የትግራይ ኃይሎች በአላማጣ አቅራቢያ ከሚገኙ ሁለት አካባቢዎች እንዲወጡ መወሰኑን አቶ ጌታቸው ረዳ አስታወቁ 

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር በአላማጣ ከተማ አቅራቢያ በሚገኙት “ገርጃለ” እና “በቅሎ ማነቂያ” በተባሉ ቦታዎች ተሰማርተው የነበሩ የክልሉ ኃይሎችን ከአካባቢዎቹ ለማውጣት ወሰነ። አስተዳደሩ ከዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው፤ ከቀያቸው የተፈናቀሉ የትግራይ ተፈናቃዮች ወደ ነበሩበት ይመለሱ ዘንድ ለማድረግ ነገሮችን ለማቅለል መሆኑን አስታውቋል። 

የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ይህን ይፋ ያደረገው፤ በፕሬዝዳንቱ ጌታቸው ረዳ አማካኝነት ትላንት አርብ ግንቦት 16፤ 2016 ባስተላለፈው መልዕክት ነው። አቶ ጌታቸው ትላንት እኩለ ለሊት ገደማ በይፋዊ የማህበራዊ ትስስር ገጾቻቸው አማካኝነት ባሰፈሩት በዚሁ መልዕክት፤  የትግራይ ኃይሎች ከ“ገርጃለ” እና “በቅሎ ማነቂያ” መንደሮች እንዲወጣ የተወሰነው ጊዜያዊ አስተዳደሩ ከፌደራል መንግስት እና ከአማራ ክልል “አስተዳደር” ጋር የደረሰበትን መግባባት “ለማክበር” ነው።  

የአማራ እና ትግራይ ክልሎች የበላይ አመራሮች የተካተቱበት ብሔራዊ ኮሚቴ፤ ባለፈው መጋቢት ወር አጋማሽ ገደማ ካደረገው ስብሰባ በኋላ በ15 ነጥቦች ላይ ከመግባባት ላይ ደርሶ እንደነበር ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ ምንጮች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።  በሁለቱ ክልሎች መካከል “የወሰን ይገባኛል ጥያቄ የሚነሳባቸውን አካባቢዎች ጉዳይ ዘላቂነት ባለው መልክ እልባት ለመስጠት” የተቋቋመው ይህ ብሔራዊ ኮሚቴ፤ መግባባት ላይ ከደረሰባቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ የተፈናቃዮች ጉዳይ እንደሆነ ምንጮቹ ገልጸዋል።

“ሁለት ወር ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ” እንዲፈጸሙ በብሔራዊ ኮሚቴው እቅድ ከተያዘላቸው ጉዳዮች መካከል፤ “ተፈናቃዮችን ወደ ቀድሞ አካባቢያቸው መመለስ” የሚለው “ቀዳሚ ስራ” እንዲሆን በመጋቢቱ ስብሰባ ላይ ከስምምነት ላይ ተደርሶ ነበር። በዚሁ ስብሰባ ላይ “ሁሉም ተፈናቃይ ያለ ቅድመ ሁኔታ እንደሚመለስ፣ በወንጀል የሚታማ ካለም በሂደት እና በማስረጃ ፌደራል መንግስት የሚከታተለው ስለሚሆን ወደቀዬው ከመመለስ የሚያስተጓጉል ምክንያት እንደማይኖር” በስብሰባው ላይ ከመግባባት ላይ ተደርሶ እንደነበር ምንጮች አስረድተዋል። 

ተፈናቃዮች ወደ ቀድሞ አካባቢያቸው ከተመለሱ በኋላ “የተመላሾችን ተሳትፎ ያካተተ የአካባቢ አስተዳደር ከቀበሌ ጀምረው እንዲመርጡ” በመጋቢቱ ስብሰባ ላይ ከውሳኔ ላይ ተደርሶ እንደነበር ምንጮቹ ጨምረው ገልጸዋል። የቀበሌ ተወካዮች “በህዝብ ከተመረጡ” በኋላ “በተራቸው የወረዳ አመራር እንዲመርጡ” እንደሚደረግ፤ ለዚሁ ሂደት የሚያስፈልገው የአስመራጭ ኮሚቴ አባላት ምርጫ “በመከላከያ ሰራዊት አስተባባሪነት ታዛቢዎች ባሉበት” እንደሚካሄድ የስብሰባው ተሳታፊዎች ተግባብተው መለያየታቸውንም ምንጮቹ አክለዋል።

በሁለቱ ክልሎች የወሰን ይገባኛል ጥያቄ በሚነሳባቸው አካባቢዎች፤ “በአማራ ክልል የተመሰረቱ የአስተዳደር እና የጸጥታ መዋቅሮች እንዲፈርሱ” በዚህ ስብሰባ ላይ ከመግባባት ላይ ተደርሶ እንደነበር የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ምንጮቹ አመልክተዋል። ይህ ውሳኔ በፌደራል መንግስትም ሆነ በአማራ ክልል በኩል እስካሁን ድረስ ይፋዊ ማረጋገጫ ባይሰጥበትም፤ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ምክትል ፕሬዝዳንት ሌተናል ጄነራል ታደሰ ወረደ ባለፈው አንድ ወር ውስጥ በሰጧቸው ተደጋጋሚ መግለጫዎች ይህንኑ አረጋግጠዋል።

ሌተናል ጄነራል ታደሰ ባለፈው ሚያዝያ 8፤ 2016 ወር በሰጡት መግለጫ፤ “የመጀመርያው ምዕራፍ ታጣቂዎች እና አስተዳደሩ በማፍረስ ምቹ ሁኔታ መፍጠር ይሆናል። ከዚያ በኋላ ተፈናቃዮች የሚመለሱ ይሆናል። ትጥቅ ሲፈታ፣ አስተዳደር ሲፈርስ፤ የተያዘ የሚታረስ መሬት ወደ ባለቤቱ ሲመለስ፤ ተፈናቃዮች ይመለሳሉ” ማለታቸው ይታወሳል። የጊዜያዊ አስተዳደሩ ምክትል ፕሬዝዳንት በወቅቱ መግለጫውን የሰጡት፤ የአማራ እና የትግራይ ክልሎች በወሰን ይገባኛል ከሚወዛገቡባቸው ቦታዎች አንዱ በሆነው በራያ አካባቢ ለቀናት የቆዩ ውጊያዎች መካሄዳቸውን ተከትሎ ነው። 

ከእነዚህ ውጊያዎች በኋላ የትግራይ ኃይሎች “የተወሰኑ የራያ አካባቢዎችን መቆጣጠራቸውን” የሚገልጹ ዘገባዎች ተሰራጭተው ነበር። ሌተናል ጄነራል ታደሰ በሚያዝያ ስምንቱ መግለጫቸው፤ እነዚህን ዘገባዎች ውድቅ ማድረጋቸው አይዘነጋም። የአማራ ክልል መንግስት ከአንድ ቀን በኋላ ባወጣው መግለጫ ግን ህወሓት “የፕሪቶሪያውን ስምምነት ሙሉ በሙሉ በመጣስ” በክልሉ ህዝብ ላይ “አራተኛ ዙር ወረራ ፈጽሟል” ሲል ወንጅሏል። 

የክልሉ መንግስት ህወሓት “ወረራ ፈጽሞባቸዋል” በሚል በዚሁ መግለጫው የጠቀሳቸው፤ የራያ አላማጣ፣ ራያ ባላ፣ ኦፍላ፣ ኮረም እና ዛታ አካባቢዎችን ነው። እነዚህ አካባቢዎች “የማንነት ጥያቄ ያለባቸው ናቸው” ያለው የአማራ ክልል መንግስት፤ ህወሓት “የሀገሪቱ ሕገ መንግስት ከመጽደቁ በፊት በነበሩ አስተዳደራዊ መዋቅር እና አደረጃጀት በኃይል ጠቅልሎ ከመውሰድ ጀምሮ የዘር ማጥፋት ወንጀል እስከመፈጸም ድረስ አሰቃቂ ጥፋት የፈጸመባቸው አካባቢዎች  ናቸው” ሲል በሚያዝያ ወር መግለጫው አትቶ ነበር። 

ከዚህ መግለጫ ሁለት ሳምንት በኋላ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ምክትል ፕሬዝዳንት ሌተናል ጄነራል ታደሰ በሰጡት ሌላ መግለጫ፤ በደቡብ ራያ እና ጸለምት አካባቢዎች ተፈናቃዮችን እስከ ግንቦት 30፤ 2016 ድረስ ለመመለስ ከፌደራል መንግስት እና ከመከላከያ ሰራዊት ተወካዮች ጋር “ሙሉ መግባባት” ላይ መደረሱን አስታውቀዋል። ምክትል ፕሬዝዳንቱ በዚሁ መግለጫቸው፤ ከሁለቱ አካላት ጋር በተደረገ ስብሰባ ላይ የትግራይ ኃይሎች “ከአካባቢው እንዲወጣ ተግባብተናል፤ እናስወጣዋለንም” ሲሉ ተደምጠው ነበር።

እርሳቸው ይህን ካሉ አንድ ወር ከሚጠጋ ጊዜ በኋላ ነው እንግዲህ፤ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር በሁለቱ አካባቢዎች ያሉ የትግራይ ኃይሎችን እንደሚያስወጣ በይፋ ያስታወቀው። ለውሳኔው ምክንያት የሆነው የትግራይ ተወላጅ ተፈናቃዮችን ወደ ነበሩበት መመለስ፤ የፕሪቶሪያ የግጭት ማቆም ስምምነት አፈጻጸም አካል መሆኑን የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው በትላንቱ መልዕክታቸው ጠቅሰዋል። የትግራይ ተፈናቃዮችን የመመለስ ተመሳሳይ እንቅስቃሴዎችም “በሂደት ላይ” መሆናቸውን አስገንዝበዋል።

ከቀያቸው የተፈናቀሉ ሰዎችን ወደ መኖሪያቸው የመመለስ ጉዳይ ባለፈው ሳምንት በነበረው የአሜሪካ አምባሳደር የፖሊሲ መግለጫ ላይም ተነስቶ ነበር። አምባሳደር ኢርቪን ማሲንጋ ይህንን ጨምሮ ሌሎችም እልባት ያላገኙ ጉዳዮችን በተመለከተ፤ ህወሓት “አካታች፣ ስርዓት የተሞላበት እና የሰዎችን ክብር የጠበቀ” አካሄድ እንዲከተል መክረው ነበር። ይህ አካሄድ “ግዛቶችን በኃይል መልሶ መውሰድ” የሚለውን አማራጭ ሊያካትት እንደማይገባ አምባሳደሩ በወቅቱ አሳስበዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)