ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሀገራዊ ምክክር ላይ በአጀንዳነት የሚቀርቡ ጉዳዮችን እንዲያዘጋጁ ተጠየቁ

በናሆም አየለ

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን፤ በሀገራዊ ምክክር ላይ “አጀንዳ ሊሆኑ ይገባሉ” የሚሏቸውን ጉዳዮች እንዲያዘጋጁ  ለተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች በደብዳቤ ጥሪ አቀረበ። የፖለቲካ ፓርቲዎቹ በሚያቀርቧቸው አጀንዳዎች ላይ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት እና የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ውይይት የሚያካሄዱበትን ሁኔታ እንደሚመቻች ኮሚሽኑ አስታውቋል። 

“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የተመለከተችው እና ባለፈው ሳምንት ለተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተላከው ደብዳቤ፣ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከባለድርሻ አካላት “አጀንዳዎችን የመሰብሰብ ስራ በማከናወን ላይ እንደሚገኝ” ጠቅሷል። በዚህም መሰረት የፖለቲካ ፓርቲዎቹ “ለሀገራዊ ምክክር ሊቀርብ ይገባል” የሚሏቸውን “የአጀንዳ ነጥቦች” የማዘጋጀት ስራ እንዲያከናውኑ ኮሚሽኑ በደብዳቤው ጠይቋል። 

በታህሳስ 2014 ዓ.ም. በጸደቀው የኮሚሽኑ የማቋቋሚያ አዋጅ፤ የሀገራዊ ምክክር አጀንዳ “በተለያዩ የፖለቲካ እና የሃሳብ መሪዎች፣ በመንግስት እንዲሁም በህብረተሰብ ክፍሎች መካከል፤ ሀገራዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ያሉ ልዩነቶችን ወይም የአለመግባባት መንስኤዎችን በትክክል የሚዳስሱ ጉዳዮች” መሆናቸውን አስቀምጧል። ኮሚሽኑ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት የሚቀርቡለትን እነዚህን አጀንዳዎች ካደራጀ በኋላ ውይይቶች የሚካሄዱባቸውን ርዕሰ ጉዳዮች የመለየት ሚናም በአዋጁ ተሰጥቶታል። 

ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ለፖለቲካ ፓርቲዎች በላከው ደብዳቤ፤ ፓርቲዎቹ በሚያቀርቧቸው አጀንዳዎች ላይ “ከሌሎች ባለድርሻ አካላት እና የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር በመገናኘት ውይይት የሚያካሄዱበትን ሁኔታ በቀጣይ የሚያሳውቅ መሆኑን” አመልክቷል። ይህ የኮሚሽኑ ደብዳቤ እንደደረሳቸው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያረጋገጡት የኢትዮጵያ ህዝብ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢህአፓ)፣ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) እና እናት ፓርቲ፤ የአጀንዳ ነጥቦችን ለኮሚሽኑ መላክን በተመለከተ የተለያየ አቋም አንጸባርቀዋል። 

የኢህአፓ ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር አቶ አብርሃም ሃይማኖት፤ “የፖለቲካ እስረኞች፣ ጋዜጠኞች፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች፣ እስካልተፈቱ ድረስ” ፓርቲያቸው “አጀንዳዎቹን ለኮሚሽኑ እንደማይልክ” ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። የእናት ፓርቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሰይፈ ሥላሴ አያሌው በበኩላቸው፤ የሚመሩት ፓርቲ ለሀገራዊ ምክክሩ የሚቀርቡ አጀንዳዎችን ለኮሚሽኑ ማስገባትን በተመለከተ ከውሳኔ ላይ እንዳልደረሰ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። በጉዳዩ ላይ የሚያሳልፈውን ውሳኔ ወደፊት እንደሚያሳውቅም አክለዋል።

የኢዜማ የሀገራዊ ምክክር ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ እዮብ መሳፍንት፤ ፓርቲው ከኮሚሽኑ ጋር “አብሮ ለመስራት የሚያስችለውን ሰነድ ማዘጋጀቱን” እንዲሁም የሚያቀርባቸውን “አጀንዳዎች መለየቱን” ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስረድተዋል። ፓርቲው በቀጣይ ሊያደርገው ያቀደውን በተመለከተ ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ እዮብ፤ “የተላከልን ደብዳቤ ላይ ‘አጀንዳዎቻችሁን ለህዝብ የምታቀርቡበትን መንገድ እናሳውቃችኋለን’ ስለሚል እሱን እየጠበቅን ነው ያለነው” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል። 

የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ከሁለት ሳምንት በፊት በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፤ ለሀገራዊ ምክክር የሚሆኑ አጀንዳዎችን የማሰባሰብ ስራ “ባጠሩ ሳምንታት” ውስጥ እንደሚጀምር አስታውቆ ነበር። የፖለቲካ ፓርቲዎችን፣ ተቋማትን እንዲሁም ማህበራትን የሚወክሉ ተወካዮች፤ ከወከላቸው ማህበረሰብ ግብዓቶችን ለማሰባሰብ አስፈላጊውን ዝግጅት እንዲያደርጉም በወቅቱ ጥሪ ማድረጉ አይዘነጋም። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)