በሰሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ የተከሰተውን የእሳት ቃጠሎ በማስነሳት የተጠረጠሩ ሶስት ሰዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ   

በናሆም አየለ

በሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ባለፈው ሐሙስ የተቀሰቀሰውን የሰደድ እሳት፤ እስካሁን ሙሉ ለሙሉ መቆጣጠር እንዳልተቻለ የሰሜን ጎንደር ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ቢምረው ካሳ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናገሩ። ለእሳት ቃጠሎው መንስኤ ሳይሆኑ አይቀሩም በሚል የተጠረጠሩ ሶስት ሰዎች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑንም ገልጸዋል። 

በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በዓለም ቅርስነት በተመዘገበው የሰሜን ተራሮች ፓርክ የእሳት ቃጠሎ የተነሳው፤ ከሶስት ቀናት በፊት ሚያዚያ 10፤ 2016 ዓ.ም ምሽት መሆኑን የሰሜን ጎንደር ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አስረድተዋል። የእሳት ቃጠሎው ሚትጎጎ፣ ሰሀ፣ ግጭ እና እናትዬ የተባሉ የፓርኩ ክፍሎችን ማዳረሱን እና ዛሬም በአካባቢዎቹ ጭስ እንደሚታይ አክለዋል። 

በሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ጽህፈት ቤት የአግሮ ኢኮሎጂ እና የዱር እንስሳት ተመራማሪ የሆኑት አቶ ታደሰ ይግዛው፤ ቃጠሎው የደረሰበት ቦታ “ቱሪስቶች የሚጎበኙት ቦታ እና ጥሩ የሆነ እይታ የነበረው” መሆኑን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አብራርተዋል። ቃጠሎው በምን ያህል የፖርኩ ክፍል ላይ ውድመት እንዳደረሰ እስካሁን ባይለይም፤ እሳቱ የደረሰባቸው ቦታዎች ግን በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ ቀይ ቀበሮ እና ዋልያ አይቤክስን የመሳሰሉ ብርቅዬ እንስሳቶች የሚኖሩባቸው መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ፎቶ፦ ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) ቪዲዮ የተወሰደ

ፓርኩ እንደ ሁለቱ ብርቅዬ እንስሳት ሁሉ፤ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙት ጭላዳ ዝንጀሮ እና የምኒልክ ድኩላ መኖሪያ ነው። በፓርኩ ውስጥ ከ1,200 በላይ የተለያዩ የዕፅዋት ዝርያዎችም ይገኛሉ። የሰደድ እሳቱ በአብዛኛው በጓሳ ሳር የተሸፈነውን የፓርኩን ክፍል እንዳቃጠለ  የሰሜን ጎንደር ዞን ምክትል አስተዳዳሪ ገልጸዋል። 

የጓሳ ሳር ደግሞ በባህሪው ንፋስ እና ሙቀት ባገኘ ቁጥር ተመልሶ የሚነድ መሆኑን የጠቀሱት ምክትል አስተዳዳሪው፤ በፓርኩ ገደላማ ቦታዎች ላይ ያለው እሳት ተገልብጦ ወደ አጎራባች ወረዳዎች እንዳይሄድ ስጋት መኖሩን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ለአጎራባች ወረዳዎች ነዋሪዎችም ስጋት መኖሩ ተገልጾ በተጠንቀቅ እንዲጠብቁ መደረጉንም አመልክተዋል። 

በሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ እሳት የተነሳበት መንስኤ ለማወቅ የአካባቢው ኃላፊዎች እና የፓርኩ አስተዳዳሪዎች ከጸጥታ ኃይሎች ጋር በመሆን ማጣራት እያደረጉ መሆኑን አቶ ቢምረው ገልጸዋል። “ፓርኩ ባለበት አካባቢ የሚኖሩ ነዋሪዎች፤ ህገወጥ ከሰል ሲያከስሉ ወይንም ለእርሻ ምንጣሮ ቃጠሎ ሲያደርጉ እሳቱ ተነስቶ ሊሆን ይችላል” የሚል ግምት መኖሩን የጠቆሙት ምክትል አስተዳዳሪው፤ ከዚህም ጋር በተያያዘ ሶስት ሰዎች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑን አስታውቀዋል። 

ፎቶዎች፦ የአማራ ክልል የአካባቢና ደን ጥበቃ ባለስልጣን

በኢትዮጵያ ካሉ 13 ብሔራዊ ፓርኮች አንዱ የሆነው ሰሜን ተራራዎች ብሔራዊ ፓርክ ከአምስት አመት በፊት ተመሳሳይ የእሳት ቃጠሎ አስተናግዶ እንደነበር ይታወሳል። በወቅቱ ተነስቶ በነበረው ከፍተኛ የእሳት ቃጠሎም ከ340 ሄክታር በላይ የፓርኩ ክፍል ውድመት ደርሶበት ነበር። በፓርኩ የአግሮ ኢኮሎጂ እና የዱር እንስሳት ተመራማሪው አቶ ታደሰ፤ አሁን የተከሰተው የእሳት ቃጠሎ ከአምስት አመት በፊት ከነበረው የሚለየው “ውጨና” የተሰኘው የዛፍ አይነትላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱ መሆኑን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስረድተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)