የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአሜሪካ አምባሳደር ኢርቪን ማሲንጋ በትላንትናው ዕለት የሰጡትን የፖሊሲ መግለጫ “የተሳሳተ” እና “መረጃ የጎደለው” ሲል ነቀፈ። በሰብአዊ መብቶች እና በድርድር ጉዳይ ላይ ያተኮረው የአምባሳደሩ መግለጫ፤ “የኢትዮጵያ እና የአሜሪካንን ታሪካዊ እና ወዳጃዊ ግንኙነት የሚጻረር” እንደሆነ ሚኒስቴሩ ተችቷል።
አምባሳደር ኢርቪን ማሲንጋ ትላንት ረቡዕ ባስተላለፉት የፖሊሲ መልዕክት፤ በኢትዮጵያ ያሉ ሁሉም የታጠቁ ኃይሎች “ጊዜያዊ ሀገር አቀፍ የተኩስ ማቆም” እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበው ነበር። አምባሳደሩ አስር ደቂቃ ገደማ በረዘመ በዚሁ ንግግራቸው ትምህርት ቤቶች፣ የጤና ተቋማት እና የውሃ መሰረተ ልማቶች በታጣቂዎች ኢላማ ሊሆኑ እንደማይገባ አሳስበዋል።
ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዛሬ ሐሙስ ግንቦት 8፤ 2016 ባወጣው መግለጫ፤ የአምባሳደሩ መልዕክት በኢትዮጵያ መንግስት ላይ የተሰነዘሩ “ውንጀላዎችን የያዘ ነው” ብሎታል። የአሜሪካው አምባሳደር መልዕክት “መንግስት የሀገሪቱን ጉዳዮች እንዴት በተሻለ መንገድ መምራት እንዳለበት ያልተጠየቀ ምክር” ያካተተ እንደሆነ ሚኒስቴሩ በመግለጫው ወቅሷል።
መግለጫው “የተመረጠ መንግስትን በኃይል ለመገልበጥ የተነሱ” እና “ሰላማዊ ዜጎች በማጥላላት፣ በማፈን እና በማሸበር የሚታወቁ” ኃይሎችን የጠቀሰ እንደሆነ ጭምር ገልጿል። አምባሳደር ማሲንጋ በትላንቱ መግለጫቸው ከጠቀሷቸው ተዋጊ ኃይሎች መካከል የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት፣ የፋኖ ታጣቂዎች እና ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ይገኙበታል።
ማሲንጋ ተቀማጭነታቸውን በአዲስ አበባ ባደረጉ የአሜሪካ አምባሳደሮች ባልተለመደ መልኩ ጠጠር ያለ መልዕክት ያስተላለፉት፤ የሲቪል ማህበረሰብ ተወካዮች እና ሌሎችም ተጋባዥ እንግዶች ፊት ባደረጉት ንግግር ነው። አምባሳደሩ ሀገራቸው በኢትዮጵያ ላይ የምትከተለውን ፖሊሲ ይፋ ባደረጉበት የትላንቱ መርሃ ግብር ላይ ከተገኙ እንግዶች መካከል በአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ ልዩ ልዑክ ማይክ ሐመር ይገኙበታል።
ሐመር ወደ አዲስ አበባ የመጡት በፕሪቶሪያ በተፈረመው ግጭት የማቆም ስምምነት አተገባበር እና የኢትዮጵያ መንግስት እና ህወሓት ያልተስማሙባቸው ጉዳዮች በፖለቲካዊ ውይይት እንዲፈቱ ለመነጋገር መሆኑን የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ቀደም ሲል አስታውቆ ነበር። ልዩ ልዑኩ በአዲስ አበባ ቆይታቸው፤ በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች የሚካሄዱ ግጭቶች በውይይት እንዲቆሙ ዳግም ግፊት የማድረግ ሃሳብ ጭምር እንዳላቸው ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዛሬ ባወጣው መግለጫ፤ ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ጋር በበርካታ ጉዳዮች ላይ ውይይት ለማድረግ ዝግጁ መሆኗን አስታውቋል። ሁለቱ ሀገራት ሊወያዩባቸው የሚችሉ አጀንዳዎች በሚል በሚኒስቴሩ መግለጫ ከተጠቀሱት ጉዳዮች ውስጥ “ለሰላም እና ጸጥታ፣ ለሰብአዊ መብቶች መከበር እና ዴሞክራሲን ለማሳደግ ስለሚደረጉ ጥረቶች” የሚለው ይገኝበታል።
ሚኒስቴሩ በዚሁ መግለጫው፤ በአምባሳደር ማሲንጋ መልዕክት ተፈጥረዋል ያላቸውን “የሐቅ ስሕተቶች” እና “ጉድለቶችን” ለማረም በአዲስ አበባ ከሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ጋር እንደሚሰራ ጠቁሟል። የሀገሪቱን ሰላም እና ዲሞክራሲያዊ ሂደቶችን የማያዳክም እና ዲፕሎማሲያዊ መርሆዎችን የሚመጥኑ የተሻሉ መንገዶች የመጠቀም አካሄድን መከተል እንደሚሻልም ሚኒስቴሩ መክሯል።
ኢትዮጵያ ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር የእርስ በእርስ መከባበር የሰፈነበት የሁለትዮሽ ውይይት እና ግንኙነቷን ለመቀጠል ቁርጠኛ መሆኗንም ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በዛሬው መግለጫ ማጠቃለያ ላይ አመልክቷል። አሜሪካ እና ኢትዮጵያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ከጀመሩ ዘንድሮ 120 ዓመት ሞልቷቸዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)