የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች የአቶ በቴን ግድያ እንዲመረምሩ ኦነግ ጠየቀ

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) በፖለቲካ ኦፊሰሩ አቶ በቴ ኡርጌሳ ላይ የተፈጸመውን ግድያ በአፋጣኝ እንዲመረምሩ ለሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ጥያቄ አቀረበ። አቶ በቴ በመቂ ከተማ የተገደሉት በተተኮሰባቸው ጥይት መሆኑን ኦነግ ምንጮቹን ዋቢ አድርጎ ገልጿል። 

ኦነግ ዛሬ ረቡዕ ባወጣው መግለጫ፤ የአቶ በቴን ሞት “ጭካኔ የተሞላበት ግድያ” ሲል ጠርቶታል። ፓርቲው በፖለቲካ ኦፊሰሩ ላይ ግድያ መፈጸሙን ቢያረጋግጥም፤ የድርጊቱን ፈጻሚዎች በተመለከተ በመግለጫው ላይ ያለው ነገር የለም። ሆኖም ግድያውን በተመለከተ  ተጨማሪ ምርመራዎች እያደረገ መሆኑን ፓርቲው አስታውቋል።

ባለፉት አስርት ዓመታት፤ በኦሮሞ የፖለቲካ እና የባህል ታዋቂ ሰዎች ላይ “ከፍርድ ውጭ ግድያዎች ሲፈጸሙ” መቆየታቸውን በመግለጫው ያስታወሰው ኦነግ፤ ይህ “ስልታዊ” እና “ኃላፊነት የጎደለው” ተግባር ኦሮሞዎችን “ጸጥ ለማሰኘት” በማሰብ እንደሆነ ፓርቲው ወንጅሏል። በድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ላይ የተፈጸመው ግድያ ከኦሮሞ ህዝብ ትውስታ ሳይደበዝዝ፤ የበቴ ኡርጌሳን አሳዛኝ ሞት መረዳቱን ፓርቲው አመልክቷል። 

አቶ በቴን “አንደበት ርቱዕ”፣ “ለራሱ የማይሳሳ” እና “ደፋር” ሲል የገለጸው ኦነግ፤ ስለ ግድያው የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች “ገለልተኛ” እና “ከማንም ያልወገነ” ምርመራ በአፋጣኝ እንዲያደርጉ ጠይቋል። የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ ዛሬ እኩለ ቀን ገደማ በትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፤ በአቶ በቴ ግድያ ላይ “ፈጣን”፣ “አድልኦ የሌለበት” እና “ሙሉ” ምርመራ እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል። የፌደራል እና የኦሮሚያ ባለስልጣናትም የድርጊቱን ፈጻሚዎች ለህግ እንዲያቀርቡ አሳስበዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)