የፌደራል መንግስት በቀጣዩ በጀት ዓመት ለክልሎች የሚያከፋፍለው ድጎማ ምን ያህል ነው?

በተስፋለም ወልደየስ

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ለ2017 ካጸደቀው የፌደራል መንግስት በጀት ውስጥ፤ ለክልሎች እና ለሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች ድጋፍ የተመደበው የገንዘብ መጠን 222.6 ቢሊዮን ብር መሆኑ ለፓርላማ በቀረበ ሰነድ ላይ ተመልክቷል። የገንዘብ ድጋፉ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ8.6 ቢሊዮን ብር አሊያም የአራት በመቶ ጭማሪ አለው።

“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የተመለከተችው የቀጣዩ በጀት ዓመት የገንዘብ ድጎማ ዝርዝር ውስጥ ሁለት አዳዲስ ክልሎች ለመጀመሪያ ጊዜ ተካትተዋል። በነሐሴ 2015 ዓ.ም. በህዝበ ውሳኔ የተመሰረቱት የደቡብ ኢትዮጵያ እና የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች፤ በድጎማ ክፍፍሉ ዝርዝር በሚያገኙት የገንዘብ መጠን አራተኛ እና ስድስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። 

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል 15.2 ቢሊዮን ብር፤ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ደግሞ 12.8 ቢሊዮን ብር የድጎማ ገንዘብ ተመድቦላቸዋል። የፌደራል መንግስት ለክልሎች ከሚሰጠው የገንዘብ ድጋፍ፤ እንዳለፉት ዓመታት ሁሉ ከፍተኛውን መጠን የሚያገኘው የኦሮሚያ ክልል ነው።

በ2017 በጀት ዓመት ለኦሮሚያ ክልል የሚሰጠው የገንዘብ ድጎማ 74.8 ቢሊዮን ብር ነው። ይህ የገንዘብ መጠን ከዘንድሮው ጋር ሲነጻጸር በሶስት ቢሊዮን ብር ገደማ ከፍ ያለ ነው። በሁለተኛነት የሚከተለው የአማራ ክልል 47 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ የገንዘብ ድጋፍ ከፌደራሉ መንግስት የሚያገኝ ሲሆን ይህም ከዘንድሮው በ1.8 ቢሊዮን ብር ብልጫ ያሳየ ሆኗል።  

ለሶስት አስርት ዓመታት ከሚጠጋ ጊዜ በኋላ ከበጀት ክፍፍል ዝርዝር ውጪ የሆነው የቀድሞው የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልል ይዞት የቆየውን የሶስተኛነት ቦታ የተረከበው የሶማሌ ክልል ነው። የሶማሌ ክልል የፌደራል መንግስት ከመደበው የድጎማ በጀት የሚያገኘው ገንዘብ 21.6 ቢሊዮን ብር ነው።

በአምስተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው የትግራይ ክልል፤ ከ2014 ዓ.ም. ጀምሮ በነበሩ ተከታታይ ዓመታት ሲመደብለት የቆየው የድጎማ መጠን ከ12 ቢሊዮን ብር ሳይሻገር ቆይቷል። ክልሉ በ2017 በጀት ዓመት የሚያገኘው የድጋፍ ገንዘብ 13 ቢሊዮን ብር ደርሷል። በጦርነት ውስጥ የቆየው የትግራይ ክልል በቀጣዩ በጀት ዓመት የሚሰጠው የገንዘብ ድጋፍ ባለፈው ዓመት ከነበረው በአምስት ቢሊዮን ብር ጨምሯል። 

በክልሎች የገንዘብ ድጋፍ ዝርዝር ውስጥ ከሚካተቱት ሁለት የከተማ አስተዳደሮች አንዷ የሆነችው አዲስ አበባ 5.4 ቢሊዮን ብር ድጎማ ተመድቦላታል። የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር በበኩሉ ሁለት ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ ከፌደራል መንግስት በድጋፍ መልክ ያገኛል።

ለሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች እና አስራ ሁለቱ ክልሎች ከተመደበው የበጀት ድጋፍ ውስጥ፤ 215.3 ቢሊዮን ብር ያህል የሚሆነው የሚሸፈነው ከፌደራል መንግስት ግምጃ ቤት መሆኑ ለፓርላማ በቀረበው ሰነድ ላይ ሰፍሯል። ይህ የፌደራል መንግስት የበጀት ድጋፍ፤ “በክልሎች ለሚከናወኑት የገጠር መሰረተ ልማት፣ የአቅም ግንባታ እንዲሁም ድህነት ተኮር የወጪ ዘርፎች ትኩረት የሰጠ ነው” ሲል ሰነዱ ያብራራል።  

የከተማ አስተዳደሮች እና ክልሎቹ ከሚሰጣቸው የበጀት ድጋፍ ሌላ፤ “የዘላቂ የልማት ግቦችን ማሳካት እንዲችሉ” ተጨማሪ 14 ቢሊዮን ብር ተመድቦላቸዋል። ይህ የገንዘብ መጠን “በክልሎች ዘላቂ ልማት እና የኢኮኖሚ ትራንስፎርሜሽን ለማረጋገጥ የሚያግዙ” የአግሮ ፕሮሰሲንግ፣ የስራ ዕድል ፈጠራ፣ የአነስተኛ እና መካከለኛ መስኖ ልማት የካፒታል ፕሮጀክቶች እንደሚውል የበጀት ማብራሪያ ሰነዱ ያስረዳል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)