በናሆም አየለ
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ባለፉት ዘጠኝ ወራት ውስጥ “ህግን ተላልፈው ተገኝተዋል” ላላቸው 55 የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ መስጠቱን አስታወቀ። ከእነዚህ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ውስጥ ለአምስቱ “ጥብቅ የጹሁፍ ማስጠንቀቂያ” እንደተሰጣቸውም ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ገልጿል።
ሁለት እና ከዚያ በላይ በሆኑ ሰዎች በፈቃደኝነት የሚመሰረቱና ለትርፍ ያልተቋቋሙ ድርጅቶች የመቆጣጠር ስልጣን በአዋጅ የተሰጠው መስሪያ ቤቱ፤ ድርጅቶቹ ስራቸውን በህግ አግባብ ማከናወናቸውን ለማረጋገጥ በየጊዜው አስፈላጊውን ክትትል ያደርጋል። በዚህም መሰረት ባለስልጣኑ ያወጣውን መመሪያ ተላልፈው ተገኝተዋል ላላቸው 55 ድርጅቶች ማስጠንቀቂያ መስጠቱን በመስሪያ ቤቱ የህዝብ ግንኙነት እና ኮሙኒኬሽን ስራ አስፈጻሚ ትግስት ዳኝነት ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።
ከእነዚህ የሲቪል ማህብረሰብ ድርጅቶች መካከል አርባ አንዱ ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው “ለአስተዳደራዊ ወጪዎች ሊወጣ ከሚገባው በላይ ወጪ በማውጣታቸው” መሆኑን የህዝብ ግንኙነት እና ኮሙኒኬሽን ስራ አስፈጻሚዋ አስረድተዋል። በ2011 ዓ.ም. የተሻሻለው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ፤ ለህዝብ ጥቅም የተቋቋሙ ድርጅቶች የአስተዳደር ወጪ ከገቢው 20 በመቶ ሊበልጥ እንደማይገባ ይደነግጋል።
አንድ ድርጅት “ከሚያከናውነው የፕሮጀክት ስራ ጋር ተያያዥነት የሌለው” ነገር ግን “ለድርጅቱ ህልውና ቀጣይነት አስፈላጊ የሆነ ከአስተዳደር ስራዎች ጋር የተያያዘ ወጪ” እንደ አስተዳደር ወጪ እንደሚቆጠር በአዋጁ ላይ ተቀምጧል። የአስተዳደር ሰራተኞች ደመወዝ እና ጥቅማ ጥቅሞች፣ ከአስተዳደር ስራ ጋር የተያያዙ የአላቂና ቋሚ እቃዎች ግዢ፣ የጥገና እና እድሳት ወጪዎች፣ የቢሮ ኪራይ የመሳሰሉ ወጪዎች በዚህ ምድብ ስር የሚካተቱ መሆናቸውንም በአዋጁ ላይ ሰፍሯል።
የአስተዳደር ወጪ ገደብን ተላልፈው ከተገኙ ድርጅቶች መካከል አምስቱ የህግ ጥሰቱን ለሁለተኛ ጊዜ ፈጽመው በመገኘታቸው “ጥብቅ ማስጠንቀቂያ” እንዲሰጣቸው እንደተደረገ ትግስት ተናግረዋል። “ጥብቅ ማስጠንቀቂያ” የተሰጣቸው ድርጅቶች አሰራራቸውን የማያስተካክሉ ከሆነ፤ የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ዋና ዳይሬክተር ድርጀቶቹ እንዲታገዱ ሊወስን እንደሚችል ከአራት ዓመት በፊት የተሻሻለው አዋጅ ያትታል።
የዋና ዳይሬክተሩ ውሳኔ በሲቪል ማህበረሰብ ቦርድ ካልተነሳ ወይም በፍርድ ቤት ካልታገደ በቀር፤ የእገዳ ውሳኔው በተሰጠ በሶስት ወራት ውስጥ ማስተካከያ ያላደረገ ድርጅት እንዲፈርስ ሊደረግ እንደሚችልም በአዋጁ ላይ ተመልክቷል። የመፍረስ ውሳኔ የተሰጠበት ድርጅት አባላት፣ መስራቾች ወይም ኃላፊዎች፤ ውሳኔው በተሰጠ በ30 ቀናት ውስጥ ቅሬታቸውን ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የማቅረብ መብት አላቸው።
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን በዚህ በጀት ዓመት ማስጠንቀቂያ ከሰጣቸው ድርጅቶች መካከል አስራ ሶስቱ ደብዳቤ እንዲደርሳቸው የተደረገው፤ “የስራ ፈቃድ ሳያገኙ የውጭ ዜጎችን ቀጥረው በመገኘታቸው” እንደሆነ የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የህዝብ ግንኙነት እና ኮሙኒኬሽን ስራ አስፈጻሚ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል።
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ፤ ማንኛውም ድርጅት “አግባብ ባለው ህግ መሰረት የስራ ፈቃድ ያልተሰጠውን የውጭ ዜጋ መቅጠር አይችልም” ሲል ክልከላ ያስቀምጣል። የውጭ ሀገር ዜጋን ሰራተኛው አድርጎ መቅጠር የሚፈልግ የትኛውም ድርጅት ከባለስልጣኑ ፍቃድ ሊጠይቅ እንደሚገባ የሚናገሩት የህዝብ ግንኙነት እና ኮሙኒኬሽን ስራ አስፈጻሚዋ፤ ይህንን በማያደርጉ ድርጅቶች ላይ መስሪያ ቤቱ እስከ እግድ የሚዘልቅ እርምጃ ሊወስድ እንደሚችል ያስረዳሉ።
“[ድርጅቶቹ] በመጀመሪያ በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ ይጠየቃሉ። ሁለተኛ ያለፍቃድ ያስገቡትን የውጭ ሃገር ዜጋ እንዲያስወጡ ይደረግና ላጠፉት ጥፋት የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ ይጻፍላቸዋል። [ከዚህ በኋላ] ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ እስከ ማገድ የሚደርስ እርምጃ ይወስዳል” ሲሉ ሂደቱን አብራርተዋል። ባለፉት ዘጠኝ ወራት ማስጠንቀቂያ ከተሰጣቸው መካከል ቀሪው አንድ ድርጅት፤ ከባለስልጣን መስሪያ ቤቱ እውቅና ውጭ የባንክ አካውንት ከፍቶ ሲንቀሳቀስ በመገኘቱ ደብዳቤ እንዲደርሰው መደረጉን ትግስት አክለዋል።
“[ድርጅቶቹ] በመጀመሪያ በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ ይጠየቃሉ። ሁለተኛ ያለፍቃድ ያስገቡትን የውጭ ሃገር ዜጋ እንዲያስወጡ ይደረግና ላጠፉት ጥፋት የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ ይጻፍላቸዋል። [ከዚህ በኋላ] ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ እስከ ማገድ የሚደርስ እርምጃ ይወስዳል”
ትግስት ዳኝነት፤ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ህዝብ ግንኙነት እና ኮሙኒኬሽን ስራ አስፈጻሚ
የሲቪል ማህብረሰብ ድርጅቶች “በራሳቸው ያመነጩትንም ይሁን ከባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በፈንድ መልክ ያገኙትን ገንዘብ ሊያንቀሳቅሱት የሚገባው፤ በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ እውቅና በተከፈተ የባንክ ሂሳብ ነው” ሲሉ ማስጠንቀቂያ የተሰጠው ድርጅት የፈጸመውን ጥሰት ስራ አስፈጻሚዋ ገልጸዋል። የሲቪል ማህበረሰብ ፈንድን ለማስተዳደር በወጣ መመሪያ ላይ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ለመዘገባቸው አገር በቀል የሲቪል ድርጅቶች “የፋይናንስ ወይም የፕሮጀክት መሳሪያዎች ድጎማ” ሊያደርግ እንደሚችል ተመልክቷል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)