የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማብቃቱን ተከትሎ በድንጋጌው ሳቢያ በእስር የቆዩ ሰዎች እንዲለቀቁ ኢሰመኮ ጥሪ አቀረበ

ባለፈው ጥር ወር መጨረሻ ለአራት ወራት የተራዘመው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማብቃቱን ተከትሎ፤ በእስር የቆዩ ሰዎች ሊለቀቁ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አሳሰበ። ኮሚሽኑ ዛሬ ረቡዕ ግንቦት 28፤ 2016 ባወጣው አጭር መግለጫ፤ “በተለያዩ የክልል አካባቢዎች የተጣሉ የእንቅስቃሴ ገደቦች እንዲነሱ” እና “ሌሎች ማህበረሰባዊ አገልግሎቶች” ወደነበሩበት እንዲመለሱ ጥሪ አቅርቧል። 

ብሔራዊው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋም በዛሬው መግለጫው፤ ካለፈው ዓመት ሐምሌ ወር መጨረሻ ጀምሮ ተግባራዊ ሲደረግ የቆየው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸምን በተመለከተ “ክትትል እና ምርመራ” ሲያደርግ መቆየቱን አስታውሷል። ይህንኑ መሰረት በማድረግም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ትግበራ ወቅት የተስተዋሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን እና ክፍተቶችን የሚያሳዩ ሪፖርቶችን በተለያዩ ጊዜያት ይፋ ማድረጉን ጠቅሷል። 

ኢሰመኮ በእነዚህ ሪፖርቶች ሲያቀርባቸው ከቆያቸው ምክረ ሃሳቦች መካከል፤ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጋር በተገናኘ ተይዘው “ተአማኒ ክስ ያልቀረበባቸው ታሳሪዎች እንዲሁም በማስገደድ የተሰወሩና ያሉበት ቦታ ሳይታወቅ የታሰሩ ሰዎች ሁሉ ከእስር እንዲለቀቁ” የሚጠይቀው ይገኝበታል። ኮሚሽኑ በዛሬው መግለጫውም፤ “በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አተገባበር አውድ ውስጥ” በእስር ላይ እንዲቆዩ የተደረጉ ሰዎች እንዲለቀቁ በተመሳሳይ መልኩ ጠይቋል።

በአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ ውስጥም ቢሆን “መሰረታዊ የሰብአዊ መብት መርህዎች ሊጣሱ አይገባም” የሚል አቋሙን በቀደሙ መግለጫዎቹ ሲያስተጋባ የቆየው ኢሰመኮ፤ ለአዋጁ የተቀመጠው የጊዜ ገደብ በማብቃቱ “ወደ መደበኛው የህግ አተገባበር ሂደት መመለስ” እንደሚገባ በዛሬው መግለጫው አሳስቧል።  ከዚህም በተጨማሪ አዋጁን መሰረት በማድረግ “በተለያዩ የክልል አካባቢዎች የተጣሉ የእንቅስቃሴ ገደቦች እንዲነሱ” እና “ማህበረሰባዊ አገልግሎቶች” ወደነበሩበት እንዲመለሱ ጥሪ አቅርቧል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)