ባለፉት 9 ወራት ከማዕድናት ሽያጭ ማሳካት የተቻለው ገቢ፤ ለበጀቱ ዓመቱ ከታቀደው 56 በመቶ ብቻ መሆኑ ተገለጸ

ኢትዮጵያ በ2016 በጀት ዓመት ለውጭ ገበያ ከምታቀርባቸው ማዕድናት 514 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት ብታቅድም፤ የበጀት ዓመቱ ሊጠናቀቅ ሶስት ገደማ ወራት ብቻ በቀሩት በዚህ ጊዜ ማሳካት የቻለችው 56 በመቶ ብቻ መሆኑ ተገለጸ። ሀገሪቱ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከወርቅ ያገኘችው የውጭ ምንዛሬ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ83 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱም ተነግሯል።

የማዕድን ሚኒስትሩ አቶ ሀብታሙ ተገኝ የመስሪያ ቤታቸውን የስራ አፈጻጸም ሪፖርት ዛሬ ሐሙስ ግንቦት 22፤ 2016 ለፓርላማ ባቀረቡበት ወቅት እንዳሉት፤ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከቀረበ የወርቅ ምርት 274 ሚሊዮን ዶላር ተገኝቷል። በእነዚህ ወራት ለብሔራዊ ባንክ ከገባው 3.023 ቶን የወርቅ ምርት ውስጥ አብዛኛውን ያቀረቡት በወርቅ ማውጣት የተሰማሩ ኩባንያዎች መሆናቸውን ሚኒስትሩ ተናግረዋል። 

ይህ የወርቅ ምርት መጠን ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር “የ12.6 በመቶ ብልጫ ያሳየ መሆኑንም” አቶ ሀብታሙ አስታውቀዋል። የኢትዮጵያ የወርቅ ምርት ባለፉት ሁለት ዓመታት ገደማ “በከፍተኛ መጠን መቀነሱ” በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቋሚ ኮሚቴ ስብሰባዎች ወቅት ጥያቄ ሲያነሳ መቆየቱ ይታወሳል።

የፓርላማው የኢንዱስትሪ እና ማዕድን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባለፈው ህዳር ወር በጠራው ስብሰባ ላይ የተገኙት የማዕድን ሚኒስትሩ፤ በ2016 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሶስት ወራት ከወርቅ ሽያጭ የተገኘው ገቢ “አጥጋቢ አይደለም” ብለው ነበር። በመጀመሪያው ሩብ ዓመት በከፍተኛ ወርቅ አምራቾች ደረጃ ለማምረት ታቅዶ የነበረው 996.1 ኪሎ ግራም ወርቅ እንደነበር በወቅቱ የጠቀሱት ሚኒስትሩ፤ አጠቃላይ አፈጻጸሙ በመቶኛ ሲሰላ 72.2 በመቶ እንደሆነ ለቋሚ ኮሚቴ አባላቱ አስረድተው ነበር። 

ሚኒስትሩ ከመንፈቅ በኋላ በፓርላማ ሲገኙ፤ በኩባንያዎች የተመረተው የወርቅ መጠን በዘጠኝ ወራት ውስጥ 2.4 ቶን መድረሱን ገልጸዋል። በዚሁ ጊዜ ውስጥ ወርቅን ጨምሮ ከማዕድናት የተገኘው አጠቃላይ ገቢ 289 ሚሊዮን ዶላር መሆኑንም ተናግረዋል። ኢትዮጵያ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ውስጥ ለዓለም ገበያ ካቀረበቻቸው ማዕድናት ውስጥ የጌጣ ጌጥ 79.55 ቶን በማስመዝገብ በመጠን ከፍተኛውን ቦታ ይዟል። 

በመጠን በሁለተኛነት የሚከተለው፤ 69.8 ቶን ያህል ወደ ውጭ የተላከው የታንታለም ኦር ማዕድን ነው። ሀገሪቱ በዚሁ ወቅት ውስጥ 32,141 ቶን የኢንዱስትሪ ማዕድናት፣ 19.9 ቶን ጥሬ እና እሴት የተጨመረበት ኦፓል እንዲሁም 11, 176.4 ቶን ሊቲየም ለውጭ ገበያ ማቅረቧን የማዕድን ሚኒስቴር ሪፖርት ያመለክታል። 

ፎቶ፦ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

በዛሬው የፓርላማ መደበኛ ስብሰባ ላይ፤ “የማዕድን ዘርፉ ዋነኛ ችግሮች” ሲሉ ሚኒስትሩ የጠቀሷቸው የጸጥታ ችግር እና ፈቃድ የተሰጣቸው ኩባንያዎች አቅም ማነስ የሚሉ ናቸው። ማዕድናት “በተለይ ወርቅ ያለባቸው አካባቢዎች አብዛኞቹ የግጭት አካባቢዎች ሆነው ቆይተዋል” ያሉት አቶ ሀብታሙ፤ ይህን ችግር ለመቅረፍ ሚኒስቴር መስሪያ ቤታቸው ከጸጥታ ተቋማት ጋር በመተባበር ስራዎችን መጀመሩን ገልጸዋል።

አንዳንድ ኩባንያዎች የማምረት አቅም እንዳላቸው ሳይረጋገጥ ፈቃድ ስለተሰጣቸው “ማምረት አይችሉም” ሲሉ የተደመጡት ሚኒስትሩ፤ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እንደዚህ አይነት “ችግር አለባቸው” ላላቸው የመንግስት እና የግል ኩባንያዎች “ማስጠንቀቂያ” መስጠቱን አስታውቀዋል። “እርምት ወስደናል። ውልም እያቋረጥን ነው” ሲሉም አቶ ሀብታሙ አክለዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)