የስፖርት ውርርድን በተመለከተ አሁን በስራ ላይ የሚገኙት መመሪያዎች እና ደንቦች፤ “ጥናትን መሰረት አድርገው ሊታገዱ ይገባል” የሚል “ጽኑ እምነት” እንዳለው የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳዮች ሚኒስቴር አስታወቀ። የስፖርት ውርርድ በወጣቶች ላይ “አሉታዊ ተጽዕኖ” ማሳደሩን እና “ለብዙ ቤተሰብ መፍረስ” ምክንያት መሆኑን ሚኒስቴሩ ገልጿል።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ይህን የገለጸው የዘጠኝ ወር የስራ አፈጻጸም ሪፖርቱን፤ ዛሬ ሐሙስ ሚያዝያ 17፤ 2016 ለተወካዮች ምክር ቤት ባቀረበበት ወቅት በተደረገው ውይይት ላይ ነው። በዛሬው የምክር ቤቱ ስብሰባ በፓርላማ አባላት ከተነሱ ጉዳዮች ውስጥ የወጣቶች ሱሰኝነት እየጨመረ መምጣት ይገኝበታል። በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የወጣቶች ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ሙና አህመድ ችግሩ በሀገር ደረጃ እየተባባሰ መምጣቱን አምነዋል።
“በተለይ አሉታዊ መጤ ልማዶች እና አደንዛዥ ዕጽ እንደ ሀገር እየተስፋፋ የመጣበት ሁኔታ አለ። ብዙ ወጣቶችን እያጣን የመጣንበት ሁኔታ ነው። ነገ ሀገር ይመራል፣ ይህቺን ሀገር ወደ በለጸገች ደረጃ ያደርሳታል ብለን የምናስበው ወጣት፤ ሩቅ አስበን መንገድ እየቀሩ ያሉበት ሁኔታ ስላለ፤ እዚህ ላይ ሁላችንም ርብርብ ካደረግን የተሻለ ነገር ማምጣት እንችላለን የሚል ነገር ነው ያለን” ሲሉ ጉዳዩ የበለጠ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ሙና አስገንዝበዋል።
ሚኒስትር ዴኤታዋ “በወጣቶች ሰብዕና ግንባታ ላይ ተግዳሮት ፈጥሯል” በሚል በማሳያነት ያነሱት የስፖርት ውርርድን (sport betting) ነው። የስፖርት ውርርድ ለሀገሪቱ ገቢ ከሚያስገባው ገቢ አኳያ ብቻ ሳይሆን፤ በወጣቶች ሰብዕና ላይ ከሚያስከትለው “አሉታዊ ተጽዕኖ” አንጻርም ሊታይ እንደሚገባ በማብራሪያቸው ላይ ጠቅሰዋል።
“ማንም ሀገር አዋጅ፣ ደንብ፣ ህጎች ሲያወጣ፤ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ ነው። በዚህ ረገድ ስፖርት ‘ቤቲንግ’ ላይ ያሉት፣ ካሁን በፊት የወጡት መመሪያዎች፣ ደንቦች፤ እንደ ሚኒስቴር መስሪያ ቤታችን ጥናትን መሰረት አድርገው ሊታገዱ ይገባል የሚል ጽኑ እምነት አለን” ያሉት ሙና፤ ፓርላማው በዚህ ረገድ እገዛ ሊያደርግ እንደሚገባ ተናግረዋል። “ገቢ አንድ ነገር ነው። ሀገር ገቢ ማግኘት አለባት። ነገር ግን በወጣቶቹ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እያስከተለ ስለሆነ፣ ብዙ ወጣቶች እያጣን ስለሆነ፣ ብዙ ቤተሰብ እየፈረሰ ስለሆነ እዚህ ላይ ብንደጋገፍ የተሻለ ነገር መስራት እንችላለን ብዬ አስባለሁ” ብለዋል ሚኒስትር ዴኤታዋ።
በተወካዮች ምክር ቤት የጤና ማህበራዊ ልማት፣ ባህልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወርቀሰሙ ማሞ፤ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሪፖርት ላይ የማጠቃለያ አስተያየት ባቀረቡበት ጊዜም የስፖርት ውርርድ ጉዳይን አስንተዋል። “ብሔራዊ ሎተሪ ከገቢ ጋር አይቶታል። በዚህም በኩል ደግሞ ሌላ ችግር እየፈጠረ ነው። ተማሪዎች ዩኒፎርማቸውን እያወለቁ [የስፖርት ውርርድ] ቤት ይገባሉ። ስለዚህ መቼ ያጥኑ። አእምሮአቸው ሊጎዳ ስለሚችል ጥንቃቄ ተደርጎ መሰራት አለበት” ሲሉ የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዋ አሳስበዋል።
“ብሔራዊ ሎተሪ ከገቢ ጋር አይቶታል። በዚህም በኩል ደግሞ ሌላ ችግር እየፈጠረ ነው። ተማሪዎች ዩኒፎርማቸውን እያወለቁ [የስፖርት ውርርድ] ቤት ይገባሉ። ስለዚህ መቼ ያጥኑ። አእምሮአቸው ሊጎዳ ስለሚችል ጥንቃቄ ተደርጎ መሰራት አለበት”
ወርቀሰሙ ማሞ፤በተወካዮች ምክር ቤት የጤና ማህበራዊ ልማት፣ ባህልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በስፖርት ውርርድ ላይ በተሰማሩ አገልግሎት ሰጪዎች ላይ በቅርቡ የወሰደውን እርምጃ “ጥሩ ስራ” ሲሉ ያደነቁት የቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢዋ፤ ይህ አካሄድ በሌሎችም አካባቢዎች በተሞክሮነት ሊወሰድ እንደሚገባ ጠቁመዋል። የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳዮች ሚኒስቴርም፤ ከስፖርት ውርርድ ጋር በተያያዘ ያለውን የወጣቶች ሁኔታ “የወደፊት የትኩረት አቅጣጫ አድርጎ እንዲያየው” እና “ጠንካራ ክትትል” እንዲያደርግ ምክረ ሃሳባቸውን አቅርበዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)