በአዲስ አበባ ከተማ ተቋርጦ የነበረው የመታወቂያ መስጠት እና እድሳት አገልግሎት በቀጣዩ ሳምንት ዳግም ይጀመራል ተባለ 

በናሆም አየለ

በአዲስ አበባ ከተማ ከአንድ ሳምንት በላይ ተቋርጦ የቆየውን የመታወቂያ መስጠት እና እድሳት አገልግሎትን በሚቀጥለው ሳምንት ለመጀመር የጥገና ስራ እያከናወነ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ የሲቪል ምዝገባ እና የነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲ ገለጸ። ኤጀንሲው ይሰጣቸው የነበሩ መደበኛ አገልግሎቶች የተቋረጡት፤ ከመረጃ ማከማቻ ቋቱ ጋር በተገናኙ “የቴሌኮም ኬብሎች” ላይ ጉዳት በመድረሱ መሆኑን ገልጿል። 

በአዲስ ከተማ አስተዳደር የሚገኘው የሲቪል ምዝገባ እና የነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲ፤ የመታወቂያ ስርጭት፣ የልደት እና የሞት ምዝገባ፣ ያላገባ የምስክር ወረቀት፣ የማስረጃ የማረጋገጥ ስራን እንዲሁም የጋብቻ እና የፍቺ ምዝገባን የሚከውን ተቋም ነው። ኤጀንሲው በመዲናዋ የሚገኙ 106 ወረዳዎችን “በዲጂታል” ስርዓት” በማስተሳሰር ይሰጣቸው የነበሩ አገልግሎቶች፤ ካለፈው አንድ ሳምንት ወዲህ በመቋረጣቸው በተገልጋዮች ላይ መጉላላትን አስከትሏል።

በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሶስት የሚገኝ የነዋሪነት ምዝገባ ጽህፈት ቤትን በትላንትናው ዕለት በአካል ተገኝቶ የተመለከተው የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ዘጋቢ፤ ለወትሮ በሰው ብዛት ይጨናነቅ የነበረው አገልግሎት መስጪያ ባዶ መሆኑን ታዝቧል። አገልግሎት መቋረጡን ባለመስማት ወደ ጽህፈት ቤቱ የመጡ ሁለት ነዋሪዎችም እምብዛም ሳይቆዩ መመለሳቸውንም ተመልክቷል።  

በዚሁ ጽህፈት የሚሰራ ባለሙያ፤ የመታወቂያ መስጠት፣ እድሳት እና ሌሎች አገልግሎቶች በመቋረጣቸው ሳቢያ፤ በቀን ከ50 በላይ ነዋሪዎችን “ሲስተም የለም” በማለት እንደሚመልሱ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግሯል። “ሲስተሙ ለምን እንደተቋረጠ ማዕከል ስንጠይቅ ‘ዳታ ሴንተሩ እየተስተካከለ ስለሆነ ነው፤ በትዕግስት ጠብቁ’ የሚል ምላሽ ነው የሚሰጡን” ሲል ችግሩ መቼ እንደሚፈታ እነርሱም እንደማያውቁ አስረድቷል።

በኤጀንሲው የ“ዲጂታል ስርዓት” ላይ ችግር ያጋጠመው፤ መስሪያ ቤቱ ከሚጠቀምባቸው የመረጃ ቋቶች መካከል አንደኛውን በሚያገናኙ የቴሌኮም መስመሮች ላይ ጉዳት ከደረሰ በኋላ መሆኑን በኤጀንሲው የኢንፎርሜሽን ኮሚኒኬሽን ቴክኖሎጂ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አእምሮ ካሳ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። በተለምዶ “ማዘጋጃ ቤት” ተብሎ በሚጠራው የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ጽህፈት ቤት ህንጻ ውስጥ ከሚገኘው የመረጃ ቋት ጋር የተያያዘው የቴሌኮም መስመር ጉዳት የደረሰበት፤ በአካባቢው የ“ኮሪደር ልማት” በሚከናወንበት ወቅት መሆኑንም አብራርተዋል።

በዚህ ጉዳት ሳቢያ በመዲናዋ የነዋሪነት ምዝገባን በ“ዲጂታል ስርዓት” መስጠት ካልጀመሩ 13 ወረዳዎች በቀር፤ በሌሎቹ ወረዳዎች የሚሰጡ  አገልግሎቶች “ሙሉ በሙሉ መቋረጣቸውን” የኤጀንሲው የኮሚኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ጀሚላ ረዲ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጠዋል። መስሪያ ቤቱ እያከናወነ ያለውን የጥገና ስራ በዚህ ሳምንት ለመጨረስ እና በቀጣዩ ሳምንት ሙሉ አገልግሎቱን ለመጀመር እየሰራ መሆኑን አቶ አእምሮ ገልጸዋል። 

የሲቪል ምዝገባ እና የነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲ የሚሰጣቸው አገልግሎቶች ላይ ከዚህ ቀደምም በተደጋጋሚ የአገልግሎት መቆራረጥ ሲከሰት መቆየቱን ያመኑት አቶ አእምሮ፤ የዚህ ምክንያቱ መስሪያ ቤቱ የሚጠቀመው የዲጂታል ስርዓት “ያረጀ በመሆኑ ነው” ብለዋል። መቆራረጡን በዘላቂነት ለማስቀረትም፤ ኤጀንሲው “አዲስ የዲጂታል ስርዓት እያለማ” መሆኑን አስታውቀዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)