የፌደራል መንግስት የህወሓት ታጣቂዎችን በአስቸኳይ ትጥቅ እንዲያስፈታ ኢዜማ ጠየቀ   

የፌደራል መንግስት ከህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ጋር በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ በተፈራረመው ስምምነት መሰረት፤ የህወሓት ታጣቂዎች በአስቸኳይ ትጥቃቸውን እንዲፈቱ እንዲያደርግ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ፓርቲ ጠየቀ። ይህ ሳይሆን ቀርቶ የህወሓት ታጣቂዎች በሚወስዷቸው እርምጃዎች በዜጎች ህይወት፣ አካል እና ንብረት ላይ ለሚደርሰው “ውድመት እና ምስቅልቅል”፤ የፌደራል መንግስት “ሙሉ ኃላፊነቱን የሚወስድ ይሆናል” ሲል ፓርቲው አሳስቧል።

ኢዜማ ጥያቄውን እና ማሳሰቢያውን ያቀረበው፤ በአላማጣ ከተማ እና አካባቢው የህወሓት ታጣቂዎች እየወሰዱት ነው ያለውን “የኃይል እርምጃ” በተመለከተ ዛሬ ሐሙስ ሚያዝያ 10፤ 2016 ባወጣው መግለጫ ነው። በእነዚህ አካባቢዎች ባለፉት ጥቂት ቀናት የተከሰቱ ሁነቶችን ከመገናኛ ብዙኃን ሲከታተል እና በራሱ የመረጃ ምንጮች ሲያጣራ መቆየቱን ፓርቲው በመግለጫው ላይ አመልክቷል። 

የህወሓት ታጣቂዎች በአካባቢዎቹ “ዳግም ወረራ ፈጽመዋል” ሲል የወነጀለው ኢዜማ፤ የፌደራል መንግስት ለችግሩ “ዛሬ ነገ ሳይል አፋጣኝ ዘላቂ መፍትሔ እንዲሰጥ” በመግለጫው ጠይቋል። የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሌተናል ጄነራል ታደሰ ወረደ ከትላንት በስቲያ በሰጡት መግለጫ፤ የትግራይ ኃይሎች “የተወሰኑ የራያ አካባቢዎችን ተቆጣጥረዋል” በሚል የወጡ ዘገባዎችን ውድቅ አድርገው ነበር። 

ኢዜማ በዛሬው መግለጫው፤ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) እና የአማራ ክልል መንግስት ባለፉት ቀናት እንደወጧቸው መግለጫዎች ሁሉ፤ ህወሓት “ለአራተኛ ጊዜ ወረራ ፈጽሟል” ሲል ከስሷል። ህወሓት ከፌደራል መንግስት ጋር በተፈራረመው ስምምነት መሰረት “በሰላሳ ቀናት ውስጥ መሳሪያ አስረክቦ ወደ ሰላም አስተሳሰብ እንዲመጣ ሊደረግ ይገባ ነበር” ያለው ፓርቲው፤ ይህ ባለመሆኑ ምክንያት ቡድኑ “ይበልጥ እራሱን አደራጅቶ ዛሬም ንጹሀን ዜጎችን ለመከራ ለእንግልት እና ከቀያቸው ተፈናቅለው ሜዳ ላይ እንዲወድቁ እያደረገ ይገኛል” ብሏል። 

“ኢ-ሕገ መንግስታዊ አደረጃጀት የነበረው የክልል ልዩ ኃይል ትጥቅ በማስፈታት መዋቅሩ እንዲፈርስ ሲደረግ፤ የፓርቲነት ሕጋዊ እውቅና የሌለው ሕወሓት በገሀድ የራሱን ታጣቂ ኃይል ያደራጀ ብቸኛ ስብስብ ሆኖ በነጻነት እየተንቀሳቀሰ ይገኛል” ሲልም ኢዜማ በመግለጫው አጽንኦት ሰጥቷል። “ይህ ስብሰብ መሳሪያ የታጠቀ ኃይል ኖሮት እስከቀጠለ ድረስ እንደ ሀገር ሰላም አይኖረንም” ሲልም ፓርቲው አክሏል። 

“ከፕሪቶሪያው ስምምነት ማግስት ልዩ አትኩሮት ሊሰጠው ይገባል ስንል የነበረው ቡድኑን ትጥቅ የማስፈታት ጉዳይ ዛሬም ቢሆን ከአጎራባች ክልሎች አልፎ ለሀገር ሉዓላዊነት ጠንቅ ሊሆን እንደሚችል መታሰብ ይኖርበታል” ያለው ኢዜማ፤ የፌደራል መንግስት ትጥቅ የማስፈታቱን ተግባር “ውሎ ሳያደር ሊያከናውነው እንደሚገባ” በአጽንኦት አሳስቧል። 

በኢትዮጵያ መንግስት እና በህወሓት መካከል ጥቅምት 23፤ 2015 በፕሪቶሪያ ከተማ በተፈረመው ግጭት የማቆም ስምምነት መሰረት፤ ከባድ የጦር መሳሪያዎችን የማስፈታት ሂደት ቅድሚያ ተሰጥቶት የሚከናወን ተግባር ነው። የጦር መሳሪያዎችን የማስፈታቱ ሂደት፤ የሁለቱ ተፋላሚ ወገኖች የጦር አዛዦች ከሚያደርጉት ስብሰባ፤ አስር ቀናት በኋላ ሊከናወን እንደሚገባ በግጭት ማቆም ስምምነት ስድስተኛ አንቀጽ ላይ ሰፍሯል።

ከዚህ ስምምነት መፈረም አንድ ሳምንት በኋላ በኬንያ ናይሮቢ የተገናኙት የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ እና የትግራይ ኃይሎች አዛዥ የነበሩት ጄኔራል ታደሰ ወረደ፤ የግጭት ማቆሙን ተግባራዊ የሚያደርግ ስምምነት ተፈራርመዋል። ቀላል የጦር መሳሪያዎችን ጨምሮ የህወሓት ታጣቂዎችን ትጥቅ የማስፈታቱ አጠቃላይ ሂደት፤ የፕሪቶሪያው ስምምነት በተፈረመ በ30 ቀናት ውስጥ ሊጠናቀቅ ከስምምነት ላይ ተደርሶ እንደነበር ይታወሳል። 

ኢዜማ በዛሬው መግለጫው “የህወሓት አመራር ነን የሚሉ አካላት” ሲል የጠራቸው ግለሰቦች፤ “ከፕሪቶሪያው ስምምነት ባፈነገጠ መልኩ” የሚያምታቱ መግለጫዎችን በአደባባይ ሲናገሩ፤ የፌደራል መንግስት “ኃላፊነቱን በአግባቡ አልተወጣም” ሲል ተችቷል።  “አሁን እየታየ ላለው ውዥንብር እና ችግር የአንበሳውን ድርሻ የሚወስደው የፌደራል መንግስት ነው” ሲልም ፓርቲው ነቅፏል።

በፌደራል መንግስት በኩል የሚታየውን “ደካማ መረጃ አሰጣጥ፣ ቸልተኝነት እና መሰል ግዴለሽነት የተሞላ ተግባር፤ በእጅጉ የሚያሳዝነን፣ በጽኑ የምናወግዘው ነው” ያለው ኢዜማ፤ የህወሓትን “የማናለብኝነት አካሄድ” ስርዓት ማስያዝ በፌደራል መንግስት በኩል ቅድሚያ መሰጠት ያለበት ጉዳይ መሆኑን ጠቁሟል። ኢዜማ “ጦርነት የሚጎስመው ስብስብ” ሲል በመግለጫው የጠቀሰውን አካል፤ የፌደራል መንግስት “ስርዓት እንዲያሲዝ እና ሕግ እንዲያስከብር” በአጽንኦት ጠይቋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)