በሙሉጌታ በላይ
በጋዜጠኞች፣ በኪነ ጥበብ ባለሙያዎች፣ በማህበራዊ ሚዲያ ተጽእኖ ፈጣሪዎች እንዲሁም በፖለቲከኞች ላይ እየተፈጸመ ያለው “የዘፈቀደ እስር” እንዳሳሰበው “ስብስብ ለሰብአዊ መብቶች በኢትዮጵያ” የተሰኘው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅት ገለጸ። እርምጃው “በአሳሳቢ ሁኔታ እየጠበበ የመጣውን የመገናኛ ብዙሃን ነጻነት እና ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት የማፈን አዝማሚያን የሚያመለክት ነው” ብሏል ድርጅቱ።
ሀገር በቀሉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ዛሬ አርብ ግንቦት 30፤ 2016 ባወጣው መግለጫ፤ በኢትዮጵያ በርካቶች ስለሚጋፈጧቸው እውነታዎች የዘገቡ እና አመለካከታቸውን ያንጸባረቁ ግለሰቦች መታሰራቸውን አስታውቋል። የግለሰቦቹ መታሰር፤ መሰረታዊ የሆኑትን የሰብዓዊ መብቶች “በግልጽ የሚጥስ” መሆኑን በመጥቀስም ድርጅቱ ተችቷል።
ኢትዮጵያ በፈረመቻቸው ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌም ሆነ በሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ዓለም አቀፍ ቃል ኪዳን ላይ፤ “አመለካከትን እና ሃሳብን ያለማንም ጣልቃ ገብነት የመግለጽ መብት” መረጋገጡን ድርጅቱ በመግለጫው አስታውሷል። በኢፌዲሪ ሕገ መንግስት ላይ የተካተቱን እነዚህን የሰብዓዊ መብቶች የኢትዮጵያ መንግስት ማክበር እንደሚገባው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቱ በመግለጫው አሳስቧል።
ኪነ ጥበብ በሰብአዊ መብት ዙሪያ ያለን ግንዛቤን ለማሳደግ “ወሳኝ ሚና” እንደሚጫወት የጠቀሰው የድርጅቱ መግለጫ፤ በኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ላይ የሚፈጸመው “የዘፈቀደ እስር’’ እና “በጥበብ ስራዎች ላይ የሚደረገው አፈና” ወደ “ኋላ የመመለስ አካሄድን” የሚያሳይ መሆኑን ገልጿል። ይህ አይነቱ አካሄድ፤ ለማህበራዊ ለውጥ እና ዕድገት ጠቃሚ የሆኑ ድምጾች ላይ “የመታፈን ስጋት” የሚፈጥር መሆኑንም ጠቁሟል።
የኢትዮጵያ መንግስት “በሰብዓዊ መብቶች ላይ የሚፈጽማቸውን ጥሰቶች” እንዲያቆም እንዲሁም የዜጎችን የመናገርና ሀሳባቸውን በነጻነት የመግለፅ መብት እንዲያከብር የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቱ አሳስቧል። ድርጅቱ “ሀሳባቸውን በነጻነት የመግለጽ መብታቸውን ተግባራዊ በማድረጋቸው ምክንያት ታስረዋል” ያላቸውን ሁሉንም ግለሰቦች፤ በአስቸኳይ እንዲፈቱም ጥሪ አቅርቧል።
“ስብስብ ለሰብአዊ መብቶች በኢትዮጵያ” ከተቋቋመባቸው ዓላማዎች ውስጥ፤ በሀገሪቱ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በሚፈጸሙበት ወቅት “መንግስት የእርምት ርምጃዎችን እንዲወስድ ጫና ማሳደር” የሚለው ይገኝበታል። “ለሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ እና እድገት” የሚሰራው ድርጅቱ፤ በኢትዮጵያ ውስጥ የሰብዓዊ መብት ሁኔታዎችን ለማሻሻል “ጥልቅ ጥናታዊ ምርምር” የማድረግ ዓላማም አለው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)