የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች የመንገደኞችን ቅድመ ጉዞ እና ስም ዝርዝር፤ ለኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት መስሪያ ቤት ከሶስት ሰዓት በፊት እንዲያሳውቁ ግዴታ የሚጥል አዋጅ ለተወካዮች ምክር ቤት ቀረበ። በአጓጓዦች ላይ ይህ ግዴታ በአዋጅ መጣሉ፤ “የሚፈለጉ አደገኛ ወንጀለኞች” እና “ሽብርተኞች” ጉዳት ሳያደርሱ በቁጥጥር ስር ለማዋል “ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል” ተብሏል።
ይህን ግዴታ ጨምሮ ሌሎችም አዳዲስ አንቀጾችን ያካተተው የኢሚግሬሽን አዋጅ ማሻሻያ ለፓርላማ የቀረበው ትላንት ሐሙስ ግንቦት 22፤ 2016 ነው። በ1995 ዓ.ም. የወጣውን የኢሚግሬሽን አዋጅ ለማሻሻል ካስፈለገባቸው ምክንያቶች “አንዱ የተቀናጀ ድንበር ቁጥጥር አስተዳደርን” አስመልክቶ ዓለም አቀፉ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት (ICAO) ተግባራዊ ካደረገው መመሪያ ጋር የኢትዮጵያን ስርዓት ማጣጣም በማስፈለጉ ምክንያት መሆኑ ተገልጿል።
የዓለም አቀፉ ድርጅቱ ተግባራዊ ያደረገው መመሪያ፤ ሀገራት የመንገደኛ ቅደመ ጉዞ መረጃ እና ምዝገባ ስርዓትን እንዲዘረጉ የሚያስገድድ ነው። ኢትዮጵያ የዚህ መመሪያ ፈራሚ ከሆኑ ሀገራት መካከል አንዷ በመሆኗ፤ ይህንኑ ስርዓት በኢሚግሬሽን ማሻሻያ አዋጅ ላይ እንዲካተት መደረጉ በአዋጅ ማብራሪያው ላይ ተመልክቷል።
በዚህ መሰረት “ማንኛውም አጓጓዥ መንገደኛን ወደ ሀገር ለማስገባት ወይም ከሀገር ለማስወጣት ከማጓጓዙ ከሶስት ሰዓት በፊት፤ የመንገደኛውን ቅድመ ጉዞ መረጃ እና ስም ዝርዝር ለኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት መስሪያ ቤት የማሳወቅ ወይም የመላክ” ግዴታ እንዲኖራቸው ተደርጓል። “ይህ መሆኑ መረጃውን በመለዋወጥ የሚፈለጉ አደገኛ ወንጀለኞች በተለይም ሽብርተኞችን ጉዳት ሳያደርሱ በቁጥጥር ስር በማዋል ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል” ሲል የአዋጁ ማብራሪያ ያስገንዝባል።
“ሀገርን የደህንነት ስጋት ላይ የሚጥሉ ሰዎች ከአየር ጉዞ ውጪ ሌሎችም የትራንስፖርት ዘዴዎች ሊጠቀሙ የሚችሉ መሆኑን ታሳቢ በማድረግ”፤ ለሌሎች አጓጓዦችም የሚሆን አንቀጽ በአዋጅ ማሻሻያው ላይ እንዲካተት መደረጉ በማብራሪያው ላይ ሰፍሯል። “ማንኛውም ከአየር ትራንስፖርት አገልግሎት ውጭ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጥ አጓጓዥ፤ በሀገራት መካከል በሚኖር በእንካ ለእንካ መርህ ወይም በሚደረግ ስምምነት መሰረት፤ የመንገደኞችን ቅድመ ጉዞ መረጃ እና ስም ዝርዝር ወደሚሄድበት አገር ከመውሰዱ በፊት እንዲያሳውቅ” በአዋጅ ማሻሻያው ግዴታ ተጥሎበታል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)