ዜጎች ከሀገር እንዳይወጡ የማገድ ስልጣንን ለኢሚግሬሽን መስሪያ ቤት ኃላፊ የሚሰጥ የአዋጅ ማሻሻያ ለፓርላማ ቀረበ  

በተስፋለም ወልደየስ

ማንኛውንም ሰው ከሀገር ውስጥ እንዳይወጣ የማገድ ስልጣንን፤ የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት መስሪያ ቤትን በዋና ዳይሬክተርነት ለሚመራ ኃላፊ የሚሰጥ የአዋጅ ማሻሻያ ለፓርላማ ቀረበ። የአዋጅ ማሻሻያው፤ በህገ ወጥ መንገድ በኢትዮጵያ የሚኖሩ የውጭ ሀገር ዜጎች “በጥቁር መዝገብ እንዲመዘግቡ እና ከሀገር እንዲወጡ” የሚያስችል “አስተዳደራዊ ቅጣት” የመጣል ስልጣንን ለኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት መስሪያ ቤት ይሰጣል።

እነዚህን አዲስ ድንጋጌዎች ያካተተው የኢሚግሬሽን አዋጅ ማሻሻያ ለፓርላማ የተላለፈው፤ ከሁለት ሳምንት በፊት በተካሄደው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ስብሰባ ቀርቦ ከጸደቀ በኋላ ነው። በ1995 ዓ.ም. የጸደቀውን ነባሩን አዋጅ ማሻሻል ካስፈለገባቸው ምክንያቶች መካከል፤ መሰረታዊ ከሆኑ መብቶችን አንዱ የሆነውን “የመዘዋወር ነጻነትን ለማስከበር” እና የኢሚግሬሽን አገልግሎቶችን ለኢትዮጵያውያንና ለውጭ ሀገር ዜጎች “በተሻለ ጥራትና ቅልጥፍና መስጠት እንዲቻል” መሆኑን የሚኒስትሮች ምክር ቤት በወቅቱ አስታውቆ ነበር።

ሀገራት “ሉዓላዊ ስልጣንን” ተግባራዊ ከሚያደርጉባቸው ህጎች “በዋነኛነት” የሚጠቀስ ነው የሚባልለት የኢሚግሬሽን ህግ፤ “በህግ የተከለከሉ ሰዎች በህገ ወጥ መንገድ ከሀገር እንዳይወጡ እና ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገቡ ቁጥጥር የሚደረግበትን አግባብ” የሚደነግግ ነው። በስራ ላይ ከዋለ 21 ዓመት የሞላው ነባሩ ህግ፤ “ከኢትዮጵያ እንዳይወጡ ስለሚታገዱ ሰዎች” እና “ከኢትዮጵያ እንዲወጡ ስለሚደረጉ የውጭ ሀገር ሰዎች” ድንጋጌዎችን አስቀምጧል።

በነባሩ ህግ መሰረት “ማንኛውም ሰው ከኢትዮጵያ እንዳይወጣ ሊታገድ የሚችለው በህግ መሰረት በፍርድ ቤት ሲታዘዝ ብቻ ነው” ይላል። ዛሬ ለፓርላማ የቀረበው የአዋጅ ማሻሻያ በነባሩ ህግ የተቀመጠውን የፍርድ ቤት “ብቸኛ ስልጣን” የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት መስሪያ ቤትን በዋና ዳይሬክተርነት ለሚመራ ኃላፊ በተጨማሪነት ያጋራ ሆኗል። 

“የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር ከሚመለከታቸው የደህንነት አገልግሎት እና ህግ አስከባሪ አካላት ከሚያገኘው መረጃ ወይም አገልግሎቱ በራሱ ከሚያገኘው መረጃ በመነሳት፤ በብሔራዊ ጥቅም እና ደህንነት ላይ ሊቀለበስ የማይችል ግልጽና ድርስ የሆነ ከፍተኛ ጉዳት የሚያስከትል ሁኔታ መኖሩን ሲያምን፤ ማንኛውም ሰው ከሀገር እንዳይወጣ ማገድ ይችላል” ሲል የአዋጅ ማሻሻያው ደንግጓል። 

ዜጎች ከሀገር እንዳይወጡ የማገድ ስልጣን ላይ ማሻሻያ የተደረገው፤ በነባሩ ድንጋጌ ምክንያት እየደረሰ ያለውን “ከፍተኛ ጉዳት” ለመቅረፍ መሆኑን ለፓርላማ የቀረበው የረቂቅ አዋጁ ማብራሪያ ያስረዳል። አሁን በስራ ላይ ባለው አዋጅ መሰረት “ከፍርድ ቤት የእግድ ትዕዛዝ እስኪገኝ ድረስ በብሔራዊ ጥቅም እና ደህንነት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደረሱ ወይም ሊያደርሱ የሚችሉ ሰዎች ከሀገር እየወጡ ከተጠያቂነት እያመለጡ በሀገራችን ብሔራዊ ጥቅም እና ደህንነት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሱ” መሆኑን የረቂቅ አዋጁ ማብራሪያ አስገንዝቧል። 

“ከፍርድ ቤት የእግድ ትዕዛዝ እስኪገኝ ድረስ በብሔራዊ ጥቅም እና ደህንነት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደረሱ ወይም ሊያደርሱ የሚችሉ ሰዎች ከሀገር እየወጡ ከተጠያቂነት እያመለጡ በሀገራችን ብሔራዊ ጥቅም እና ደህንነት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሱ [ነው]”

– የኢሚግሬሽን አዋጅ ማሻሻያ ማብራሪያ

የአዋጅ ማሻሻያው፤ ለኢሚግሬሽን መስሪያ ቤት ዋና ዳይሬክተር “ማንኛውንም ሰው ከሀገር እንዳይወጣ ማገድ እንዲችል ቢፈቅድም”፤ “ያለአግባብ የሰዎችን የመንቀሳቀስ መብት እንዳይገድብ” ተጨማሪ ድንጋጌ እንዲካተት መደረጉ በማብራሪያው ተመላክቷል። የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት “ከሀገር እንዳይወጣ ያገደውን ሰው ይዞ የሚያቆይ ከሆነ ፍርድ ቤት መቅረቡን ማረጋገጥ አለበት” ሲል የአዋጅ ማሻሻያው ደንግጓል። 

የኢፌዲሪ ሕገ መንግስት አንቀጽ 32 “ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ወይም በሕጋዊ መንገድ ሀገሪቱ ውስጥ የሚገኝ የውጭ ዜጋ በመረጠው የሀገሪቱ አካባቢ የመዘዋወርና የመኖሪያ ቦታ የመመስረት፤ እንዲሁም በፈለገው ጊዜ ከሀገር የመውጣት ነጻነት አለው” ይላል። ነባሩ የኢሚግሬሽን አዋጅ “ከኢትዮጵያ የሚወጣ ማንኛውም ሰው፤ የጸና የጉዞ ሰነድ፣ የማይስፈልግ ካልሆነ በቀር ወደ ሚሄድበት ሀገር ለመግባት የሚያስችል ቪዛ እና እንዳስፈላጊነቱ የጤና ምስክር ወረቀት መያዝ” እንደሚኖርበት ያስቀምጣል።

በዛሬው የተወካዮች ምክር ቤት ስብሰባ ዝርዝር ዕይታ እንዲደረግበት ለፓርላማው የውጭ ግንኙነት እና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የተመራው የኢሚግሬሽን አዋጅ ማሻሻያ አዲስ ካካተታቸው አንቀጾች መካከል “አስተዳደራዊ ቅጣትን” የሚመለከተው ይገኝበታል። አስተዳደራዊ ቅጣት የመጣል ስልጣን እንዲካተት የተደረገው፤ በኢትዮጵያ በህገ ወጥ መንገድ ከሚኖሩ የውጭ ሀገር ዜጎች ጋር በተያያዘ መሆኑን የአዋጅ ማሻሻያውን ለማብራራት ለፓርላማ የቀረበው ሰነድ ያመለክታል።    

“ከጊዜ ወደ ጊዜ በህገ ወጥ መንገድ በሀገራችን ውስጥ የሚኖሩ የውጭ ሀገር ዜጎች እየተበራከቱ፤ በህገ ወጥ ድርጊቶች እየተሳተፉ ከፍተኛ ችግር እየፈጠሩ በመሆኑ በአስተዳደራዊ ቅጣት በመቅጣት ከህገ ወጥ ድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ማድረግ አስፈላጊ ስለሆነ ነው” ሲል የአዋጅ ማብራሪያው ያስረዳል። በዚህ መልክ በኢትዮጵያ የሚንቀሳቀሱ የውጭ ሀገር ዜጎችን “በጥቁር መዝገብ እንዲመዘገቡ እና ከሀገር እንዲወጡ ማድረግ ወደ ህጋዊ ስርዓት እንዲመጡ በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ሚና” እንዳለውም ማብራሪያው አክሏል። 

በዚህም መሰረት የሚኒስትሮች ምክር ቤት በሚያወጣው ደንብ አማካኝነት፤ የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት መስሪያ ቤት አስተዳደራዊ ቅጣት እንዲጥል በአዋጅ ማሻሻያው ስልጣን ተሰጥቶታል። “ይህን አዋጅ አሊያም በዚህ አዋጅ መሰረት የወጣ ደንብ ወይም መመሪያን የጣሰ ማንኛውም ሰው፤ የሚኒስትሮች ምክር ቤት በሚያወጣው ደንብ መሰረት አስተዳደራዊ እርምጃ ይወሰድበታል” ሲል የአዋጅ ማሻሻያው ደንግጓል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)