በኢትዮጵያ ያሉ ሁሉም የታጠቁ ኃይሎች “ጊዜያዊ ሀገር አቀፍ የተኩስ ማቆም” እንዲያደርጉ የአሜሪካ አምባሳደር ጠየቁ

በተስፋለም ወልደየስ

በኢትዮጵያ ያሉ ሁሉም የታጠቁ ኃይሎች “ጊዜያዊ ሀገር አቀፍ የተኩስ ማቆም” እንዲያደርጉ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኢርቪን ማሲንጋ ጥሪ አቀረቡ። ታጣቂዎቹ ትምህርት ቤቶች፣ የጤና ተቋማትን እና የውሃ መሰረተ ልማቶችን ኢላማ ማድረጋቸውን እንዲያቆሙም አምባሳደሩ አሳስበዋል።

በአምባሳደርነት ተሹመው ወደ ኢትዮጵያ ከመጡ ስምንት ወር የሞላቸው ማሲንጋ፤ ከእርሳቸው በፊት በነበሩ አምባሳደሮች ሲተገበር እምብዛም ያልታየውን ይፋዊ የፖሊሲ መልዕክት በዛሬው ዕለት አስደምጠዋል። አምባሳደሩ መልዕክታቸውን ለማስተላለፍ የመረጡት ታሪካዊው የአሜሪካን ግቢ፤ የንግግራቸው ማጠንጠኛ ከነበረው የሰብዓዊ መብት ጉዳይ ጋር ቁልፍ ተዛምዶ ያለው ነው።  

በአሁኑ ወቅት የየመን ማህበረሰብ ትምህርት ቤት አካል የሆነው የቀድሞው የአሜሪካ ቆንስላ ግቢ፤ በጣሊያን ወረራ ወቅት የየካቲት 12 ጭፍጨፋ ሲካሄድ 750 የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን ተሸሽገውበት የነበረ ነው። ማሲንጋ በንግግራቸው ወቅቱን ሲያስታውሱ፤ “በሺህዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ያለምንም ማስረጃ እና የህግ ሂደት “ኢላማ የተደረጉበት ነበር” ብለዋል። 

የአሜሪካው አምባሳደር ድሮ እና ዘንድሮን ባነጻጸረ ንግግራቸው፤ ወደ 20 ሺህ ገደማ ኢትዮጵያውያን ያለቁበት የጣሊያኑ ጭፍጨፋ ከተፈጸመ ከ87 ዓመታት በኋላ፤ በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች እና በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን “ተመሳሳይ ፍርሃትን መጋፈጣቸውን ቀጥለዋል” ብለዋል። ሽፍታዎች፣ የታጠቁ ቡድኖች፣ አንዳንዴም የመንግስት የጸጥታ ኃይሎች፤ በህይወት የመኖር፣ የሰብዓዊ ክብርን፣ መከበርን በመሰሉ መብቶች ላይ “ያለምንም ተጠያቂነት ጥሰቶች ይፈጽማሉ” ሲሉ ማሲንጋ በንግግራቸው ወንጅለዋል። 

ይህ አካሄድ “በህግ የመገዛት እና የህግ የበላይነትን ችላ ማለት የሚንጸባረቅበት” እንደሆነ የገለጹት አምባሳደሩ፤ በጦርነት እና ግጭት ወቅት እንኳ የሰብዓዊ መብቶች ሊረሱ እንደማይገቡ አሳስበዋል። “የሁሉም ሰው ክብር በተለይ ደግሞ የሰላማዊ ሰዎች ደህንነት፤ በግጭት ወቅቶች ሊጠበቁ ይገባል” ሲሉም ማሲንጋ አጽንኦት ሰጥተዋል። ይህ መርህ በአሁኑ ወቅት “ውስጣዊ ግጭት” በገጠማት በኢትዮጵያ ጭምር ሊከበር እንደሚገባውም አሳስበዋል።   

ሁሉም ሀገር “ራሱን የመከላከል ህጋዊ መብት አለው” ያሉት የአሜሪካው አምባሳደር፤ ሆኖም ሀገራት ራሳቸውን የሚከላከሉበት መንገድ “ያለምንም ጥርጥር የወደፊት ግጭቶችን አካሄድ የሚወስን” መሆኑን አስታውሰዋል። ሀገር የመከላከያ መንገዶቹ “በዛሬው እና በወደፊቱ የማህብረሰብ ትስስር” ላይ ይበልጡኑ ተጽዕኖ የሚያሳድር መሆኑን አስገንዝበዋል። የታጠቁ ወገኖች “የፖለቲካ ግቦቻቸውን ከውይይት ይልቅ በግጭት ለማሳካት” ሲሞክሩ፤ ለሚፈጸሙ በደሎች ሁኔታዎች የተመቻቹ እንደሚሆኑም አመልክተዋል። 

የታጠቁ ወገኖችን አካሄድ ለመግታት መንግስት የሚወስዳቸው እርምጃዎች “በፖለቲካ ምህዳር ላይ የማይካድ ተጽዕኖ” እንደሚያሳድር አምባሳደር ማሲንጋ በንግግራቸው ጠቁመዋል። በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች “ከፍርድ ውጪ የሚፈጸሙ ግድያዎች፣ የዘፈቀደ እስሮች፣ የአስገድዶ መሰወር፣ ከግጭት ጋር የተያያዙ ወሲባዊ ጥቃቶች” በተለያዩ ወገኖች መፈጸማቸውን የሚያትቱ ሪፖርቶች በሚወጡበት ጊዜ፤ እርሳቸውም ሆነ ባልደረቦቻቸው “ጥልቅ ሀዘን” እንደሚሰማቸው አምባሳደሩ ተናግረዋል። 

እነዚህ ድርጊቶች “በአስቸኳይ” መፍትሔ ሊሰጣቸው እና ተጠያቂነት ሊረጋገጥ እንደሚገባ ማሲንጋ አሳስበዋል። የአሜሪካው አምባሳደር “ተጠያቂነት ከሚረጋገጥባቸው መንገዶች” ውስጥ በምሳሌነት በንግግራቸው የጠቀሱት “እውነተኛ እና ግልጽ የሽግግር ፍትህ ሂደትን” ነው። በኢትዮጵያ የሽግግር ፍትህ ተግባራዊ እንዲሆን የሚያስችል የፖሊሲ ሰነድ ከአንድ ወር በፊት በሚኒስትሮች ምክር ቤት ከጸደቀ በኋላ ተግባራዊ መደረግ መጀመሩን የኢትዮጵያ መንግስት ማስታወቁ አይዘነጋም።  

እንደ ሽግግር ፍትህ ሁሉ በአምባሳደር ማሲንጋ ንግግር ተደጋግሞ የተነሳው የሀገራዊ ምክክር ጉዳይ ነው። በኢትዮጵያ ያሉ ታጣቂ ቡድኖች “ከጦር አውድማዎች ፈጣን ድል እንደማይገኝ” ተገንዝበው፤ ራሳቸውን ለውይይት እንዲያዘጋጁ አምባሳደሩ መክረዋል። በኢትዮጵያ በመካሄድ ላይ ያለው የሀገራዊ ምክክር ሂደት “ፍጽምና የጎደለው ቢሆንም”፤ ሁሉም ወገኖች የዕድሉ ተጠቃሚ መሆን እንደሚገባቸው ማሲንጋ አበክረው አስገንዝበዋል። 

የአሜሪካው አምባሳደር በአማራ፣ በኦሮሚያ እና በትግራይ ላይ ላሉ ተዋጊ ኃይሎች በውይይት እንዲሳተፉ በንግግራቸው ጥሪ ቢያቀርቡም፤ በሀገራዊ ምክክር ሂደቱም ሆነ በሽግግር ፍትህ ላይ የሚኖረውን “ወሳኝ ተሳትፎ” በተመለከተ የጠቀሱት ህወሓትን ነው። ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) በሂደቶቹ ላይ የሚኖረው ተሳትፎ ከትግራይ ክልል አልፎ ለኢትዮጵያ ሰላም እና መረጋጋት “ወሳኝ” እንደሆነ ማሲንጋ በንግግራቸው አመልክተዋል።

ከቀያቸው የተፈናቀሉ ሰዎችን ወደ መኖሪያቸው መመለስን ጨምሮ ሌሎችም እልባት ያላገኙ ጉዳዮችን በተመለከተ፤ ህወሓት “አካታች፣ ስርዓት የተሞላበት እና የሰዎችን ክብር የጠበቀ” አካሄድ እንዲከተል አምባሳደሩ መክረዋል። ይህ አካሄድ “ግዛቶችን በኃይል መልሶ መውሰድ” የሚለውን አማራጭ ሊያካትት እንደማይገባም አጽንኦት ሰጥተዋል። 

አምባሳደር ማሲንጋ በአማራ ክልል በውጊያ ላይ ለሚገኙ የፋኖ ኃይሎች ባስተላለፉት መልዕክት፤  “ውይይትን አንቀበልም ማለታቸው ለራሳቸውም እንደማይጠቅማቸው” ተናግረዋል። በአማራ ያሉ በርካታ ሰዎች “የቆሙለት ዓላማ ፍትሃዊ ነው” የሚል እምነት እንዳላቸው የጠቀሱት አምባሳደሩ፤ ይህንኑ “መከራከሪያቸውን” ከግጭት ይልቅ በውይይት ማቅረብ እንደሚገባቸው አሳስበዋል። ከዚህ በተቃራኒ በክልሉ ውጊያዎች የሚቀጥሉ ከሆነ ግን “በሌሎች የኢትዮጵያ ክፍሎች እንዳለው በውጤቱ የሚሰቃዩት ሰላማዊ ሰዎች መሆናቸውን” አክለዋል።   

የአሜሪካው አምባሳደር በዛሬው የፖሊሲ ንግግራቸው በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሱትን የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ተዋጊዎችንም አንስተዋል። የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ተወካዮች ከፌደራል መንግስት ጋር በታንዛንያ የሰላም ንግግር ሲያደርጉ መቆየታቸውን ማሲንጋ በበጎ እርምጃነት ጠቅሰዋል። የሰራዊቱ ተወካዮች በዳሬሰላም ድርድር ወቅት ከስምምነት ለመድረስ “እውነተኛ ጥረት” ማድረጋቸውንም አስታውሰዋል። የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ተዋጊዎች በድርድር “ተስፋ ሳይቆርጡ” “በድጋሚ መተማመንን ለመገንባት ጥረት” እንዲያደርጉ እና በህዝብ ዘንድ “ከፍተኛ ድጋፍ ያለውን ሰላም የማስፈን ሂደት” እንዲቀጥሉበት አሳስበዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)