የኦነግ የፖለቲካ የፖለቲካ ኦፊሰር አቶ በቴ ኡርጌሳ ተገደሉ

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር አቶ በቴ ኡርጌሳ ትላንት ማክሰኞ ሚያዝያ 1፤ 2016 ምሽት መገደላቸውን ምንጮች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገለጹ። አቶ በቴ የተገደሉት በትውልድ ቦታቸው መቂ ከተማ እንደሆነ ምንጮች ተናግረዋል። 

የአራት ልጆች አባት የሆኑት አቶ በቴ መኖሪያቸው በአዲስ አበባ አቅራቢያ በሚገኘው ለገጣፎ ሲሆን፤ በዋነኛነት የሚተዳደሩበትን የግብርና ስራቸውን ሲያካሄዱ የቆዩት ግን በመቂ አካባቢ ነበር። በዚህም ምክንያት ወደ መቂ በተደጋጋሚ ይመላለሱ እንደነበር ለእርሳቸው ቅርበት ያላቸው ምንጮች ገልጸዋል። 

ትላንት ምሽት መገደላቸውን የተነገረው የአቶ በቴ አስክሬን የተገኘው፤ ከመቂ ወደ ባቱ ከተማ በሚወስደው መንገድ አቅራቢያ በሚገኝ “መሊሳ” በተባለ አካባቢ መሆኑን የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ምንጮች አመልክተዋል። የአቶ በቴ ቤተሰቦች በዛሬው ዕለት ሶስት ሰዓት ገደማ የሟችን አስክሬን ከአካባቢው መውሰዳቸውንም አክለዋል።

የኦነግ የፖለቲካ ኦፊሰሩ ከአንድ ወር በፊት “ሁከት እና በጥብጥ በማነሳሳት” ወንጀል ተጠርጥረው ለ16 ቀናት ያህል በእስር ላይ መቆየታቸው ይታወሳል። አቶ በቴ በአዲስ አበባ ስካይ ላይት ሆቴል ሲቪል በለበሱ የጸጥታ ኃይሎች ተይዘው በቁጥጥር ስር የዋሉት የካቲት 14፤ 2016 ነበር። ፖለቲከኛው በተያዙበት ወቅት፤ ከ“አፍሪካ ኢንተለጀንስ” የዜና ድረ ገጽ ዘጋቢ አንቷን ጋሊንዶ ጋር በውይይት ላይ እንደነበሩ ለፍርድ ቤት ተናግረው ነበር።

ከአቶ በቴ ጋር በቁጥጥር ስር ውሎ የነበረው ፈረንሳዊው ጋዜጠኛ አንቷን፤ ለአንድ ሳምንት ያህል በአዲስ አበባ ከታሰረ በኋላ ተለቅቆ ወደ ሀገሩ ፈረንሳይ መመለሱ አይዘነጋም። ጋዜጠኛው ከተለቀቀ በኋላ ተጨማሪ አምስት የምርመራ ቀናት ተፈቅዶባቸው በእስር ላይ የቆዩት አቶ በቴ፤ 100 ሺህ ብር በማስያዝ በዋስትና እንዲፈቱ በአዲስ አበባ ከተማ የመጀመሪያ ፍርድ ቤት የተወሰነላቸው የካቲት 27፤ 2016 ነበር።

ሆኖም ፖሊስ በውሳኔው ላይ ይግባኝ በማለቱ፤ የኦነጉ ፖለቲከኛ ለተጨማሪ ሁለት ቀናት በእስር ለማሳለፍ ተገድደዋል። የፖሊስን ይግባኝ የተመለከተው የአዲስ አበባ ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የታች ፍርድ ቤት ውሳኔን በማጽናቱ፤ አቶ በቴ የካቲት 30፤ 2016 ከእስር ተፈትተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)