ባለፈው ማክሰኞ ግንቦት 6፤ 2016 ለፓርላማ የቀረበው የፌደራል መንግስት ሰራተኞች የአዋጅ ረቂቅ በማሻሻያነት ካካተታቸው አንቀጾች መካከል “ገለልተኛ እና ነጻነት ያለው” የሲቪል ሰርቪስ አሰራር ስርዓትን በስራ ላይ ማዋል የሚለው ይገኝበታል። ይህን ስርዓት ተግባራዊ ማድረግ ያስፈለገው በሲቪል ሰርቪስ ውስጥ “መንግስታዊ እና ፖለቲካዊ ስራዎች የየራሳቸውን መስመር እንዲይዙ ለማድረግ” መሆኑን የአዋጅ ረቂቁን ለማብራራት የቀረበው ሰነድ አመልክቷል።
የመንግስት አገልግሎት እና አስተዳደር ፖሊሲ ባመላከተው አቅጣጫ መሰረት በአዋጁ እንዲካተት በተደረገው ድንጋጌ መሰረት፤ አንድ የመንግስት ሰራተኛ “በህዝብ ምርጫ አሸንፎ የሚመጣ ፓርቲ በሚመሰረተው መንግስት ውስጥ በብቃት እና በታማኝነት የሚሰራ” መሆን ይኖርበታል። የመንግስት መስሪያ ቤት በበላይነት የሚመራ ኃላፊም “በኢፌዲሪ ህገ መንግስት መሰረት መንግስት ያደራጀ የፖለቲካ ፓርቲ የሚሰጠውን የፖለቲካ ተልዕኮ አፈጻጻም የማረጋገጥ ኃላፊነት” ተጥሎበታል።
ሆኖም የበላይ ኃላፊው ይህን በሚያደርግበት ጊዜ “የመስሪያ ቤቱን አሰራር ሥርዓት እና የስራ ዕቅድ ከግምት በማስገባት ሚዛኑን በጠበቀ ሁኔታ መከናወኑን ማረጋገጥ” እንደሚጠበቅበት በአዋጅ ረቂቁ ላይ ሰፍሯል። የመንግስት አገልግሎት ዘርፍን ከፖለቲካ አስተዳደር ጉዳዮች ጋር “የመደበላለቅ ችግር” በአሁኑ ወቅት “በስፋት የሚታይ” መሆኑን አዋጁን ለማብራራት ለፓርላማ የቀረበው ሰነድም ይቀበላል።
“ይህን ስር የሰደደ ባህል በአንድ ጊዜ ተቆርጦ ይቅር ማለት ተግባራዊ ሊሆን የማይችል አቋም ሲሆን፤ በሌላ በኩል በዚህ አግባብ ይቀጥል ማለት በዘርፉ የታሰበው ተቋማዊ ለውጥ እንቅስቃሴ ተልዕኮዎችን እና እቅዶችን በተፈለገው መጠን፣ ጊዜ፣ ወጪ እና ጥራት ለማሳካት ያዳግታል” ሲል የአዋጅ ማብራሪያው ያስረዳል። “ስለሆነም አስቀድሞ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው የፖለቲካ ስራ አስፈጻሚ የሚያሳድረውን ጫናና ጣልቃ ገብነት መቀነስ እና ግንኙነታቸው የተመጣጠነ መስመር እንዲይዝ ማድረግ ይሆናል” ሲልም አጽንኦት ይሰጣል።
አዲሱ አዋጅ የመንግስት መስሪያ ቤቶች “ከፖለቲካ አስተዳደሩ ሙሉ ለሙሉ ነጻ ሊሆኑ ይገባል” የሚል አቋም እንደሌለው የአዋጁ ማብራሪያ ያትታል። “የፖለቲካ እና አስተዳደራዊ ጉዳዮች አንዳንድ ሀገራዊ ጉዳዮችን ከማስፈጸም አኳያ ሊለያይ የማይችል ግንኙነት ያላቸው መሆኑ ግምት እና ግንዛቤ ተወስዷል” ሲልም ያክላል።
“ድንጋጌው በዋናነት የመንግስት አገልግሎት ሥርዓቱ ከፖለቲካዊ አቅጣጫ፣ ጫና እና ጣልቃ ገብነት ነጻ መሆን ያለበት መሆኑን አጠቃላይ መርህ ሲያስቀምጥ፤ በተለዩ እና በሚታወቁ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ደግሞ ሚዛኑን የጠበቀ ግንኙነት እንዲኖራቸው ማድረግ ተገቢ መሆኑንም ግምት ውስጥ አስገብቶ ተደንግጓል” በማለት የአዋጅ ረቂቅ ማብራሪያው ያስገንዝባል። በዚሁ ድንጋጌ ላይ መንግስታዊ እና ፖለቲካዊ ስራዎች “የየራሳቸውን አሰራር ስርዓት ተከትለው ሳይቀላቀሉ የሚሰሩበትን አግባብ መከተላቸውን” ለማረጋገጥ የሚያስችል የማስፈጸሚያ ደንብ ወደፊት በሚኒስትሮች ምክር ቤት እንደሚወጣ ሰፍሯል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)