በሙሉጌታ በላይ
በአማራ ክልል ለአስር ወራት የቆየው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መፍትሔ እንዳላመጣ የኦሮሞ ፌደራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) እና እናት ፓርቲ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገለጹ። ሌላኛው ተቃዋሚ ፓርቲ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ግን አዋጁ በክልሉ “የተወሰኑ መረጋጋት እንዲኖር አድርጓል” ሲል አስታውቋል።
ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የሆነው የሚኒስትሮች ምክር ቤት፤ በአማራ ክልል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲታወጅ የወሰነው ሐምሌ 28፤ 2015 ነበር። ምክር ቤቱ ውሳኔው ያሳለፈው፤ በአማራ ክልል በወቅቱ አጋጥሞ የነበረውን የጸጥታ መደፍረስ “በመደበኛ የህግ ማስከበር ስርዓት ለመቆጣጠር አዳጋች” መሆኑን በመጥቀስ፤ የክልሉ መንግስት ያቀረበለትን ጥያቄ መሰረት በማድረግ ነው።
ከአማራ ክልል በተጨማሪ እንዳስፈላጊነቱ “በየትኛውም የኢትዮጵያ አካባቢ” ተፈጻሚነት እንዲኖረው የተደረገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፤ የመጀመሪያ የቆይታ ጊዜው ስድስት ወራት ነበር። ሆኖም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን የማጽደቅ እና የጊዜ ቆይታውን በድጋሚ የማደስ ስልጣን በህገ መንግስቱ የተሰጠው፤ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባለፈው ጥር ወር መጨረሻ ባደረገው ስብሰባው አዋጁን ለአራት ወራት አራዝሞታል።
አዋጁ እንዲራዘም ካስፈለገባቸው ምክንያቶች አንዱ፤ ከአማራ ክልል ውጪ በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች ያሉ “አንዳንድ አዝማሚያዎች እና የጸጥታ ስጋቶች” ስላሉ መሆኑን የፍትህ ሚኒስትሩ ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ በዚሁ የፓርላማ ስብሰባ ላይ ተናግረው ነበር። ከዚህም በተጨማሪ “በእቅድ የታየዙ እና ቀሪ ስራዎችን ለመስራት ተጨማሪ ጊዜ የሚያስፈልግ መሆኑ” አዋጁ ለመራዘሙ ሌላኛው ምክንያት እንደሆነ ሚኒስትሩ በወቅቱ ጨምረው ገልጸዋል።
“ለህዝብ ደህንነት እና ሰላም በጣም ጠቃሚ እና አስፈላጊ ነው” የተባለለት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፤ ለተጨማሪ ጊዜ እንደማይራዘም ፍንጭ የተገኘው ከአንድ ወር ቆይታ በኋላ ነው። የተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑትን የአቶ ክርስቲያን ታደለን የህግ ከለላ ለማንሳት በመጋቢት ወር መጀመሪያ በፓርላማ በተካሄደ ስብሰባ ላይ፤ “የምንገምተው እና ተስፋ የምናደርገው በቀጣይ ጥቂት ወራት ውስጥ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ያበቃል” ሲሉ የፍትህ ሚኒስትሩ መናገራቸው ለዚህ በማስረጃነት ሲጠቀስ ቆይቷል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተጨማሪ የአራት ወራት ቆይታ በዚህ ሳምንት ቢጠናቀቅም፤ አዋጁ መነሳቱን በተመለከተ በመንግስት በኩል እስካሁን በይፋ የተሰጠ ማረጋገጫ የለም። “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ይህንኑ አስመልክቶ ለፍትህ ሚኒስቴር ጥያቄ ብታቀርብም፤ ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ምላሽ አላገኘችም። ይሁንና የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በትላንትናው ዕለት ባወጣው መግለጫ፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ “ማብቃቱን” አስታውቋል።
የአዋጁ የቆይታ ጊዜ መጠናቀቁን ተከትሎም በድንጋጌው ሳቢያ “በእስር የቆዩ ሰዎች እንዲለቀቁ”፣ “በተለያዩ የክልል አካባቢዎች የተጣሉ የእንቅስቃሴ ገደቦች እንዲነሱ” እና “ሌሎች ማህበረሰባዊ አገልግሎቶች” ወደነበሩበት እንዲመለሱም ኢሰመኮ ጥሪ አቅርቧል። ብሔራዊ የመብት ተሟጋች ተቋም፤ ለአዋጁ የተቀመጠው የጊዜ ገደብ በማብቃቱ “ወደ መደበኛው የህግ አተገባበር ሂደት መመለስ” እንደሚገባም በዚሁ መግለጫው ጨምሮ አሳስቧል።
እንደ ኢሰመኮ ሁሉ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አተገባበሩን በተመለከተ ተደጋጋሚ መግለጫዎችን ሲያወጡ የቆዩ ተቃዋሚ ፓርቲዎች፤ አዋጁ በሀገሪቱ ላለው የጸጥታ ችግር መፍትሔ አለማምጣቱን በመጥቀስ ይተቻሉ። የኦፌኮ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና፤ “የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ምን አይነት ችግር ለመፍታት እንደታወጀ አይገባኝም። አዋጁ በታወጀበትም ባልታወጀበትም ጦርነት ቀጥሏል” በማለት ለውጥ አለማምጣቱን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል።
መንግስት በመደበኛ የሕግ ስርዓት መግዛት በማይችልበት ወቅት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንደሚታወጅ የሚያስረዱት ፕሮፌሰር መረራ፤ “በኢትዮጵያ ሁኔታ ግን ሰው ለምን እንደሚጨነቅ አይገባኝም። ላለፉት 50 ዓመታት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ ነው የኖርነው” ሲሉ በአሁኑ ወቅት ያለውን ሁኔታም ከዚህ የተለየ እንዳልሆነ ያብራራሉ። “ብልጽግና [ፓርቲ] ላለፉት ስድስት ዓመታት ህግ እና ስርዓትን አክብሮ አይደለም እየገዛ ያለው። የጠበንጃ አገዛዝ ነው። የጉልበት አገዛዝ ነው። ብዙ ለውጥ የሚያመጣ አይመስለኝም” ሲሉም ያክላሉ።
የእናት ፓርቲ የብሔራዊ ስራ አስፈጻሚ አባል እና የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ዳዊት ብርሃኑም፤ ከኦፌኮው ሊቀመንበር ጋር የሚቀራረብ ሀሳባቸውን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። አቶ ዳዊት፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ “መፍትሔ ሳይሆን ይዞ የመጣው፤ ይበልጥ ግጭት፣ ጦርነት እና ቁርሾ ከፍ እንዲል ነው ያደረገው’’ ይላሉ።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ “እንደአስፈላጊነቱ በሌሎች አካባቢዎች ሊተገበር ይችላል” መባሉን የሚጠቅሱት የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ፤ እናት ፓርቲ አዋጁ “ለአማራ ክልል ብቻ የወጣ ነው” ብሎ እንደማያምን ይናገራሉ። “የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንደሀገር ህዝባችንን ታሳሪ እንዲሆን ያደረገ፣ አብዛኛው ህዝባችን በመፈራራት እንዲቀመጥ ያደረገ፣ በመሰረታዊ [ሁኔታ] የሚታዩ ችግሮች እንዳይፈቱ ምክንያት የሆነ ነው” ሲሉም ተችተዋል።
የኢዜማ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ዶ/ር ሙሉዓለም ተገኘወርቅ ግን፤ ከሁለቱ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች የተለየ ሃሳብ አላቸው። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ፤ በአማራ ክልል “በከተማዎች መሃል ይደረጉ የነበሩ የጥይት ድምጾችን [ያስቆመ]፣ ንጹሃን ዜጎች ላይ ይደርሱ የነበሩ መከራዎች በተወሰነ መልኩ መረጋጋት እንዲኖር ያደረገ ነው” ሲሉ ዶ/ር ሙሉዓለም ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።
“ማህበራዊ አገልግሎቶች ተቋርጠው ነበር። መንገዶች ተዘግተው ነበር። ሰዎች እንቅስቃሴ ማድረግ አይችሉም ነበር። አሁን እሱን አናይም” ሲሉም የፓርቲው ህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አጽንኦት ይሰጣሉ። አዋጁ በጠቅላላ “ምን አትርፏል፣ ምን አጉድሏል?’ የሚለውን ለማወቅ “በቂ ትንተና እና ሰፊ ጊዜ” የሚፈልግ ቢሆንም፤ በአዋጁ ምክንያት “በንጹኃን ዜጎች ላይ የደረሱ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን አስመልክቶ” ፓርቲያቸው ተደጋጋሚ መግለጫዎች ሲያወጣ መቆየቱን ዶ/ር ሙሉዓለም አስታውሰዋል።
በእነዚህ መግለጫዎችም “የመብት ጥሰት የፈፀሙ የጸጥታ አካላት ካሉ ለፍርድ እንዲቀርቡ፣ አግባብ ያልሆኑ እርምጃዎችን የወሰዱ በየትኛውም ወገን ያሉ አካላት ተጠያቂ እንዲሆኑ” ፓርቲው ይፋዊ ጥያቄ ማቅረቡንም ገልጸዋል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ “ጊዜያዊ መፍትሔ እንጂ ዘላቂ ሰላም የሚሰጥ እንዳልሆነ” ኢዜማ እንደሚያምንም የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አስታውቀዋል።
ዘላቂ መፍትሔ የሚገኘው “ከንግግር፣ ከምክክር፣ ኃላፊነትን ለመውሰድ ዝግጁ እና ቆራጥ አመራር” ሲኖር መሆኑን ዶ/ር ሙሉዓለም ያስገነዝባሉ። በተለይ የገዢው ፓርቲ አባል የሆኑ በክልሉ ያሉ አመራሮች “እግራቸው ሁለት ቦታ እየረገጠ፤ ለሰብዓዊ መብት ቀውስ፣ ለንጹሃን ዜጎች ማለቅ ምክንያት ባለመሆን” ለችግሩ መፍትሔ ማበጀት እንደሚችሉ አመልክተዋል።
የእናት ፓርቲው አቶ ዳዊት አሁን በኢትዮጵያ ላለው ችግር መፍትሔው “ድርድር ነው” ባይ ናቸው። ለዚህም “ሁሉን አቀፍ፣ ግልጽ እና በአግባቡ የሚመራ አስቸኳይ የሆነ የሀገር አድን ፖለቲካዊ ድርድር መከናወን አለበት” ብሎ ፓርቲያቸው በጽኑ እንደሚያምን ገልጸዋል።
የኦፌኮው ሊቀመንበር ፕሮፌሰር መረራ በበኩላቸው “ለዲሞክራሲ የሚደረግ ሽግግር” ላይ መሰራት እንዳለበት ያሳስብሉ። እኛን እኮ የሚሰማን አጣን እንጂ፤ ከመገዳደል ፖለቲካ ሀገሪቷ እና ሕዝቦቿ መውጣት አለባቸው [ብለናል]፤ ወደ መደራደር ፖለቲካ መግባት አለብን፤ ከዚያ ውጭ ምንም [መፍትሔ] የለም” ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)