የሀገራዊ ምክክር የአጀንዳ ማሰባሰብ ምዕራፍ፤ በአዲስ አበባ ከተማ ደረጃ በዛሬው ዕለት በይፋ ተጀመረ 

በተስፋለም ወልደየስ

የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍን፤ በአዲስ አበባ ከተማ ደረጃ ዛሬ ረቡዕ ግንቦት 21፤ 2016 በይፋ አስጀመረ። የአዲስ አበባው ምክክር፤ የሚካሄድበት የጊዜ ሰሌዳ ገና ላልተወሰነለት ለመጪው ሀገር አቀፍ የምክክር ጉባኤ “ቁልፍ ሚና ይኖረዋል” ተብሎለታል።

በታህሳስ 2014 ዓ.ም. በአዋጅ የተቋቋመው የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ስራዎቹን ሲያከናወን የቆየው፤በአራት ምዕራፎች ከፋፍሎ ነው። የቅደመ ዝግጅት እና የዝግጅት የስራ መርሃ ግብር ምዕራፎችን ያጠናቀቀው ኮሚሽኑ፤ ዛሬ ያስጀመረው የምክክር ምዕራፍ እና በስተመጨረሻ የሚያከናውነው የምክክር ውጤቶችን የመተግበሪያ ምዕራፍ ይቀሩታል።

ኮሚሽኑ በአዲስ አበባ ከተማ ደረጃ የምክክር ምዕራፉን ባስጀመረበት የዛሬው ስነ ስርዓት ላይ፤ ከአዲስ አበባ ከተማ 119 ወረዳዎች በተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተወከሉ ተሳታፊዎች ተገኝተዋል። ተሳታፊዎቹ የወከሏቸው የህብረተሰብ ክፍሎች፤ የመንግስት እና የግል ተቋማት ሰራተኞች፣ መምህራን፣ የንግዱ ማህበረሰብ፣ ወጣቶች፣ ሴቶች፣ ተፈናቃዮች፣ የተገለሉ ማህበረሰቦች እና የህብረተሰብ መሪዎችን መሆኑን ከኮሚሽኑ የተገኘ መረጃ ያመለክታል።  

ቁጥራቸው ከሁለት ሺህ በላይ የሚልቀው እነዚህ ተሳታፊዎች፤ በቀጣይ ሶስት ቀናት ለሀገር አቀፍ ጉባኤ የሚሆኑ የአጀንዳ ሀሳቦች ላይ ምክክር ያደርጋሉ። በሀገር አቀፍ የምክክር ጉባኤ ላይ አዲስ አበባን ወክለው የሚሳተፉ ተወካዮችንም ይመርጣሉ።

የህብረተሰብ ክፍል ተወካዮቹ በቡድን በመከፋፈል በሚያደርጓቸው ምክክሮች ላይ ከሚወያዩባቸው ርዕሰ ጉዳዮች መካከል፤ “የግጭቶች መነሻ ዋና ዋና ምክንያቶች ምንድናቸው?” የሚለው ይገኝበታል። በኢትዮጵያ ውስጥ “ያሉ እና የነበሩ ዋና ዋና ችግሮች” እና “የችግሮቹ መሰረታዊ መንስኤዎች ምንድናቸው?” የሚለውም ሌላው ለውይይት የተመረጠ ርዕሰ ጉዳይ ነው።  

በእነዚህ እና በሌሎች ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የሚደረጉ የቡድን ውይይቶች ውጤት፤ ለህብረተሰብ ክፍል ተወካዮች የጋራ መድረክ ላይ ከቀረበ በኋላ ለሀገር አቀፍ የምክክር ጉባኤ በአጀንዳ ግብዓትነት ይውላሉ። በዚህ ምክክር የሚለዩ አጀንዳዎችን፤ በቀጣይ በሚከናወነው የሀገር አቀፍ ጉባኤ “አጀንዳ ቀረጻ” ወቅት እንዲካተቱ የማድረግ ኃላፊነት ያለበት የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ነው።

ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ይህንኑ ኃላፊነቱን “በአግባቡ የሚወጣ መሆኑን”፤ የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ ለአዲስ አበባ ከተማ ተወካዮች ማረጋገጫ ሰጥተዋል። ፕሮፌሰር መስፍን በዛሬው የመክፈቻ ስነ ስርዓት ላይ ባሰሙት ንግግር የምክክሩ ተሳታፊዎች የተጣለባቸውን “ታላቅ እና ታሪካዊ ኃላፊነት መወጣት መቻላቸው”፤ በሀገሪቱ በአሁኑ ወቅት ያሉ ወቅታዊ ችግሮችን “ዘላቂ በሆነ መንገድ ለመፍታት” የሚደረገው ጥረት በስኬት እንዲቋጭ “ወሳኝ ጉዳይ” መሆኑንም አስረድተዋል።

“በሚገባ የሚተዋወቁ ህዝቦች ይከባበራሉ፣ ይተሳሰባሉ፣ እርስ በእርሳቸው በእኩልነት ይተያያሉ። በሀገራቸውም እኩል ይሆናሉ። ማንኛውም ችግር የሚፈታው በሃሳብ ልዕልና መሆኑን ተረድተው የጉልበት ወይም የማስገደድ መፍትሔ ጊዜያዊ መሆኑን በመረዳት ሁሉንም አሸናፊ የሚያደርገውን ምክክር በመርህ ደረጃ ይይዛሉ” ያሉት ዋና ኮሚሽነሩ፤ ዛሬ በአዲስ አበባ ደረጃ የተጀመረው የምክክር ሂደት “በቀጣይ ለሚከናወነው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ስኬታማነት ቁልፍ ሚና ይኖረዋል” ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል።

በአዲስ አበባው የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ሂደት የሚሳተፉ ተወካዮች “ከሌሎች ባለድርሻ አካላት እኩል አሻራቸውን የሚያሳርፉበት” መሆኑን ፕሮፌሰር መስፍን አስገንዝበዋል። ከዛሬ ጀምሮ ለተከታታይ ሰባት ቀናት የሚካሄደውን የአዲስ አበባውን የምክክር መድረክ ዋና ኮሚሽነሩ “ታሪካዊ” ሲሉ በንግግራቸው ገልጸውታል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)