ለኢትዮጵያ ሰብአዊ እርዳታ የሚውል ከ600 ሚሊዮን ዶላር በላይ በለጋሾች ቃል ተገባ

በኢትዮጵያ ሰብአዊ እርዳታ ለማቅረብ ለጋሾች ከ630 ሚሊዮን ዶላር በላይ ለመስጠት ቃል መግባታቸውን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ታዬ አጽቀሥላሴ ገለጹ። ለጋሾቹ ይህን ቃል የገቡት፤ የኢትዮጵያ መንግስት፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) እና ዩናይትድ ኪንግደም ዛሬ ማክሰኞ ሚያዝያ 8፤ 2016 በጄኔቫ ባካሄዱት የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር ላይ ነው።

በዚሁ መርሃ ግብር ላይ ንግግር ያደረጉት አቶ ታዬ፤ የኢትዮጵያ መንግስት ዋነኛ ትኩረት “የዜጎች መተዳደሪያን  ከአደጋ መጠበቅ፣ የአደጋ ስጋትን ቅነሳን ከልማት እቅዶች ጋር መዋሃድ እንዲሁም የተጋላጭ ሰዎችን የመቋቋም አቅም ማጠናከር” መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል። ለጋሾች ለኢትዮጵያ ሰብአዊ እርዳታ ለማቅረብ ቃል የገቡት የገንዘብ መጠን ከ630 ሚሊዮን ዶላር በላይ መሆኑን አቶ ታዬ ቢገልጹም፤ ተመድ ቀደም ብሎ ባወጣው መግለጫ የተጠቀሰው አሃዝ ግን በ20 ሚሊዮን ዶላር ገደማ ዝቅ ያለ ነው። 

በመንግስታቱ ድርጅት መግለጫ መሰረት፤ ከፍተኛውን የገንዘብ መጠን ለመስጠት ቃል በመግባት ቀዳሚ የሆነችው አሜሪካ ነች። አሜሪካ 253 ሚሊዮን ዶላር ለኢትዮጵያ ሰብአዊ እርዳታ ለመስጠት ቃል መግባቷን የተባበሩት መንግስታት ይፋ ያደረገው ሰነድ ያሳያል። ዩናይትድ ስቴትስን በመከተል ከፍ ያለውን ቃል የገቡት ዩናይትድ ኪንግደም እና የአውሮፓ ህብረት ናቸው።

 ዩናይትድ ኪንግደም 125 ሚሊዮን ዶላር፣ የአውሮፓ ህብረት ደግሞ 46 ሚሊዮን ዶላር ለመስጠት ቃል ገብተዋል። “ይህ ጅማሮ ነው ብለን እንረዳለን” ያሉት በተመድ የሰብአዊ ጉዳዮች ረዳት ዋና ጸሀፊ ጆይስ ምሱያ፤ እገዛው “ዓመቱን ሙሉ” እንደሚቀጥል አስታውቀዋል። የሰብዓዊ እርዳታው “ይጨምራል ብለን ተስፋ እናደርጋለን” ሲሉም አክለዋል።

በዛሬው የጄኔቫ መርሃ ግብር ቃል የተገባው የገንዘብ መጠን፤ በኢትዮጵያ ሰብአዊ ርዳታ ለማቅረብ ከሚያስፈልገው እጅግ ያነሰ ነው። የመንግስታቱ ድርጅት በሚቀጥሉት ሶስት ወራት ብቻ ለኢትዮጵያ እርዳታ ለማቅረብ የሚያስፈልገው የገንዘብ መጠን አንድ ቢሊዮን ዶላር መሆኑን ማስታወቁ ይታወሳል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)