ አቶ ጥበቡ ታደሰ ዛሬ አርብ መጋቢት 27፤ 2016 በኮሚሽኑ በዋና ጽህፈት ቤት በሰጡት መግለጫ እንዳሉት፤ የተወካዮች መረጣ ሙሉ ለሙሉ ተጠናቀቀባቸው ክልሎች አፋር፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ጋምቤላ፣ ድሬዳዋ፣ ሀረሪ፣ ሲዳማ፣ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ እና ደቡብ ኢትዮጵያ ናቸው። በአዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮችም በተመሳሳይ መልኩ ተወካዮች የማስመረጡ ተግባር መገባደዱን ገልጸዋል።

በእነዚህ ሂደቶች የተመረጡ ከ14 ሺህ በላይ ተወካዮች፤ በቀጣይ በየክልሎቹ እና በሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች በሚካሄዱ ህዝባዊ መድረኮች ላይ “ህብረተሰባቸውን ወክለው” እንደሚሳተፉ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ጠቁሟል። በክልል ከተሞች ላይ የሚደረገው ምክክር አንዱ ክልል ተወያይቶ አጀንዳውን ሲጨርስ ሌላው ክልል ውይይት እንዲጀምር የሚደረግ ሳይሆን፤ በክልሎች እና ከተማ መስተዳድሮች የሚገኙ ተወካዮች በተመሳሳይ ወቅት የሚያከናወኑት እንደሚሆን የኮሚሽኑ ቃል አቃባይ ተናግረዋል።

የወረዳ ተወካዮችን ወደ ክልል ከተሞች በማምጣት የሚደረገው ውይይት፤ ከስምንት እስከ አስር ባሉት ቀናት ውስጥ ለመጨረስ መታቀዱንም አቶ ጥበቡ አስረድተዋል። የእነዚህ ውይይቶች ተሳታፊዎች የአጀንዳ ግብአት ከማሰባሰብ በተጨማሪ፤ በቀጣይ በሀገር አቀፍ ደረጃ በሚካሄደው ምክክር ላይ የሚሳተፉ ተወካዮችን እንዲለዩ እንደሚደረግ አመልክተዋል።

በአጀንዳ የማሰባሰብ መድረኮች ላይ ለመሳተፍ የተመረጡ ተወካዮች፤ ከወከላቸው ማህበረሰብ ግብዓቶችን ለማሰባሰብ አስፈላጊውን ዝግጅት እንዲያደርጉም ቃል አቀባዩ ጥሪ አቅርበዋል። ከግንቦት 2015 ዓም ጀምሮ በመካሄድ ላይ ባለው የተሳታፊዎች ልየታ እና ተወካዮችን የማስመረጥ ተግባር ላይ 130 ሺህ ዜጎች ተሳትፈዋል ተብሏል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር) 

[በዚህ ዘገባ ላይ ከቆይታ በኋላ ተጨማሪ መረጃዎች ታክለውበታል]