የቡድን ሰባት ሀገራት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች፤ በኢትዮጵያ ያሉ “ውጥረቶች” እንደሚያሳስቧቸው ገለጹ  

የቡድን ሰባት ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በኢትዮጵያ በርካታ አካባቢዎች ይታያሉ ያሏቸው፤ “የማያቋርጡ እና ኃይለኛ ውጥረቶች” እንደሚያሳስቧቸው ገለጹ። በኢንዱስትሪ የበለጸጉት ሰባት ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በኢትዮጵያ ይፈጸማሉ የሚባሉ “የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች እና በደሎች ሪፖርቶች”፣ “ብርቱ ኢኮኖሚያዊ ቀውስ” እና “የምግብ ዋስትና እጦት መስፋፋት” እንዳሰጋቸውም አስታውቀዋል።

ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቹ በኢትዮጵያ ጉዳይ ስጋታቸውን ያንጸባረቁት፤ በጣልያኗ ካፕሪ ደሴት ያካሄዱትን ስብሰባ ሲያጠናቅቁ ዛሬ አርብ ምሽት ባወጡት  መግለጫ ነው። ሚኒስትሮቹ በዚሁ መግለጫቸው፤ በኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት እና በህወሓት መካከል በተፈረመው ግጭት የማቆም ስምምነት አተገባበር ረገድ የተወሰዱ እርምጃዎችን በበጎ እንደሚቀበሉ ገልጸዋል።

በሰብዓዊ መብቶች እና በሲቪል ሰዎች ጥበቃ፣ ውጥረቶችን ለመፍታት በሚደረግ ፖለቲካዊ ውይይት፣ በዕርቅ፣ በብሔራዊ ውይይት፣ የሽግግር ፍትህ እና በግጭት ወቅት ወንጀል የፈጸሙ ተጠያቂ ለማድረግ፤ ተጨማሪ እና ዘላቂ እርምጃዎች ተግባራዊ እንዲደረጉ አበረታተዋል። በሌሎች የኢትዮጵያ ክፍሎች በመካሄድ ላይ በሚገኙ ግጭቶች የሚሳተፉ ወገኖች፤ በንግግር ሰላም ለማውረድ ተመሳሳይ ቁርጠኝነት እንዲኖራቸውም ጥሪ አቅርበዋል። 

በግጭት የተጎዱ ማህበረሰቦች በማገገም እና መልሶ ግንባታ፣ የቀድሞ ታጣቂዎችን ትጥቅ አስፈትቶ በመበተን እና መልሶ በማዋሀድ እንዲሁም ለተፈናቃዮች ዘላቂ መፍትሔ በማበጀት ከተገኘው ሰላም በአፋጣኝ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ እንደሚያሻ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቹ በመግለጫቸው አሳስበዋል።

የቡድን ሰባት አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች መግለጫ፤ ኢትዮጵያ እና ሶማሌላንድ ከአራት ወራት ገደማ በፊት የተፈራረሙትን የመግባቢያ ስምምነት ጉዳይ ጭምር ያነሳ ነው። የመግባቢያ ስምምነቱ “እንደሚያሳስባቸው” የገለጹት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቹ፤ ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ በመካከላቸው የተፈጠረው ውጥረት እንዳይባባስ ሁሉንም የውይይት “ቻናሎች” ክፍት እንዲያደርጉ መክረዋል።

ሁለቱ ሀገራት በአፍሪካ ህብረት ማዕቀፍ እና በሁለትዮሽ መገናኛዎቻቸው ተጠቅመው፤ ከቀጠናዊ አጋሮቻቸው እንዲሰሩም ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቹ አሳስበዋል። ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ ልዩነታቸውን ለመፍታት የሚከተሉት አካሄድ፤ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ቻርተር ከሰፈረው የሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት መርህ ጋር የተጣጠመ መሆን እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል። 

ከትላንት በስቲያ ረቡዕ ሚያዝያ 9፤ 2016 ጀምሮ ሲካሄድ በቆየው እና ዛሬ በተጠናቀቀው የቡድን ሰባት ሀገራት ስብሰባ፤ የካናዳ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ጣልያን፣ ጃፓን፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና አሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ተሳትፈዋል። በስብሰባው ላይ የአውሮፓ ህብረት ከፍተኛ ተወካይም ተሳትፈዋል። 

ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቹ በስብሰባው ማጠናቀቂያ ባወጡት መግለጫ፤ ከኢትዮጵያ በተጨማሪ የአፍሪካ ቀንድ፣ የሶማሊያ፣ የሱዳን፣ የሊቢያ እና የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ጉዳዮች ተነስተውበታል። መግለጫው ከአፍሪካ ባሻገር፤ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቹ በስብሰባቸው ትኩረት ያደረጉባቸው የተለያዩ የዓለም ጉዳዮችን ጭምር የዳሰሰ ነው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)