አዲሱ የሃይማኖት ጉዳዮች ረቂቅ አዋጅ የትኞቹን ተግባራት ይከለክላል?

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከወራት በፊት ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ውይይት ባደረጉበት ወቅት በተደጋጋሚ ከተነሱላቸው ጥያቄዎች መካከል የሃይማኖት ጉዳዮችን የተመለከቱት ይገኙበታል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወቅቱ በሰጡት ምላሽ መንግስታቸው ይህንኑ የሚመለከት ህግ በቅርቡ እንደሚያወጣ አስታውቀው ነበር። 

አብይ ከአማራ ክልል የተወጣጡ ተወካዮችን ባለፈው የካቲት ወር በጽህፈት ቤታቸው ባወያዩበት ስብሰባ “ሃይማኖትን በሚመለከት ህግ እናወጣለን። ሃይማኖት እና መንግስት ተለያይተው ስራቸውን ይሰራሉ። በቅርቡ ህጉ እንደሚጸደቅ ተስፋ ይደረጋል። ያኔ ሁሉም በህግ ይሰራል። አሁን ተቀላቅሏል። ያልተቀላቀለ ጉድ የለም። እንደዚያ አይቻልም” ሲሉ ተደምጠው ነበር። 

“በእስላም ተቋም ውስጥ ሆኖ ፖለቲካ ማራመድ ትክክል አይደለም። ያ ግለሰብ ፖለቲካ ካሰበ ችግር የለበትም። እምነቱን በግል እየተከተለ፤ ፖለቲካውን ደግሞ ከፓርቲ ጋር ማራመድ ይችላል። ያ ካልሆነ በስተቀረ ይበልጥ ጥፋት ስለሚያመጣ እኛም በዚህ አግባብ ብናየው፤ መንግስትም እንደ መንግስት እንዲሰራ ብንፈቅድ ለሁላችን ይጠቅማል” ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወቅቱ አሳስበዋል።    

ከእርሳቸው ገለጻ ሁለት ወራት በኋላ በሰላም ሚኒስቴር የተዘጋጀው “የሃይማኖት ጉዳዮች አዋጅ” ረቂቅ ሰነድ፤ ይህንኑ የሚያስተጋቡ አንቀጾች በውስጡ ይዟል። ለሃይማኖት ተቋማት “የተከለከሉ ተግባራትን” በሚዘረዝረው የአዋጁ ክፍል፤ ተቋማቱ “ሃይማኖትን ሽፋን አድርጎ በሚፈጸም ወንጀል ወይም ለማህበረሰቡ ሰላምና ጸጥታ ስጋት በሆነ እንቅስቃሴ እና ተግባር መሳተፍ ወይም መደገፍ” እንደማይችሉ ተደነግጓል።

የሃይማኖት ተቋማቱ “ከህዝብ ደህንነት፣ ሰላም፣ ጤና፣ ትምህርት እና ሞራል እንዲሁም የዜጎችን መሰረታዊ መብትና ነጻነቶች ተጻራሪ የሆኑ ተግባራትን ከመፈጸም” መቆጠብ እንዳለባቸውም በአዋጅ ረቂቁ ላይ ተቀምጧል። አዲሱ አዋጅ የሃይማኖት ተቋማት “በሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር መሳተፍ እና መተላለፊያ መሆን” እንደሌለባቸውም ያትታል።

በስድስት ክፍሎች እና በ32 አንቀጾች በተከፋፈለው በዚህ የአዋጅ ረቂቅ ከተካተቱ “ክልከላዎች” መካከል፤ “የሃይማኖት ተቋማት ከተቋቋመበትና ከተመዘገበበት ሃይማኖታዊ ዓላማ ውጭ መንቀሳቀስ” የሚለው አንዱ ነው። የሃይማኖት ተቋማት “የሌላውን ሃይማኖት ማናናቅ፣ መስደብ፣ ማዋረድ፣ በአማኞች መካከል ግጭትን ሊያስነሱ የሚችሉ መልዕክቶችን በማናቸውም መንገድ ማስተላለፍ” እንደማይችሉ የሚከለክለው ንዑስ አንቀጽ ሌላኛው ነው።   

አዲሱ አዋጅ የሃይማኖት ተቋማት “በሕግ በተከለከሉ ቦታዎች ሃይማኖታዊ ቅስቀሳዎችን” እንዳያካሄዱም ይከለክላል። የሃይማኖት ተቋማቱ “በመንግስት ተቋማት፣ በመንግስታዊም ሆነ በግል መደበኛ የትምህርት ተቋማት ሃይማኖታዊ ሰበካ ወይም ቅስቀሳ ማድረግ” እንደማይችሉም በአዋጅ ረቂቁ ላይ ተቀምጧል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)