ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ስልጣን ከያዙ ወዲህ ለስድስተኛ ጊዜ የመከላከያ ሚኒስትራቸውን ቀየሩ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ ሰኞ ግንቦት 12 በሰጡት ሹመት፤ ከመስከረም 2014 ጀምሮ በመከላከያ ሚኒስትርነት ሲያገለግሉ የቆዩት ዶ/ር አብርሃም በላይ ከኃላፊነታቸው ተነስተው በአይሻ መሐመድ ተተክተዋል።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ስራ አስፈጻሚ የነበሩት አብርሃም፤ በመከላከያ ሚኒስትርነት የተሾሙት በ6ኛው አጠቃላይ ሀገራዊ ምርጫ ያሸነፈው የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ብልጽግና ፓርቲ መንግስት ሲመሰርት ነበር። አብርሃም የመከላከያ ሚኒስትር ከመሆናቸው በፊት የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ሆነው ሰርተዋል።
አብርሃም የመከላከያ ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት አሁን የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የደህንነት አማካሪ ሆነው በመስራት ላይ የሚገኙትን ዶ/ር ቀንዓ ያደታን ተክተው ነበር። በዛሬው ሹም ሽር አብርሃምን የተኩት የመስኖ እና ቆላማ አካባቢ ሚንስትሯ አይሻ መሐመድ ለኃላፊነቱ እንግዳ አይደሉም።
አይሻ ከጥቅምት እስከ ሚያዝያ 2011 ዓ.ም. ድረስ የመጀመሪያዋ የኢትዮጵያ ሴት የመከላከያ ሚኒስትር ሆነው ሰርተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ስልጣን በያዙ በጥቂት ወራት ልዩነት ካቢኔያቸውን ሲያዋቅሩ ሹመት ከተሰጣቸው 20 ሴቶች አንዷ የሆኑት አይሻ፤ የመከላከያ ሚኒስትርነትን የተረከቡት ከአቶ ሞቱማ መቃሳ ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ስልጣን ሲይዙ ለ10 ዓመታት ባገለገሉት አቶ ሲራጅ ፈጌሳ ምትክ የመጀመሪያቸውን የመከላከያ ሚኒስትር የሾሙት አቶ ሞቱማ መቃሳን ነበር። አቶ ሞቱማ በሚያዝያ 2010 በተሰጣቸው የመከላከያ ሚኒስትርነት ያገለገሉት ግን ለስድስት ወራት ገደማ ብቻ ነው።
በጥቅምት 2011 ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ካቤኒያቸውን ሲያዋቅሩ የኮንስትራክስሽን ሚኒስትር የነበሩት የምህንድስና ባለሙያዋ አይሻ መሐመድ አቶ ሞቱማ መቃሳን ተኩ። በመከላከያ ሚኒስትርነት አንድ ዓመት ለማይሞላ ጊዜ የሰሩት አይሻ በሚያዝያ 2011 ዓ.ም. በአቶ ለማ መገርሳ ተተክተው የከተማ ልማት እና የኮንስትራክሽን ሚኒስትር ሆነዋል። የአፋሯ ተወላጅ አይሻ ከዚህ ቀደም የባህል እና ቱሪዝም ሚኒስትርም ነበሩ።
አይሻ ወደ መከላከያ ሚኒስቴር የሚያዛውራቸው ሹመት እስከተሰማበት እስከ ዛሬው ዕለት ድረስ የመስኖ እና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር ሆነው ሲሰሩ ቆይተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ባለፈው ሳምንት የጎንደር ከተማ የውሃ እና መንገድ ፕሮጀክቶች አፈጻጸምን በጽህፈት ቤታቸው በገመገሙበት ወቅት ሪፖርት ካቀረቡ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች መካከል አንዷ አይሻ ነበሩ።
አይሻ በሚመሩት በመስኖ እና ቆላማ አካባቢ ሚኒስቴር ተቆጣጣሪነት ስራው እየተከናወነ ያለው የመገጭ መስኖ ግድብ ስራ ክፉኛ መጓተት፤ በጠቅላይ ሚኒስትሩ አለመወደዱ በባለፈው ሳምንት ግምገማ ወቅት ተስተውሏል። አብይ ግንባታው ከተጀመረ 11 ዓመት ያስቆጠረው የመገጭ መስኖ ግድብን የያዘው ኩባንያ ኮንትራክት በአንድ ሳምንት ውስጥ እንዲቋረጥ በወቅቱ አዝዘው ነበር።
ይህንንም ተከታትለው እንዲያስፈጽሙ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አይሻን በስም በመጥራት የስራ መመሪያ ማስተላለፋቸው አይዘነጋም። ለአራት ዓመታት የሚቆይ የመገጭ ግድብ የግንባታ ኮንትራት በ2001 ሲፈረም 2.4 ቢሊዮን ብር እንደነበር እና ግድቡ የሚጠይቀው ገንዘብ በአሁኑ ወቅት ወደ 6.4 ቢሊዮን ብር እንዳሻቀበ አይሻ በባለፈው ሳምንት ግምገማ ላይ አስረድተው ነበር።
ወደ 68 በመቶ የተጠጋውን የዚህን ግድብ ግንባታ አፈጻጸም በጥብቅ መከታተል፤ ከመከላከያ ሚኒስትርነት ወደ የመስኖ እና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትርነት የተዛወሩት የዶ/ር አብርሃም አንደኛው ስራ ይሆናል። ዶ/ር አብርሃም ከትላንት በስቲያ ቅዳሜ የመከላከያ ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን ፕሮጀክቶች የደረሱበትን ደረጃ ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ሲያስጎበኙ ታይተው ነበር። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)
[እርማት፦ ቀደም ሲል በነበረው ዘገባ “በስድስት ዓመት ውስጥ አራት ጊዜ ሹመት ተሰጥቷል” የሚለው “ስድስት ጊዜ” በሚለው ማስተካከያ ተደርጎበታል። በዘገባው ላይ ሌሎች መረጃዎችም ታክለዋል። በመረጃ አሰባሰብ ላይ ለተፈጠረው ስህተት ይቅርታ እንጠይቃለን።]