በሀገራዊ ምክክሩ ላይ አዲስ አበባን የወከሉ የባለድርሻ አካላት ወኪሎች የምክክር አጀንዳዎችን ለኮሚሽኑ አስረከቡ

በናሆም አየለ

በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችን እና የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን በመወከል በሀገራዊ ምክክር የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ሲሳተፉ የቆዩ ተወካዮች፤ በሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ላይ “ሊመከርባቸው ይገባሉ” ብለው የለዩአቸውን ጉዳዮች ለሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ምክር ቤት አስረከቡ። ተወካዮቹ ለምክክር ካስያዟቸው አጀንዳዎች ውስጥ “የአዲስ አበባ ባለቤትነት እና አወቃቀር፣ የቋንቋ፣ የሰንደቅ አላማ እና የህገ መንግስት” ጉዳዮችን የተመለከቱ ይገኙበታል ተብሏል።

ዛሬ ማክሰኞ ግንቦት 27፣ 2016 በአድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም የመሰብሰቢያ አዳራሽ በተካሄደ የርክክብ ስነ ስርዓት፤ ተወካዮቹ አጀንዳዎቹን በስምንት ርዕሰ ጉዳዮች በመከፋፈል ለምክክር ኮሚሽኑ እንዳቀረቡ ተገልጿል። ከእነዚህ ርዕሰ ጉዳዮች መካከል፤ “ታሪክ እና ትርክትን”፣ “የሃገረ መንግስት ግንባታ እና የሃገር አንድነትን”፣ “የአንድነት እና ብዝሃነትን” የሚመለከቱ የአጀንዳ ሃሳቦችን የያዙ እንደሚገኙበት ተነግሯል። 

አሁን በስራ ላይ ካለውን የኢፌዲሪ ህገ መንግስት ጋር የሚያያዙ፣ ተወካዮቹ የተመረጡበት የአዲስ አበባ ከተማ ጉዳይን በቀጥታ የሚመለከቱ፣ ኢትዮጵያ ከሌሎች ሀገራት ጋር ባላት የውጭ ግንኙነት ጉዳይ ላይ የሚያጠነጥኑ የአጀንዳ ርዕሰ ጉዳዮችም ለምክክር ከተመረጡት ውስጥ እንደሚገኙበት በሂደቱ የተሳተፉ ተወካዮች አስረድተዋል። የተቋማት ግንባታ፣ የምጣኔ ሀብት፤ ማህበራዊ እና ባህል ርዕሰ ጉዳዮችም እንዲሁ በአጀንዳነት መያዛቸውን ተወካዮቹ አብራርተዋል።  

የባለድርሻ አካላትን በመወከል በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ከተሳተፉት አንዱ የሆኑት አቶ አማር ዳርጌ፤ በእነዚህ ርዕሰ ጉዳዮች ስር ከተካተቱ ዝርዝር አጀንዳዎች መካከል “የአዲስ አበባ የባለቤትነት እና አወቃቀር፣ የሃይማኖት እኩልነት፣ የቋንቋ እና የህዝብ መዝሙር” ጉዳዮች እንዳሉበት ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።  

በስምንት ርዕሶች በተደራጁት አጀንዳዎች ውስጥ “የህገ መንግስት፣ የሃይማኖት እኩልነት፣ የአዲስ አበባ የባለቤትነትና የአወቃቀር፣ የቋንቋ፣ የህዝብ መዝመር ጉዳዮች ዋነኞቹ ናቸው” ሲሉ ከባለድርሻ አካላት ወኪሎች አንዱ የሆኑት አቶ አማረ ዳርጌ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። በሂደቱ የተሳተፉት ሌላኛዋ ተወካይ ጠበቃ አዲስ መሐመድ በበኩላቸው “የመንግስት አወቃቀር፣ የምርጫ፣ የመሬት፣ የብሔራዊ ጀግና እና ብሔራዊ ምልክት፣ የሰንደቅ አላማ” ጉዳዮች በአጀንዳነት መያዛቸውን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል።

ተወካዮቹ መዲናይቱን ወክለው የምክክር አጀንዳዎችን ያስረከቡት፤ ላለፉት ሰባት ቀናት በአዲስ አበባ ከተማ ደረጃ ሲካሄድ በቆየው የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ላይ ሲሳተፉ ከቆዩ በኋላ ነው። በአጀንዳ ማሰባሰቡ የመጀመሪያዎቹ ሶስት ቀናት፤ ከአዲስ አበባ ከተማ 119 ወረዳዎች በተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተወከሉ ከሁለት ሺህ በላይ ሰዎች ተሳትፈዋል። 

እነዚህ ተሳታፊዎቹ የወከሏቸው የህብረተሰብ  ክፍሎች፤ የመንግስት እና የግል ተቋማት ሰራተኞች፣ መምህራን፣ የንግዱ ማህበረሰብ፣ ወጣቶች፣ ሴቶች፣ ተፈናቃዮች፣ የተገለሉ ማህበረሰቦች እና የህብረተሰብ መሪዎችን እንደሆነ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ አስታውቋል። ተወካዮቹ በግዮን ሆቴል በነበራቸው የሶስት ቀናት ቆይታ፤ በ22 ቡድን ተከፍለው ከየህብረተሰብ ክፍላቸው ያመጡትን አጀንዳዎችን የመለየት እና የማደራጀት ስራዎችን ሲያከናውኑ ቆይተዋል።

በእነዚህ ተሳታፊዎች የተመረጡ 121 ተወካዮች ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመጣመር ከእሁድ ግንቦት 25 ጀምሮ“የአዲስ አበባ ከተማ አጀንዳዎች ናቸው” ያሏቸውን ሃሳቦች ለይተዋል። በቡድን በቡድን በመሆን በተካሄደው በዚህ የአጀንዳ መለየት ሂደት ከተሳተፉት ተወካዮች መካከል፤ በአዲስ አበባ ከተማ እና በሀገር አቀፍ ደረጃ ከሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፖርቲዎች፣ በአዲስ አበባ ከተማ ከተመዘገቡ የተቋማት እና ማህበራት የተወከሉ ግለሰቦች ይገኙበታል። የመንግስት ተወካዮች እና ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦችም በዚህ ሂደት ተሳታፊ ነበሩ። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)