ሰላማዊ ሰልፍ በማስተባበራቸው በአዋሽ አርባ ታስረው ከቆዩ እስረኞች የተወሰኑት ወደ አዲስ አበባ ተዘዋወሩ

በሙሉጌታ በላይ

ባለፈው ህዳር ወር መጨረሻ በአዲስ አበባ ከተማ ሊካሄድ የነበረን ሰላማዊ ሰልፍ ሲያስተባብሩ ከነበሩ ግለሰቦች መካከል አራቱ፤ ለሁለት ወር ገደማ በእስር ላይ ከቆዩበት ከአዋሽ አርባ ወታደራዊ ካምፕ ከትላንት በስቲያ አርብ አመሻሽ ወደ አዲስ አበባ መዘዋወራቸውን ምንጮች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገለጹ። ከሰልፉ አስተባባሪዎች አንዱ የነበሩት እና ላለፈው አንድ ሳምንት በአዲስ አበባ ፖሊስ ቁጥጥር ስር የነበሩት አቶ የሺዋስ አሰፋ በትላንትናው ዕለት ከእስር ተለቅቀዋል። 

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኀበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ሊቀመንበር በነበሩት አቶ የሺዋስ እና በሌሎች ፖለቲከኞች አስተባባሪነት፤ በአዲስ አበባ ከተማ ህዳር 30፤ 2016 ሊካሄድ የነበረው ሰላማዊ ሰልፍ “የእርስ በእርስ ጦርነት ይብቃ፤ ሰላም ይስፈን” የሚል መሪ ቃል ነበረው። ሰላማዊ ሰልፉ ካነገባቸው ሶስት ዓላማዎች መካከል፤ የመከላከያ ሰራዊት “የአገር ሉዓላዊነትን ከማስጠበቅ ሚናው ውጪ” በኦሮሚያ እና አማራ ክልል ከሚሳተፍባቸው “ደም አፋሳሽ ተግባሮች” ተቆጥቦ፤ “ወደ ጦር ሰፈር እንዲመለስ” መጠየቅ የሚለው አንዱ ነበር። 

የሰላማዊ ሰልፉ አስተባባሪዎች “በአማራ ተወላጅነታቸው ምክንያት ያለምንም ፍርድ በየማጎሪያዎቹ ታፍነው ይገኛሉ” ያሏቸው ዜጎች፤ “ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ከእስር ወይም ከእገታ እንዲፈቱ” መጠየቅ ሌላው የሰልፉ ቁልፍ አጀንዳ ነበር። ሶስተኛው የሰላማዊ ሰልፉ ዓላማ፤ በተለይ በኦሮሚያ፣ አማራ እና ትግራይ ክልሎች የሚገኙ ተፈናቃዮች “የፖለቲካ ቁማር መጫወቻ መሆናቸው እንዲቆም እና በአስቸኳይ ወደቀያቸው እንዲመለሱ” የሚጠይቅ ነው። 

ሆኖም ሰልፉ ይደረጋል ከተባለበት ዕለት ሶስት ቀናት አስቀድሞ የፌደራል የጸጥታ እና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል ባወጣው መግለጫ፤ “በሰላማዊ ሰልፍ ሽፋን አዲስ አበባን የሁከት እና የብጥብጥ ማዕከል ለማድረግ የሽብር ተልዕኮ ተቀብለው በህቡዕ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ቡድኖች ሴራ መክሸፉን” አስታውቋል። የጋራ ግብረ ኃይሉ “እኩይ የጥፋት ሴራ” ሲል የጠራውን ድርጊት ለመፈጸም፤ “ተልዕኮ ወስደው ሲንቀሳቀሱ ነበሩ” የተባሉ 97 ተጠርጣሪዎችም በቁጥጥር ስር እንደዋሉም በወቅቱ ተገልጿል።

የጸጥታ እና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይሉ መግለጫውን ካወጣ ከአንድ ቀን በኋላ የሰላማዊ ሰልፉ አስተባባሪዎች በሰጡት መግለጫ፤ ሰልፉ መራዘሙን እና ከአስተባባሪ ኮሚቴዎች ውስጥ አራቱ መታሰራቸውን አስታውቀው ነበር። በወቅቱ መታሰራቸው የተገለጸው የሰልፉ አስተባባሪዎች፤ የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ (ኢህአፓ) ምክትል ተቀዳሚ ፕሬዝዳንት መጋቢ ብሉይ አብርሃም ኃይማኖት፣ የትንሳኤ ሰባ እንደርታ ፓርቲ አመራሮች አቶ ጊደና መድኅን እና አቶ ካልአዩ መሀሪ እንዲሁም የኢዜማ የቀድሞ አባል መምህር ናትናኤል መኮንን ናቸው።

ሁለቱ የትንሳኤ ሰባ እንደርታ ፓርቲ አመራሮች እና የኢህአፓ ምክትል ተቀዳሚ ፕሬዝዳንት፤ በአፋር ክልል በሚገኘው አዋሽ አርባ ወታደራዊ ካምፕ ለሶስት ወራት በእስር ከቆዩ በኋላ ባቀረቡት “አካልን ነጻ የመውጣት ክስ መነሻነት በፍርድ ቤት በተሰጠ ትእዛዝ” መለቀቃቸውን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ከሰሞኑ ባወጣው መግለጫው አስታውቆ ነበር። የኢዜማ የቀድሞው አባል መምህር ናትናኤል፤ በየካቲት ወር መጀመሪያ በፍርድ ቤት ተመሳሳይ ውሳኔ ቢሰጠውም፤ ከእስር የተፈታው ባለፈው ሳምንት መሆኑን ኢሰመኮ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጿል

ከሰላማዊ ሰልፉ አስተባባሪዎች መካከል በአዋሽ አርባ ወታደራዊ ካምፕ ቀርተው የነበሩ አራት እስረኞች፤ ከትላንት በስቲያ አርብ ግንቦት 30፤ 2016 አመሻሹን ወደ አዲስ አበባ እንዲዘዋወሩ መደረጋቸውን ምንጮች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ዋና መስሪያ ቤት ቅጽር ግቢ ወደሚገኘው የእስረኞች መቆያ የተዘዋወሩት የሰልፉ አስተባባሪዎች፤ የኢህአፓ ፓርቲ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር ዝናቡ አበራ፣ ጠበቃ አበራ ንጉስ፣ ዮሴፍ ተሻገር እና እዮብ ገብረ ስላሴ መሆናቸውን ምንጮቹ ጨምረው ገልጸዋል።

አራቱን የሰላማዊ ሰልፍ አስተባባሪዎች ጨምሮ ባለፈው አርብ ከአዋሽ አርባ ወደ አዲስ አበባ የመጡት እስረኞች 17 መሆናቸውን ምንጮች ጠቁመዋል። የእስረኞቹ ቤተሰቦች ትላንት ቅዳሜ ጠዋት በተለምዶ “ሶስተኛ ፖሊስ ጣቢያ” ወደሚባለው የእስረኞች ማቆያ በሄዱበት ወቅት፤ በስፍራው የነበሩት ፖሊሶች ያመጡትን  ምግብ እና ልብስ እንደተቀበሏቸው አስረድተዋል። ሆኖም ቤተሰቦች እስረኞቹን ለማነጋገር ሲጠይቁ “እንደማይቻል” እንደተነገራቸው አክለዋል።

በአዋሽ አርባ ወታደራዊ ካምፕ የነበሩ እስረኞች ወደ “ሶስተኛ ፖሊስ ጣቢያ” በተዛወሩ በማግስቱ፤ ለአንድ ሳምንት ያህል በዚያው ታስረው የቆዩት አቶ የሺዋስ ከእስር ተፈትተዋል። አቶ የሺዋስ “በማህበራዊ ሚዲያ ሁከት እና ብጥብጥ በማነሳሳት” ተጠርጥረው በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋሉት ግንቦት 23፤ 2016 እንደነበር ጠበቃቸው አቶ ሰለሞን ገዛኸኝ “ለኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። አቶ የሺዋስ ትላንት ቅዳሜ ሰኔ 1፤ 2016 ከሰዓት በኋላ የተፈቱት የመታወቂያ ዋስ በማስያዝ ነው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)