በተስፋለም ወልደየስ
ማንኛውም የመንግስት መስሪያ ቤት “ኢትዮጵያን የሚመስል የሰራተኞች ስብጥር መኖሩን የሚያረጋግጥ”፣ “የብሔር ብሔረሰቦችን ብዙሃነት እና አካታችነት” ያገናዘበ ስርዓት ተግባራዊ ማድረግ እንዳለበት የሚደነግግ የአዋጅ ረቂቅ ለፓርላማ ቀረበ። በመንግስት መስሪያ ቤት ውስጥ የሚፈጸም የሰራተኛ ስምሪት፤ የብሔር ብሔረሰቦችን እና ህዝቦችን “ሚዛናዊ ተጽዕኖ” ለማሳደግ በሚያስችል መልኩ መፈጸም እንዳለበትም የአዋጅ ረቂቁ ያዝዛል።
እነዚህን ድንጋጌዎች ያካተተው አዲሱ የህግ ማዕቀፍ፤ በ2010 ዓ.ም. የጸደቀውን እና እስካሁን በስራ ላይ የቆየውን “የፌደራል መንግስት ሰራተኞች አዋጅ” የሚተካ ነው። በአስራ ሰባት ክፍሎች እና በ160 አንቀጾች የተዋቀረው ይህ የአዋጅ ረቂቅ፤ የደመወዝ ጭማሪ፣ የደመወዝ እርከን፣ የመንግስት ሰራተኞች ክፍያ እና ጥቅም ጥቅም፣ የማትጊያ ወይም ማበረታቻ ስርዓት፣ የሰራተኞች ብቃት ምዘና እና ማረጋገጫ፣ የስልጠና አሰጣጥ እና ስራ ስምሪትን የተመለከቱ ድንጋጌዎች በዝርዝር የቀረቡበት ነው።
በነባሩ አዋጅ ያልተካተቱ “ነጻ ገለልተኛ ስርዓት መገንባት”፣ “ሁሉ አቀፍ ብዝሃነት፣ አካታችነት እና ተጨማሪ የድጋፍ እርምጃ አፈጻጸምን” የተመለከቱ ድንጋጌዎችንም አዲሱ የአዋጅ ረቂቅ በውስጡ ይዟል። የአዋጅ ረቂቁ ዛሬ ማክሰኞ ግንቦት 6፤ 2016 በተካሄደው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ላይ በቀረበበት ወቅት፤ አዲሱ የህግ ማዕቀፉ እንዲዘጋጅ ካስፈለገበት ምክንያቶች ውስጥ የ“ህብረ ብሔራዊነትን” ጉዳይ አንዱ መሆኑን በፓርላማ የመንግስት ተጠሪው አቶ ተስፋዬ በልጅጌ ተናግረዋል።
“የመንግስት ሰራተኞች የሰው ኃይል ምልመላ እና መረጣ ግልጽነት ባለው ውድድር እና ብቃት ላይ የተመሰረተ ሆኖ ህብረ ብሔራዊነትን፣ የአካል ጉዳተኞች፣ የጾታ ተዋጽኦ እና የመሳሰሉትን ብዝሃነት እና አካታችነት ያገናዘበ፤ የመንግስት ሰራተኞች ስብጥርን ከግምት ውስጥ ያስገባ የመንግስት አገልግሎት እና አስተዳደር ስርዓት መገንባት አስፈላጊ በመሆኑ ይህ ረቂቅ የፌደራል ሰራተኞች አዋጅ ተዘጋጅቷል” ሲሉ አቶ ተስፋዬ ለፓርላማ አባላት አስረድተዋል።
የአዋጅ ረቂቁ ይህንን ጉዳይ በዳሰሰበት ክፍሉ፤ “በማንኛውም የመንግስት መስሪያ ቤት ኢትዮጵያን የሚመስል የመንግስት ሰራተኞች ስብጥር መኖሩን በማረጋገጥ፤ የብሔር ብሔረሰቦችን፣ የአካል ጉዳተኞች፣ የጾታ ተዋጽኦ የመሳሰሉትን ብዙሀነት እና አካታችነትን ያገናዘበ የመንግስት አገልግሎት እና አስተዳደር ስርዓት ተግባራዊ መደረግ አለበት” ሲል ደንግጓል። የመንግስት መስሪያ ቤቶች “ብቃት እና ውድድርን መሰረት በማድረግ” የሰራተኞች ስብጥር እንዲኖር የሚያስችሉ ዕቅዶችን መተግበር እንዲሁም የክትትልና የቁጥጥር ስርዓት መዘርጋት እንዳለባቸውም በአዋጅ ረቂቁ ላይ ሰፍሯል።
“ብቃት እና ውድድርን መሰረት ማድረግ” የሚለው አገላለጽ፤ አነስተኛ ብሔራዊ ተዋጽኦ ስላላቸው ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች በተጠቀሰበት የአዋጁ ክፍልም ተጠቅሷል። “በመንግስት መስሪያ ቤት የሚፈጸም የሰራተኛ ስምሪት፣ የብሔር ብሔረሰቦችንና ህዝቦች ሚዛናዊ ተዋጽኦ ለማሳደግ የሚያስችሉ እቅዶችን በመተግበር፣ ብቃት እና ውድድር መሰረት ተደርጎ መፈጸም አለበት” ሲል የአዋጅ ረቂቁ ያዝዛል።
ይህ አካሄድ “በተጨማሪ ድጋፍ” ጭምር ሊታገዝ እንደሚገባ በአዋጁ ላይ ሰፍሯል። “በመንግስት መስሪያ ቤቶች ውስጥ አነስተኛ ብሔራዊ ተዋጽኦ ያላቸው ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በቅጥር፣ በደረጃ ዕድገት፣ በዝውውር፣ በድልድል፣ በትምህርትና ስልጠና አፈጻጸም የተጨማሪ ድጋፍ እርምጃ ተጠቃሚ መሆን አለባቸው” ሲል የአዋጅ ረቂቁ ደንግጓል። ተጨማሪ የድጋፍ እርምጃን ጨምሮ የብዝሃነት፣ አካታችነትን በሚመለከት በአዋጁ የተዘረዘሩ ድንጋጌዎችን ለማስፈጸም፤ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ሊያወጣ እንደሚችልም ተመላክቷል።
የብዝሃነት እና አካታችነት ጉዳይ ከብሔረሰብ፣ ከጾታ እና ከአካል ጉዳተኝነት አንጻር ብቻ ሊታይ እንደማይገባ፤ በዛሬው የተወካዮች ምክር ቤት ስብሰባ አስተያየት ከሰጡ የፓርላማ አባል አንዱ የሆኑት አቶ ከድር እድሪስ አሳስበዋል። “አሁን ያሉ የፌደራል ተቋማት አደረጃጀት ስንመለከት በተለይ ደግሞ ከብዝሃነት አንጻር ሰፊ ጥያቄ የሚነሳበት ነው” ያሉት የፓርላማ አባሉ፤ ተቋማቱ “ኢትዮጵያን መምሰል እንዲችሉ” የሃይማኖት ብዝሃነት ጉዳይ ከግምት በአጽንኦት ሊታይ እንደሚገባ ጠቁመዋል።
“ብዝሃነት ሲጠቀስ ብዙ ጊዜ የብሔረሰብ ጉዳይ ይነሳል። የጾታ ጉዳይ ይነሳል። የአካል ጉዳተኝነት ጉዳይ ይነሳል። ከብዝሃነት አኳያ ግን በዋነኛነት የሃይማኖት ብዝሃነት የረቂቅ አዋጁ አካል መሆን አለበት። ስለዚህ [የአዋጁ ረቂቅ] የሚመራለት ቋሚ ኮሚቴ ይህንን አዋጅ በሚያይበት ጊዜ፤ የሃይማኖት ብዝሃነት በጣም አሳሳቢ ጉዳይ (serious issue) እየሆነ እየመጣ ስለሆነ እንዲያየው ለመግለጽ ነው” ሲሉ አቶ ከድር አስተያየታቸውን አጠቃልለዋል።
እንደ አቶ ከድር ሁሉ የረቂቅ አዋጁ በዚህ ጊዜ መዘጋጀት “በጣም ጠቃሚ” መሆኑን የገለጹት የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የፓርላማ ተወካዩ አቶ አበባው ደሳለው፤ ሆኖም የአካታችነት እና የሰራተኞች ስብጥር ጉዳይ “አተገባበር ላይ ችግር ሊፈጥር ይችላል” የሚለውን ስጋታቸውን በአስተያየታቸው አንጸባርቀዋል። ብሔር ብሔረሰቦች “እኩል መታየት አለባቸው” በሚለው ላይ እንደሚስማሙ የተናገሩት የፓርላማ አባሉ፤ ሆኖም አተገባበሩ በመንግስት ሰራተኛ መዋቅሩ ላይ “የሚያፋልስ ነገር” እንዳይኖር ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባ አስገዝበዋል።
“ብሔር ብሔረሰብን እናስተናግዳለን ስንል ጥንካሬያቸውን በማየት፣ ብቃታቸውን ባገናዘበ መልኩ ሊሆን ይገባል እንጂ ብሔራቸውን ብቻ ታይቶ ሰዎች ስራ ሊሰጣቸው አይገባም ወይም በተለያዩ ቦታዎች ሹመት ሊሰጣቸው አይገባም። ይሄ ‘ሜሬት’ የምንለውን ነገር እና ብቃትን ትልቅ ግምት ልንሰጠው ይገባል። ምክንያቱም ‘እንደ አንድ ሀገር ማሰብ አለብን፣ ለብሔራችን ብቻ ማሰብ የለብንም’ እያለ ብልጽግናም ራሱ ብዙ ጊዜ የሚናገረው ነው። እንደ ሀገርም ብዙ ጊዜ የሚባል ነገር ነው” ሲሉ አቶ አበባው አብራርተዋል።
“አንድ ሰው አቅሙ እያለው በብሔሩ ምክንያት ከደረጃው ዝቅ እንዳይል ወይም ከስራው እንዳይፈናቀል መስራት ይገባል” ያሉት እኚሁ ይሄ የፓርላማ አባል፤ የአዋጁ ረቂቁ የሚመራለት የፓርላማ ቋሚ ኮሚቴ ይህንን ከግምት ውስጥ እንዲያስገባ ማሳሰቢያ ሰጥተዋል። በዛሬው የተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ የተገኙት 239 የፓርላማ አባላት፤ የሰው ሀብት፣ ስራ ስምሪት እና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ረቂቅ አዋጁን በዝርዝር እንዲመለከተው የመሩት በሙሉ ድምጽ ነው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)