በአተት በሽታ ወረርሽኝ ሳቢያ ሳምንታዊው የባቲ ከተማ ገበያ ዝግ ሆኖ እንዲውል ተደረገ   

በናሆም አየለ

በአማራ ክልል፤ ኦሮሞ ብሔረሰብ ልዩ ዞን በምትገኘው ባቲ ወረዳ ስር ባሉ አካባቢዎች የአጣዳፊ ተቅማጥ እና ትውከት (አተት) ወረረሽኝ በመከሰቱ፤ ዘወትር ሰኞ በባቲ ከተማ የሚውለው ገበያ በዛሬው ዕለት እንዳይካሄድ ተደረገ። በወረዳው ባለፈው አንድ ሳምንት ብቻ 76 ሰዎች በወረርሽኙ መጠቃታቸው መረጋገጡን የአማራ ክልል የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስታውቋል። 

በባቲ ከተማ በየሳምንቱ የሚካሄደው “ትልቁ የሰኞ ገበያ”፤ ከወረዳው ነዋሪዎች በተጨማሪ ከደሴ፣ ኮምቦልቻ፣ ገርባ እና ደጋን ከተማ ጭምር የሚመጡ በሺህዎች የሚቆጠሩ ገበያተኞች ጭምር የሚገበያዩበት ነው። በወረዳው በሚገኙት ጨቆርቲ፣ ፉራ እና ቀርሣ በተባሉ ቀበሌዎች በተከሰተው የአተት ወረርሽኝ ምክንያት፤ የባቲ ከተማ አስተዳደር ዛሬ ሰኞ ሚያዝያ 7፤ 2016 የገበያ ክልከላ አድርጓል። 

የአተት ወረርሽኝ በባቲ ወረዳ ከመከሰቱ በፊት የሰኞ ገበያ በዚህ አይነት መልኩ የሚካሄድ ነበር | ፎቶ፦ ከኡሙ ጁሃር ቪድዮ የተወሰደ

በከተማ አስተዳደሩ የተቋቋመው ግብረ ኃይል፤ በከተማይቱ የሚገኙ የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች (ኬጂዎች) በዛሬው ዕለት ተዘግተው እንዲውሉም ውሳኔ አስተላልፏል። ግብረ ኃይሉ ከዚህም በተጨማሪ በየመንገዱ ላይ ተጠብሰው የሚሸጡ ምግቦችን እንዲሁም ሀብሀብ እና የተለያዩ ፍራፍሬዎችን በመንገድ ላይ ዘርግቶ መሸጥን ከልክሏል። “የቀርሣ ውሃ” እና “አውሳ በር” ከሚባለው አካባቢ በታች የሚገኙ ውሃዎችን ከመጠቀም እንዲቆጠቡም ለነዋሪዎች መልዕክቱን አስተላልፏል።

“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያነጋገረቻቸው አንድ የባቲ ከተማ ነዋሪ፤ የገበያ ክልከላው በዛሬው ዕለት ተግባራዊ ሆኖ መዋሉን አረጋግጠዋል። ክልከላውን ባለመስማት ወደ ገበያው የመጡ ነዋሪዎች፤ በአከባቢው ፖሊስ እና ሚሊሺያ አባላት ወደ መጡበት እንዲመለሱ መደረጋቸውንም እኚሁ የዓይን እማኝ ተናግረዋል። 

የባቲ ገበያ በዛሬው ዕለት እንዳይካሄድ የተደረገው የአተት ወረርሽኝ ተላላፊ ስለሆነ “ንክኪን ለመቀነስ” በማሰብ መሆኑን የአማራ ክልል የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር አቶ በላይ በዛብህ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስረድተዋል። የአተት ወረርሽኝ በባቲ ወረዳ በሚቀኙ ቀበሌዎች ላይ ከተከሰተ አንድ ሳምንት እንደሆነው የገለጹት ዳይሬክተሩ፤ እስከ ትላንት ድረስ 76 ሰዎች በወረርሽኙ መጠቃታቸውን እና አንድ ሰው በበሽታው መሞቱን መረጋገጡን አስታውቀዋል።

የአካባቢው ነዋሪው የበሰሉ ምግቦችን ብቻ እንዲጠቀም እንዲሁም ለመጠጥ አገልግሎት የሚጠቀመው የቧንቧ ውሃን ብቻ እንዲሆን መልዕክቶች እየተላለፉ መሆናቸውን ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል። ይህን መሰሉ የግንዛቤ ማስጨበጫ እና የቅስቀሳ ስራ፤ ወረረሽኙ በተከሰተባቸው  ጨቆርቲ እና ፉራ ቀበሌዎች በትላትናው ዕለት ሲካሄድ መዋሉን ከባቲ ወረዳ የመንግስት ኮምዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል። 

“በሽታውን በቁጥጥር ስር ለማዋል ያለመ ነው” የተባለለት የቅሰቀሳ ስራ በቀጣይ ቀናት በሌሎች የባቲ ወረዳ ቀበሌዎች እንደሚቀጥልም ጽህፈት ቤቱ አክሏል። በአማራ ክልል በአሁኑ ወቅት የአተት ወረርሽኝ የተከሰተው በባቲ ወረዳ ብቻ መሆኑን የክልሉ የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጿል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)