የ2017 በጀት የውጭ ምንዛሬ ግብይት ላይ የሚደረግ ማሻሻያን ታሳቢ አድርጎ እንዳልተዘጋጀ የገንዘብ ሚኒስትሩ ተናገሩ 

በተስፋለም ወልደየስ

የ2017 በጀት ሲዘጋጅ ብር ከዶላር አኳያ ያለውን የምንዛሬ ተመን የሚያዳክም ውሳኔ ተግባራዊ ይደረጋል በሚል ታሳቢ እንዳልሆነ የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ ተናገሩ። በኢ-መደበኛው እና በባንኮች በሚደረገው ይፋዊ ምንዛሬ መካከል ያለውን ልዩነት የሚያጠብ እርምጃን አስመልክቶ “የቀረበ ነገር የለም” ያሉት አቶ አህመድ፤ የፌደራል መንግስት በጀት የተዘጋጀው “የነበረው አካሄድ እንደሚቀጥል ታሳቢ ተደርጎ” መሆኑን አስታውቀዋል። 

የገንዘብ ሚኒስትሩ ይህን የተናገሩት፤ ዛሬ ማክሰኞ ሰኔ 4፤ 2016 በተካሄደው የህዝብ ተወካዮች መደበኛ ስብሰባ ላይ ከፓርላማ አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ ነው። አቶ አህመድ ዛሬ ፓርላማ የተገኙት፤ ለፌደራል መንግስት የተመደበውን የ2017 በጀት አስመልክቶ ዝርዝር መግለጫ ለማቅረብ ነበር።

ሚኒስትሩ 40 ደቂቃ ገደማ ከፈጀው የዛሬው የበጀት መግለጫ ንግግራቸው ግማሹን ያዋሉት፤ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ባለፉት ዓመታት አስመዝግቧል ያሉትን “ስኬቶች” እና ያጋጠሙትን “ተግዳሮቶች” ለማስረዳት ነው። የኢትዮጵያ መንግስት ላለፉት ሶስት ዓመታት ሲተገብረው የቆየው የመጀመሪያው የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራ በዚህኛው የሚኒስትሩ የንግግር ክፍል በስፋት ተዳስሷል።

ከዚህ ዓመት ጀምሮ ተግባራዊ መደረግ የጀመረው ሁለተኛው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ፤ ይቀርፋቸዋል ተብለው ከሚጠበቁ  ተግዳሮቶች መካከል አንዱ “የውጭ ምንዛሬ እጥረት” መሆኑን የገንዘብ ሚኒስትሩ ገልጸዋል። የፌደራል መንግስት “የውጭ ምንዛሬ አጠቃቀምን ለማሻሻል አስፈላጊ የሆኑ የማሻሻያ እርምጃዎች” እንደሚወስድ አቶ አህመድ በበጀት መግለጫ ንግግራቸው ቢጠቅሱም፤ ዝርዝሩን ሳያብራሩ ግን ቀርተዋል። 

ሆኖም ከእርሳቸው ንግግር መጠናቀቅ በኋላ መድረኩ ለጥያቄ ክፍት ሲደረግ፤ “የውጭ ምንዛሬ እጥረት” ጉዳይ በአንድ የፓርላማ አባል ተነስቷል። የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኀበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) የፓርላማ ተወካይ የሆኑት ዶ/ር አብርሃም በርታ፤ በገንዘብ ሚኒስትሩ ንግግር “ ‘ለውጭ ምንዛሬ እጥረት መፍትሔ እንሰጣለን’ ከማለት በዘለለ የተባለ ነገር የለም” ሲሉ ተችተዋል። 

 “ህጋዊውን እና ኢ-መደበኛውን የውጭ ምንዛሬ ገበያ እኩል ለማድረግ የሚደረጉ ሙከራዎች” እንዳሉ “ከአንዳንድ ወገኖች” መስማታቸውን የገለጹት የፓርላማ አባሉ፤ “የውጭ መንግስታት በብድር ምክንያት በኢትዮጵያ ላይ ጫና በመፍጠር” ይህንኑ ለማስፈጸም እንደሚንቀሳቀሱ የሚገልጹ መረጃዎችንም በተጨማሪነት ጠቅሰዋል። እንዲህ አይነቱ እርምጃ “የማንወጣው ችግር ውስጥ ይከተናል” የሚል የባለሙያዎች ትንታኔ እንዳለ አስገንዝበዋል።  

ፎቶ፦ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀጥታ ስርጭት የተወሰደ

“ችግሩን ለመቅረፍ የሚወሰዱ እርምጃዎች የህዝባችንን የኑሮ ሁኔታ የሚያረጋጋ፣ ሀገርን ጭምር የሚያረጋጋ መሆን መቻል አለበት” ያሉት ዶ/ር አብርሃም፤ የውጭ ምንዛሬ ችግርን ለመፍታት የሚወሰደው እርምጃ “በጥንቃቄ መታየት አለበት” ሲሉ አሳስበዋል። የገንዘብ ሚኒስትሩ ለፓርላማ አባሉ ስጋት አዘል አስተያየት በሰጡት ምላሽ፤ ለችግሩ ወደፊት የሚሰጠው መፍትሔ “በከፍተኛ ጥንቃቄ” እና “ብስለት በተሞላበት” መልክ እንደሚካሄድ ከአንድም ሁለት ጊዜ ማረጋገጫ ሰጥተዋል።

በህጋዊው እና በኢ-መደበኛው የውጭ ምንዛሬ ገበያ መካከል ያለው ክፍተት “ሰፊ” መሆኑን የገለጹት አቶ አህመድ፤ “ይሄንን የመቆጣጠር ስራ መስራት ይኖርብናል” ሲሉ ለፓርላማ አባላት ተናግረዋል። “የውጭ ምንዛሬ አቅርቦት የማሳደግ ጉዳይ፤ በአጠቃላይ ብዙ ስራ የሚጠይቅ ነው” ያሉት ሚኒስትሩ፤ ለዚህም “ምርታማነትን ማሳደግ”፣ “ኢንቨስትመንትን በከፍተኛ ሁኔታ ማስፋት” እና “ወደ ሀገር ውስጥ የሚላክ ገንዘብን (ሬሚታንስ) ማሳደግ” እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል። 

አቶ አህመድ “ቁልፍ የፖሊሲ መሳሪያ” ሲሉ የጠሩትን የውጭ ምንዛሬ እጥረት ለመቅረፍ የኢትዮጵያ መንግስት ከዚህ ቀደም ያደረጋቸውን ጥረቶችንም በማብራሪያቸው አንስተዋል። “በመጀመሪያውም ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አንዱ የተያዘ ዕቅድ ነው የነበረው። ሆኖም ግን በመጀመሪያው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አላሳካንም ብለን የያዝነው ጉዳይ ነው” ብለዋል የገንዘብ ሚኒስትሩ።  

“የውጭ ምንዛሬ ግኝት እና አቅርቦት አጠቃላይ የውጭ ምንዛሬ ግብይት ስርዓታችን sustianable እንዲሆን የማድረግ ጉዳይ፤ በቀጣይ በጥናት ላይ ተመስርቶ የማሻሻያው አካል ሆኖ የሚሰራ ስራ እንዳለ ሆኖ፤ በሚቀጥለው ዓመት በጀት በዚህ መልኩ ይደረጋል ተብሎ የቀረበ ነገር የለም” ሲሉ አቶ አህመድ ጨምረው ገልጸዋል። የ2017 በጀት የተያዘው “የነበረው አካሄድ እንደሚቀጥል ታሳቢ ተደርጎ ነው” ያሉት የገንዘብ ሚኒስትሩ፤ “ዘንድሮ የነበረውን ይፋዊ የውጭ ምንዛሬ መጠን (official exchange rate) ታሳቢ አድርጎ ነው በጀቱ የቀረበው የሚለውን መያዝ ያስፈልጋል” ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል።

ኢትዮጵያ በውጭ ምንዛሬ እጥረት ምክንያት የሚያጋጥማትን ጫና “ተቋቁማ እያለፈች” መሆኑን አቶ አህመድ በማብራሪያቸው ቢጠቅሱም፤ ጉዳዩ “ተጨማሪ ማሻሻያ እንደሚፈልግ” ግን አምነዋል። ማሻሻያው “በከፍተኛ ጥንቃቄ እና ብስለት በተሞላበት መልኩ ነው የሚመራው። በዚህ ዙሪያ ምንም የሚያሳስባችሁ ነገር መኖር የለበትም” ሲሉ ለፓርላማ አባላቱ ማስተማመኛ ሰጥተዋል። 

የገንዘብ ሚኒስትሩ በዛሬው ማብራሪያቸው በቀጣይ ዓመታት የሚጠበቁ “የፖሊሲ ማሻሻያ ኢንስትሩመንቶች” እንደሚኖሩም ጠቁመዋል። “የትኛው ኢንስትሩመንት መቼ ተግባራዊ ይደረጋል?” የሚለው “በከፍተኛ ጥንቃቄ” እና “ጥናት ላይ ተመስርቶ” የሚደረግ መሆኑንም ተናግረዋል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)