“ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር በተያያዘ” በእስር ላይ የሚገኙ ሶስት ጋዜጠኞች “አካልን ነጻ የማውጣት” አቤቱታ ለፍርድ ቤት አቀረቡ

በሙሉጌታ በላይ

የተፈጻሚነት የጊዜ ወሰኑ ባለፈው ሳምንት ካበቃው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጋር በተያያዘ በእስር ላይ የሚገኙ ሶስት ጋዜጠኞች፤ “አካልን ነጻ የማውጣት” (habeas corpus) አቤቱታ ለፍርድ ቤት አቀረቡ። አቤቱታውን በጠበቆቻቸው በኩል ለፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ያቀረቡት ጋዜጠኞች በቃሉ አላምረው፣ በላይ ማናዬ እና ቴዎድሮስ ዘርፉ ናቸው።

ጋዜጠኞቹ አቤቱታውን ያቀረቡት፤ የፌደራል ፖሊስ “ሕገ መንግስታዊ መብታቸውን በመጣስ በእስር እንዲቆዩ” በማድረጉ መሆኑን ከጠበቆቻቸው አንዱ የሆኑት አቶ አዲሱ ጌታነህ “ለኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ጋዜጠኞቹ “ካለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ መያዛቸው”፣ ከተያዙም በኋላ “በ48 ሰዓታት ውስጥ ፍርድ ቤት መቅረብ ሲኖርባቸው” ይህንን መብታቸውን መነፈጋቸውን ጠበቃው ገልጸዋል።

“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” የተመለከተችው “አካልን ነጻ የማውጣት” አቤቱታ፤ ጋዜጠኞቹ “ከፍርድ ውጭ ተገድደው የተያዙ” መሆናቸውን ይገልጻል። “አልፋ ሚዲያ” የተሰኘው የበይነ መረብ መገናኛ ብዙሃን መስራች እና አዘጋጅ የሆነው ጋዜጠኛ በቃሉ፤ በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከታወጀ ከሁለት ቀናት በኋላ ነበር።

የሚኒስትሮች ምክር ቤት፤ በዋነኛነት በአማራ ክልል እና እንዳስፈላጊነቱ ደግሞ “በየትኛውም የኢትዮጵያ አካባቢ” ተፈጻሚነት ያለውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲታወጅ የወሰነው ሐምሌ 28፤ 2015 ነበር። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በተወካዮች ምክር ቤት ከጸደቀ ከአንድ ሳምንት በኋላ፤ “ምኒልክ” በተሰኘ የበይነ መረብ ቴሌቪዥን ላይ በፖለቲካ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ፕሮግራም አዘጋጅ የነበረው ጋዜጠኛ ቴዎድሮስ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውሏል። 

“ኢትዮ ኒውስ” የተሰኘው የበይነ መረብ መገናኛ ብዙኃን መስራች እና አዘጋጅ የሆነው ጋዜጠኛ በላይ ደግሞ በህዳር 2016 ለእስር ተዳርጓል። ሶስቱም ጋዜጠኞች በፌደራል ፖሊስ አባላት በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ በአፋር ክልል ወደሚገኘው አዋሽ አርባ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ካምፕ ተወስደው “በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ለወራት በእስር እንዲቆዩ መደረጋቸው” በተደጋጋሚ ሲገለጽ ቆይቷል። 

ጋዜጠኛ በቃሉ ባለፈው ጥር ወር መጀመሪያ ላይ ለህክምና ወደ አዲስ አበባ እንዲመጣ የተደረገ ቢሆንም፤ “ህክምናውን ሳይጨርስ” በሚያዝያ ወር አጋማሽ በድጋሚ ወደ አዋሽ አርባ መወሰዱን ቤተሰቦቹ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር ተናግረዋል። ባለፈው ህዳር ወር መጨረሻ ወደ አዋሽ አርባ የተወሰደው ጋዜጠኛ በላይ፤ በወታደራዊ ካምፑ ለሰባት ወራት በእስር ላይ ከቆየ በኋላ አዲስ አበባ ወደሚገኘው የፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ እንዲዛወር ተደርጓል። 

የሶስቱ ጋዜጠኞች ጠበቆች ለፌደራል የመጀመሪያ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ስምንተኛ የፍትሐ ብሔር ችሎት ባቀረቡት “አካልን ነጻ የማውጣት” አቤቱታ ላይ በተከሳሽነት የጠቀሱት የፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮን ነው። አቤቱታው የቀረበው በሁለት መዝገብ ተከፍሎ መሆኑን ጠበቃ አዲሱ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።

ከአቤቱታ አቅራቢ ጋዜጠኞች መካከል ሁለቱ አሁንም በአዋሽ አርባ የሚገኙ በመሆኑ፤ የፌደራል ፖሊስ “እስረኞችን እስከማመጣቸው በሚል ጊዜ እንዳያጓትተብን አቤቱታውን በሁለት መዝገብ አቅርበናል” ሲሉ ጠበቃው አስረድተዋል። በአንደኛው መዝገብ በቃሉ እና ቴዎድሮስ ሲካተቱ፤ በሌላኛው ደግሞ የጋዜጠኛ በላይ ጉዳይ ለብቻው ቀርቧል።

የጋዜጠኞቹ ጠበቆች በአቤቱታቸው ላይ “[የፌደራል ፖሊስ] ደንበኞቻችንን እንዲለቅ ስናነጋግር፤ በቂ መልስ ካለመስጠቱም በተጨማሪ ደንበኞቻችን በአካል እንዳናገኝ ተከልክለናል” ሲሉ አስፍረዋል። በሕገ መንግስቱ “ማንኛውም እስረኛ ከጠበቆቹ፣ ከቤተሰቡ፣ ከሀይማኖት አባቶች እና ከወዳጅ ዘመዱ ጋር የመገናኘት መብት እንዳለው” የጠቀሱት ጠበቃ አዲሱ፤ ከዚህ ድንጋጌ በተቃራኒ ሶስቱም ጋዜጠኞች ከቤተሰቦቻቸው ጋር መገናኘት እንዳልተፈቀደላቸው ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።

ለፍርድ ቤት በቀረበው “አካልን ነጻ የማውጣት” አቤቱታ፤ የፌደራል ፖሊስ የጋዜጠኞቹን “ሕገ መንግስታዊ መብታቸውን በመጣስ በእስር ላይ ማቆየቱ ሕገ ወጥ ተግባር ነው” ሲሉ ጠበቆቹ አመልክተዋል። ጠበቆቹ አቤቱታቸውን እስካቀረቡበት ጊዜ ድረስም “በደንበኞቻቸው ላይ የቀረበባቸው ክስም ሆነ የተከፈተባቸው የጊዜ ቀጠሮ መዝገብ እንደሌለ” በመጥቀስ፤ ፍርድ ቤቱ የጋዜጠኞቹን “ሕገ መንግስታዊ መብት በማክበር ከእስር እንዲለቀቁ ውሳኔ እንዲሰጥላቸው” ጠይቀዋል። 

የጋዜጠኞቹን አቤቱታ የተቀበለው ለፌደራል የመጀመሪያ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ስምንተኛ የፍትሐ ብሔር ችሎት፤ የፌደራል ፖሊስ በጽሁፍ የተዘጋጀ ምላሹን ከነገ በስቲያ አርብ ሰኔ 07፤ 2016 በሬጅስትራር በኩል እንዲያቀርቡ ትዕዛዝ ሰጥቷል። ፍርድ ቤቱ ጋዜጠኞቹ ያቀረቡትን አቤቱታ በችሎት ለመስማት ለመጪው ማክሰኞ ሰኔ 11፤ 2016 ቀጠሮ ሰጥቷል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)